Sunday, 28 June 2020 00:00

ጣናን ከህመሙ ለማዳን የተደረገ አለማቀፋዊ ጥሪ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ዳጉ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባሳለፍነው ሳምንት “ጣና ሃይቅ የሀገር ሀቅ ሁለንተናዊ ትኩረት ለጣና” የተሰኘ አንድ የጉዞ መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ጉዞው ወደጣና ሲሆን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የበጐ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች ህብረት አባላት፣ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት፣ የፋሲል ከነማና ባህር ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችን ያካተተ ነው፡፡ የዛሬ ሳምንት በጐንደር ሊቦከምከም ወረዳ ተጓዦች የእምቦጭ ነቀላ ካካሄዱ በኋላ በነጋታው ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ብናልፍ አንዱ አለም፣ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተጓዦቹ እንቦጭ የነቀሉበትን የሃይቁን ክፍል ጐብኝተው ሲመለሱ በጉዳዩ ላይ ከተጓዦቹ ጋር በአቫንቲ ብሉ ናይል ሆቴልና ሪዞርት ምክክር አድርገው ነበር አቶ ደመቀም ጉዳዩ የአንድ ሰሞን ብቻ እንዳይሆን ለጉዞው አዘጋጅ ዳጉ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ ለአርቲስቶቹና ለጋዜጠኞ አደራ ብለዋል፡፡ በጉዞውና በእምቦጭ ነቀላው የተሳተፈችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት ጥቂቶቹን ስሜት እንደሚከተለው ታጋራናለች፡፡  

                   “አገሩን የሚወድ ሁሉ ጣናን ከችግሩ ለመታደግ መረባረብ አለበት”
                            (የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ)

    እኛ በዘርና በጎሳ ተከልለን፣ ጣናን የመሰለ ሀይቅ ከእጃችን ሊያመልጥ ነው፡፤ እከሌ የኔ ዘር ነው፤ ያኛው የሌላ ዘር ነው እንባባላለን፤ ከዘር ከጎሳና ከቀለም በፊት ሰው መሆናችንን መዘንጋታችን ያበሳጫል።  እኔ እዚህ ቦታ ላይ እምቦጭ ለመንቀልና ለማየት ስመጣ ሰው ስለሆንኩ ይመለከተኛል ብዬ ነው። እዚህ እምቦጭ ለመንቀል የተሰበሰቡትን ወጣቶች አንድነት፣ ትብብርና ኢትዮጵያዊ ወኔ ስመለከት ተስፋ ይሰጠኛል። አንድነታችንን ህብረታችንን፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ማንም አይነጥቀንም ብዬ በደስታ እሞላለሁ። አሁን በዙሪያችን እምቦጭ እየነቀሉ ያሉ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ የፋሲል ከነማና የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችና ሁላችንም፣ ዘርና መልካችን ሳንጠያየቅ፣ በአንድነት የወረረንን ጠላታችንን አረም፣ እስትንፋሳችን ከሆነው ጣና ሀይቅ ላይ ለመንቀል ሁላችንም ጫማችንን ልብሳችንን አውልቀን፣ እዚህ ጭቃ ውስጥ ነው ያለነው፤ ይሄ ያስደስተኛል። ይሄ ነው የሰው ልጅ ባህሪ።  ዛሬ እዚህ በመምጣቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ጣናን ለመታደግ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ወይ ለተባለው፣ ምንም ጥያቄ የለውም ያስፈልጋል፡፡  
ወደድንም ጠላንም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ፣ በእምቦጭ ላይ አቋም ተይዞ በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሳይሆን በቋሚነት ከተሰራ ጣና ከችግሩ ይላቀቃል።
ባለሀብቶችም ሆኑ የማስተባበር አቅም ያላቸውም የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።  ዝም ብሎ አገሬን እወዳለሁ ማለት አይሰራም። ስለዚህ አገር ከክልል፣ ከዘር፣ ከቀለምና ከጎሳ በላይ ነውና አገሩን የሚወድ ሁሉ ጣናን ከችግሩ ለመታደግ መረባረብ አለበት። እኛም አሁን ዘመቻውን ጀምረነዋል፤ እንቀጥልበታለን።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአያት የአባቶቻችን እዳ አለብን፤ እነሱ የተከበረ አገር ነው ያስረከቡን፤ ንፁህና ሕይወት የሆነውን ጣናን ነው የተውልን። እኛም ለተተኪዎቻችን የተከበረች ኢትዮጵያን ከእነሀብቷ ከእነሙሉ ተፈጥሮዋ ማስረከብ አለብን፡፡ ይህን ካላደረግን የሞራልም የሕግም ዕዳ ይዘን ነው የምናልፈው።

          “የአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ጥረቱ ይቀጥላል”
                (ጋዜጠኛ ማናዬ እውነቱ፤ የጉዞው አዘጋጅ)

         ዳጉ ኮሙኒኬሽን ይህንን “የጣና ሀይቅ የአገር ሀቅ” ሁለንተናዊ ትኩረት ለጣና የተሰኘውን የጉዞ መርሃ ግብር ይመለከተኛል ብሎ ሲያዘጋጅ እምቦጭ በአርቲስቶችና በጋዜጠኞች አቅም ብቻ ተነቅሎ ያልቃል ብሎ ሳይሆን አገራቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት እነዚህ አርቲስቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ወዘተ ያላቸውን እውቅናና ተቀባይነት ተጠቅመው፣ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚኖሩ የአገር ተቆርቋሪዎች መልዕክት ለማስተላለፍና ጣና አሁን ካለበት ዘርፈ ብዙ ፈተና አንጻር ሁለንተናዊ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፤  የጉዞው መሪ ቃል የሚገልጸውም ይህንኑ ነው። እቦታው ላይ ሆነን ጣና ያለበትን ሁኔታ ስንመለከት በእልህና በቁጭት፣ ጭቃ እስከ ወገባችን ውጦን ነበር ስንነቅል የነበረው። ይህ ሁኔታ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በስፋት እየተለቀቀ በመሆኑ፣ ሁሉም ሰው ትኩረት ሰጥቶ የበኩሉን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። ይህ የእምቦጭ ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ጥረት ማድረግ የጀመርነው ከ3 ዓመት በፊት ነበር። ሆኖም በለውጡ ሰሞን በተፈጠሩ አለመረጋጋቶችና መሰል ጉዳዮች የጣና ጉዳይ እንደገና መቀዛቀዝ ታይቶበት ነበር።  ይህን መቀዛቀዝ ማስወገድና ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ የሁላችንም ሀላፊነት ስለሆነ ዳጉ ኮሙኒኬሽንም ይህንን ተነሳሽነት ወስዶ የተሳካ መርሃ ግብር አከናውኗል። በአርቲስቶች፣ በጋዜጠኞችና በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አገር ወዳዶች ውስጥ ቁጭት ቀስቅሷል ብዬ አምናለሁ። ሌላው ቀርቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የስራ ጓዶቻቸው እኛ እምቦጭ ከነቀልንና ቅስቀሳ ካደረግን በኋላ ሰምተው ጣና ያለበትን ሁኔታ ጐብኝተው ተመልሰዋል:: ይሄ በጣም የሚያስደስት ነው ትኩረቱ ከዚሁ ይጀምራል ማለት ነው፡፡
አሁንም የጣና ጉዳይ የአንድ ሰሞን የዘመቻና የግርግር ጉዳይ ሆኖ እንዳይቀር ዳጉ ኮሙኒኬሽን ጥረቱን ይቀጥላል። በዚህ አጋጣሚ ይህ መርሃ ግብር እንዲሳካ አዎንታዊ ምላሽ ለሰጡ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ ለተከበሩ አርቲስቶቻችን፣ ለጋዜጠኞች፣ ለፋሲል ከነማና ለባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችና ለኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች ህብረት አስተባባሪዎች ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።
 
           “አረሙን ለማጥፋት በተሰራ ስህተት ነው እዚህ ደረጃ የደረሰው”
                     (ብርሃኑ ውብነህ፤ በአሳ ንግድ ረጅም ዓመት የሰሩ)

      ላለፉት 15 ዓመታትና ከዚያ በላይ በአሳ ንግድ ላይ የቆየሁ ግለሰብ ነኝ፡፡ የሀይቁንም ስነ ምህዳር በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ አረሙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ሊስፋፋባቸው የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች ለምን እንደተፈጠረም እገነዘባለሁ። በችግር አፈታቱ ዙሪያ ማለትም አረሙን ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ በተፈጠሩ ስህተቶች አረሙ ተስፋፍቶ እዚህ ደረጃ እንደደረሰ ማየት ችያለሁ። ችግሩ የገዘፈው የአረሙን ስነ ሕይወታዊ ባህሪና የሀይቁን ሥነ ምህዳር ያልተከተለ እርምጃ መውሰዳችን ለችግሩ መባባስ መንስኤ ነው ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ የአረሙ ስነ ሕይወታዊ ባህሪ ስንል፣ የሚበቅልበትን፤ የሚራባበትና የሚሰራጭበት ሁኔታ ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ጥናቶች መሰረት፤ እምቦጭ በሁሉም የአካል ክፍሎቹ እየተራባ፣ በንፋስ እየተገፋ የሚሰራጭ አደገኛ አረም ነው። ለመኖርና ሕልውናውን ለማጠንከርም ከውሃ ላይ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመውሰድ፣ ውሃ ላይ ተዘርግቶ፣ ውሃ በሀይል እየወሰደና እያተነነ የሚኖር መጥፎ የአረም ዝርያ ነው። ስለዚህ ይህን አረም ከምድር ለማጥፋት አበባ ሳያወጣና ፍሬ ሳያፈራ በጥንቃቄ ነው ማስወገድ ያለብሽ፡፡ እንዳልኩሽ አረሙን በእጅ መነካካቱ እየተበጣጠሰ ሲወድቅ፣ ቅጠሉም ስሩም ግንዱም መራባትና እንደገና ማንሰራራት የሚችል በመሆኑ ሥራው ታጥቦ ጭቃ ይሆናል። ስለዚህ ሳይጠና፣ አረሙ ተፈጥሮ ሳይታወቅ በቂ የሰው ሀይል ስላለ ብቻ ነው ሲነካካ ሲበጣጠስና ሲሰራጭ የኖረው። በምንም ሁኔታ አረሙን መነካካት አረሙ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው።  ምን አይነት ስትራቴጂ ብንጠቀም ነው አረሙን ማጥፋት የምንችለው ለተባለው በ2009 ዓ.ም አካባቢ፣ የክልሉ መንግሥት “አረሙ ከአቅሜ በላይ ሆነ፤ የማጨጃ ማሽን ይገዛ” ሲል፣ እኔ አዲስ አበባ ካለሁበት ሆኜ ችግሩ ምን እንደሆነ፣ ስለጣና ሥነ ምህዳር አጠቃላይ ነገርና በአረሙ ዙሪያ እንዲሁም አሁን አረሙን ለማስወገድ በሚል በዘፈቀደ የሚሰሩ ስህተቶች እንዲቆሙ የሚገልጽ 36 ገጽ ያለው ምክረ ሀሳብ ጽፌ አቀረብኩ። ይህን ተከትሎ የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በላይነህ፣ ያለሁበት አዲስ አበባ ድረስ መጥተው “በእርግጥ ሥነ ምህዳሩን አናውቀውም፤ በምን መልኩ ታግዘናለህ?” አሉኝ። “እኔ አሳ ከተከዜ እያመጣሁ አዲስ አበባ ነው የምነግደው፤ በአሁኑ ወቅት ከጣና ብዙ አሳ እየወጣ አይደለም፤ ስለዚህ መደበኛ ሥራዬን ትቼ መምጣት አልችልም፤ አልኩኝ። ከዚያ በኋላ በአማራ ቲቪ ምክረ ሀሳብና በጉዳዩ ዙሪያ ቴክኖሎጂ ያለው ከእኛ ጋር መስራት የሚችል ያመልክት ብለው አስነገሩ። ማስታወቂያውን ተከትሎ ካለኝ የረጅም ጊዜ ልምድ በመነሳት ማህበረሰብ አቀፍ የሆነ የጣናን ሥነ ምህዳርና የአረሙን ባህሪ ማዕከል ያደረገ ምክረ ሀሳብ አቅርቤ እያለሁ፣ በሶሻል ሚዲያ “አረም የሚያጭድ ማሽን እምቦጭን ያጠፋል” የሚል ዘመቻ ተከፈተ፡፡ የሁሉም ቀልብ ወደ ማሽኑ ተሳበ። የጣና ሰሜን ምስራቅ አካባቢ ተዳፋትና ከሀይቁ እስከ ሁለት ኪ.ሜ ድረስ ውሃ አዘል ስለሆነ ማሽኖቹን እስከ ሀይቁ ድረስ ማምጣት አይቻልም። ማሽኑ ለመንሳፈፍ ደግሞ 70 ሴንቲ ሜትር ይፈልጋል። ስለዚህ በጣና ሥነ ምህዳር እምቦጭን በማሽን ለማስወገድ በጭራሽ አይቻልም ብዬ ተቃወምኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ከአካባቢ ጥበቃ የቴክኒክ ቡድን አባላት ጋር ሳንግባባ ተለያየን እኔ በልዩነት ወጣሁ፡፡ “አይ የሕዝብ ግፊት አለ፤ ፖለቲካዊ መልክ ያዘ” ተባለ የሕዝብ ግፊት ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ግንኙነት የለውም፤ ጣናን የሚያድነው ሳይንስና እውቀት እንጂ የሕዝብ ግፊት አይለም፤ ችግሩ መፈታት ያለበት ሳይንስን፣ ህግንና ቴክኒክን መሰረት አድርጎ ነው። በ2009 ዓ.ም በሰው ሀይል አብዛኛው አረም ተነስቶ ውጤታማ የሚባል ሥራ ተሰርቶ ነበር። ነገር ግን እኔ አረሙ ተመልሶ እንደሚያንሰራራ እርግጠኛ ስለሆንኩ አረሙ ሊስፋፋ የሚችልበት አካባቢ ላይ አጥር ይሰራ፤ የሥነ ምህዳሩን መውጫና መግቢያ ስለማታውቁት ለእኛ ዕድል ስጡንና ውጤቱን እናሳያችሁ አልናቸው፡፡ እሱንም አልተቀበሉንም። ከዚያ በ2010 ዓ.ም ኤጀንሲው ከመቋቋሙ በፊት የእምቦጭን ጉዳይ የሚሰራው ግብረ ሀይል በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሲገመገም ባልተጠራሁበት ስብሰባ ገብቼ ልዩነቴን አሳየሁ። በሚዲያ ችግሩ ተፈታ ብላችኋል ግን በተጨባጭ ችግሩ አልተፈታም፤ እስከ ዛሬ ለአንድ ዓመት አድክማችሁኛል፤ አልተቀበላችሁትም፤ ተጠቀማችሁበትም አልተጠቀማችሁበትም መረብ በመጠቀም እምቦጭን ማስወገድ የሚል ቴክኖሎጂዬን በነፃ እሰጣችኋለሁ አልኩኝ። ከዚያ በአቶ ገዱ ትዕዛዝ እገዛ ተደርጎልኝ፤ ትንሽ የነበረውን ቴክኖሎጂ ወደ መካከለኛ አሳድጌ፣ ብዙ እምቦጭ በአንዴ ማውጣት የሚችልና ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ተመካክሬ የአዕምሮ ንብረት ያደረግኩትን ሥራ አሳየሁ፡፡
ቴክኖሎጂው ዊንች (ህንጻ ሲሰራ እቃ የሚያቀብለው መሳሪያ ትራክተር ላይ ይገጠምና አርሶ አደሮቹ ከእምቦጭ ጀርባ ሄደው መረብ ያስገባሉ። ሁለቱ መረብ ዳርና ዳር በክብ ብረቶች ይታሰርና ከኋላ መረቡ በእንግሊዝኛ (ሀ) ቅርፅ ይኖረዋል። ከዚያ 10 ወይም 15 ሜትር ገመድ ታሰሪለትና በዊንቹ ይጎተታል። ይህ ቴክኖሎጂ ከተነቀለበት እስከ 20 ሜትር ዳርቻ ድረስ መከመር ያስችላል። በጣምም ውጤታማ ነው። ዊንቹ ካደገ በአንድ ጊዜ አራት መቶ ካሬ ማፅዳት ይችላል። በአንድ ዊንች ስድስት ሄክታር አረም ማውጣት እንችላለን። እኔ በፕሮቶታይፕ ደረጃ ሰርቼ አሳየኋቸው። የኤጀንሲው ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ ስራ ከጀመሩ በኋላ መጥተው አዩት፤ ግን ምንም ምላሽ አልሰጡኝም። በኤጀንሲው አተገባበርም ላይ ክፍተት አለ፤ ምክንያቱም ኤጀንሲው ስትራቴጂክ ዶክመንት የለውም፤ በአጠቃላይ ተቀራርቦ ተናብቦ መስራት ላይ ችግር አለ፡፡ ይሄ ችግር ካልተቀረፈ ጣናን መታደግ አይቻልም ባይ ነኝ።    


             “የጣና ጉዳይ የመተንፈስና ያለመተንፈስ ጉዳይ ነው”
                   (አርቲስት ግሩም ኤርሚያስ)

      ባህር ዳር ብዙ ጊዜ እመጣለሁ፡፡ ከዚህ በፊትም እዚህ ሀይቅ ላይ “አባይ ወይስ ቬጋስ” የሚል ፊልም ሰርተን እናውቃለን። እማስታውሰው እዚህ ቦታ ላይ በታንኳ እየቀዘፍን ፊልም ሰርተንበታል። ያኔ በታንኳ የቀዘፍኩት ቦታ ላይ አሁን ካንቺ ጋር በእግራችን ቆመን እያወራን ነው ያለነው። ይሄ የመጀመሪያው ሀዘንና ድንጋጤ የፈጠረብኝ ጉዳይ ነው። የምሬን ነው የምልሽ፣ አሁን በምንነጋገርበት ሰዓት የተሰማኝ ስሜት ለምሳሌ ህጻናት ያማቸዋል፤ ግን ህመማቸውን መግለጽ አይችሉም። አሁን ላይ የጣና ጉዳይ በጣም አሞኛል። ግን ያንን ህመም እንዴት መግለጽ እንዳለብኝ አላውቅም። የጣና እምባ አልባ ጩኸቱ ይታያል፤ እንድናድነው የሚማፀነን ይመስለኛል፤ ልናድነው ይገባል። ጠቅለል ሳደርገው ጣና አሁን ላይ የታመመ ግን ህመሙን መግለጽ ያቃተው ሰውን ይመስላል።
ምን ይበጃል? ለተባለው እኔ ይበጃል የምለውን ልግለጽ፡፡ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን አሉ፡፡ በውሃና በሥነ ምህዳር እንዲሁም በዕፅዋት ሳይንስ ላይ የሚመራመሩ ማለቴ ነው። እነዚህ ኤክስፐርቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምር ሰርተው አንድ መፍትሄ ያመጣሉ የሚል እምነት አለኝ። አንድ ነገር ግን መጠቆም እችላለሁ። አንድ መጣጥፍ ሳነብ ያገኘሁት ነው፡፡
እንደ ጥቁምታ ሊያገለግል ይችላል። እምቦጭ አረም ከላቲን አሜሪካ እንደተነሳ ነው ጽሑፉ የሚጠቁመው፡፡ ከዚያ በአትላንቲክ ውያኖስ አድርጎ፣ ወደ አፍሪካ መግባቱንና በዚህም በርካታ አገሮች በእምቦጭ አረም የመጠቃት ችግር እንደገጠማቸው ይገልፃል:: ለምሳሌ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና.. ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ስንመጣ ደግሞ ኬንያ፣ ታንዛኒያና፣ ኡጋንዳ በቪክቶሪያ ሀይቅ ስለሚገናኙ ሀይቁ በእምቦጭ ተጠቅቷል ማለት ነው። ይህንን ካልን በኋላ እምቦጭን ለማጥፋት 3 ዓይነት ዘዴዎች ተጠቁመዋል። የመጀመሪያው ማሽን መጠቀም ነው። የሌሎች አገራት ተሞክሮዎችን ስንመለከት 10 ሄክታር የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት 6 ሺህ ሰዓት ያስፈልጋል። 60 ሺህ ሄክታር የእምቦጭ አረም ሀይቁን ቢሸፍን ይህንን ለማጥፋት 16 ዓመት ይፈጃል።
ሌላው ኬሚካል መጠቀም ነው። ይህ ግን በሀይቁ ውስጥ ያሉ ብዝሃ ሕይወትና ለእኛ ጠቃሚ የሆኑ እጽዋትን ያበላሻል። ስለዚህ ሶስተኛው አማራጭና ኬኒያ ተጠቅማ ውጤታማ የሆነችበትን እኛም ለምን እንዳልተጠቀምንበት ጥያቄ የሚሆንብኝ አንድ አማራጭ አለ፡፡ ለዚህ አረም አንደኛ ጠላት የሆነ አንድ የነቀዝ ዝርያ አለ። ነቀዙ “ውቭል ሳይድ” ነው የሚባለው፡፡ ይህ ነቀዝ ወደ አረሙ ከገባ እምሽክ አድርጎ በልቶ ነው የሚጨርሰው። ኬኒያ ቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ ተጠቅመውበት፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ስኬት አስመዝግበዋል። እኛ አገር ለምን እንደማንጠቀምበት አልገባኝም? እየተሰራበትም ካለ እሰየው። አንደኛ ወጪ ብዙ አይደለም፤ ሁለተኛ ስነ ምህዳሩ ላይ፣ ብዝሃ ህይወትም ላይ ሆነ በውሃው ላይ ምንም አይነት ጉዳት አያመጣም። እነዛ ነቀዞች አረሙን በልተው ሲጨርሱ የት ነው የሚሄዱት ለተባለው የጥናት ጽሑፉ፤ ነቀዞቹ ምንም አይነት ጉዳት እንደማያደርሱ፣ አረሙን ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፉ ሌሎች ብዝሃ ህይወትንም ሆነ ዕፅዋቶችን እንደማይነኩ… እንደውም ገና በዕጭ ደረጃ ያሉት ነቀዞች የእምቦጩን የውስጥ ክፍል እንደሚመገቡና ትልልቆቹ ሁሉንም የአረሙን ክፍል በልተው እንደሚጨርሱ እንጂ አረሙ ሲያልቅ ወዴት ይሄዳሉ የሚለው በአርቲክሉ ላይ አልተመላከተም፡፡  ነገር ግን ዜሮ ሪስክ እንደሆኑ፤ ምንም ጉዳት  እንደማያስከትሉ መጣጥፉ አፅንኦት ሰጥቶት አንብቤያለሁ። እኔ ባለሙያ አይደለሁም፤ ያነበበኩትን ነው የምነግርሽ፡፡ በኬሚካል ብዝሃ ህይወትና ስነ ምህዳር ሊጎዳ ይችላል፡፡ በማሽን 16 ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ስለዚህ ውጤታማው መንገድ በነቀዝ አስበልቶ መጨረስ ነውና በሀገራችንም ይሄ ነገር ቢጠና የሚለውን ለመጠቆም ነው።
ከዚህ ስትመለስ ምን ለማድረግ አስበሃል ለተባለው፣ እንግዲህ ሁሉም ሰው የራሱ ቋንቋ አለው፡፡ የኪነ ጥበብ ሰው ቋንቋው የሚሰራበት ዘርፍ ነው። በቋንቋዬ አንድ ነገር መስራት አለብኝ መቼና እንዴት የሚለውን ነገር አሁን መናገር አልችልም፤ ነገር ግን አንቺም እንዳልሽው የጣና ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳ ነው። ለምን ብትይ ጣና በዓለም ላይ ካሉ 250 ትልልቅ ከሚባሉ ሀይቆች አንዱ ነው የአለም ሀብትም ነው የጣና ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ብቻም አይደለም። ጣናን እያየነው ከደረቀ የምንጎዳውም እኛ ብቻ አይደለንም ልክ “በተርፍላይ ኢፌክት” እንደሚባለው እዚህ ያለ ችግር እዛ ያለውንም ይጎዳል፤ ስለዚህ እነ ግብፅም ሌላ ሌላ ሽኩቻ ውስጥ ከሚገቡ ለአባይ ከ60 በመቶውን ውሃ የሚለግሰውን ጣናን በመታደግ አባይን ማዳን አለባቸው። ስለዚህ የጣና ጉዳይ የመተንፈስና ያለመተንፈስ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ሰው አየር ልትነጠቅ ነው ቢባል፣ ምን የሚሆን ይመስልሻል? ልክ እንደዛው ጣናን ልንነጠቅ ስለሆነ ሁላችንም ተረባርበን ልንታደገው ይገባል። እንቅልፍ የሚያስተኛም አይደለም።

Read 1196 times