Saturday, 27 June 2020 15:06

ሞትና ፍቅር

Written by  ድርሰት፡- መሐመድጆን ኪለር ትርጉም፡- አውግቸው ተረፈ
Rate this item
(2 votes)

 አለን አውስተን በችኮላ አረማመድ፣ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ፣ ያሮጌውን ፎቅ ደረጃ በዳበሳ ከወጣ በኋላ መተላለፊያው ላይ ቆሞ በደብዛዛ ብርሃን በየክፍሉ በር ላይ የተጻፈውን ለማንበብ ሞከረ፡፡ ነገር ግን የሚፈልገውን በር ጽሑፍ ለይቶ እስኪያገኝ ድረስ ብዙ ደቂቃዎችን አባከነ:: ትንሽ ቆይቶ እንደምንም ብሎ አገኘው፡፡
አስቀድሞ ተነግሮት ስለነበረም በሩን ከፍቶ ገባ፡፡ ክፍሉ በጣም ጠባብ ሆኖ አንድ አሮጌ ጠረጴዛ፣ ካንድ አሮጌ የእንጨት ወንበርና ከአንድ ተሽከርካሪ ወንበር በስተቀር ምንም የቤት ዕቃ አይታይም፡፡ በአንደኛው የቤቱ ማዕዘን ጥግ ሁለት አሮጌ ዕቃ መደርደርያዎች አሉ፡፡ አንድ ደርዘን ያህል ጠርሙሶችና ብልቃጦች ተደርድሮባቸዋል፡፡
እንድ ሽማግሌ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠው ጋዜጣ ያነባሉ፡፡ አውስተን ቃል ሳይናገር ይዞት የነበረውን ካርድ ለሽማግሌው ሰጣቸው፡፡ “ተቀመጥ ሚስተር አውስተን” አሉ ሽማግሌው፣ በትህትና አነጋገር፣ “ስተዋወቅህ ደስታ ይሰማኛል”
 “እኔንም ደስ ብሎኛል” አለ አውስተን፣ “አንድ ዓይነት መድኃኒት..እ...እ..ልዩ ዓይነት መድኃኒት አለዎት የሚባል እውነት ነው?”
“የኔ ልጅ!” አሉ ሽማግሌው፣ “ንግዴ ይህን ያህል ትልቅ ሊባል አይችልም፡፡ የጥርስ ሳሙናና የመሳሰሉት ዓይነት ዕቃዎች እኔ ዘንድ አይገኙም። ግን እንደምታየው ለየት ያሉ ናቸው፡፡ የምሰጣቸው መድኃኒቶች እንደ ተራዎቹ ሁሉ ውጤታቸው በጉልህ ለዓይን የሚታይ አይደለም፡፡
“መልካም እንደዚህ ከሆነ…” አውስተን ሊቀጥል ሲል፣ “ይኸውልህ ለምሳ ያህል” ብለው ሽማግሌው አቋረጡት። ከመደርደርያው ላይ አንዲት ብልቃጥ አወረደና፣ “ይህ ፈሳሽ ነገር በወተት በወይንማ ወይም በሌላ መጠጥ ላይ ቢጨመር መልኩ ተለይቶ አይታወቅም፡፡ በሌላ ምርመራም ቢሆን ተለይቶ አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ይህን መድኃኒት መውሰዱንና አለመውሰዱን ለማወቅ ሬሳውን መርምረን ልንደርስበት አንችልም፡፡”
አውስተን በድንጋጤ ተውጦ፣ “መርዝ ነው ማለትዎ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
“የጓንቲ ማጠቢያ ልትለውም ትችላለህ” አሉ ሽማግሌው በግዴለሽነት አነጋገር:: “ምናልባትም ለጓንቲ ማጠቢያ ያገለግል ይሆናል፡፡ ሞክሬው አላውቅም፡፡ የሕይወት ማጠቢያ መርዝ ልትለውም ትችላህ፡፡ ሕይወት አንዳንዴ ንጽህና ያስፈልጋታል፡፡”
“የዚህ ዓይነት መድኃኒት አልፈልግም” አለ አውስተን፡፡
“ባትፈልገውም ምንም አይደል” አሉ ሽማግሌው፣ “ለመሆኑ ዋጋው ስንት እንደሆነ ታውቃለህ? አንድ ማንኪያ መድኃኒት አምስት ሺህ ብር ነው፡፡ ከዚያ በታች ንክች አላደርገውም፤ አንድ ሳንቲም ቢጎድል እንኳ”
“መድኃኒቶችዎ ሁሉ በጣም ውድ እንዳልሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” አለ አውስተን፣ በጥርጣሬ እያስተዋላቸው።
“ኦ!የኔ ልጅ፣ እንደሱ አይደለምኮ” አሉ ሽማግሌው፣ “ለምሳሌ ያህል፣ ለፍቅር መድኃኒት ያን ያህል ዋጋ መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ የፍቅር መድኃኒት ከሚፈልጉ ወጣቶች ከስንት አንዱ ነው፣ አምስት ሺህ ብር የሚኖረው፡፡ ገንዘብ ካለውማ ማን የፍቅር መድኃኒት ይገዛል?”
“ይህን በማለትዎ አመሰግንዎታለሁ::” አለ አውስተን፣ በደስታ ተውጦ፡፡ “ነገሩን የማየው እንደዚህ አድርጌ ነው፡፡” አሉ ሽማግሌው:: “አንድ ደንበኛዬን አንድ ጥሩ ዕቃ እሸጥለታለሁ፡፡ ሌላ ቀን ፍለጋ ይመጣል:: ዋጋ ቢወደድበትም አይቀርም:: አስፈላጊ ከሆነ  ገንዘብ አጠራቅሞ ይመጣል::”
“እንግዲያውማ” አለ አውስተን፣ “የፍቅር መድኃኒት መሸጥዎ ርግጠኛ ነገር ነዋ!
“የፍቅር መድኃኒት ባልሸጥማ ኖሮ” አሉ ሽማግሌው፣ ሌላ ብልቃጥ ከመደርደርያው ላይ እያነሱ፣ “ሌላውን ጉዳይ ባልጠቀስኩልህም ነበር፣ አንድ ሰው ምስጢር ጠባቂነቱ ሲረጋገጥ ነው መድኃኒት ሊሰጥ የሚችል”
“ታዲያ እነዚህ መድኃኒቶች ይሠራሉ ወይስ ...እ…” አውስተን ሊጠይቅ የፈለገውን አልጨረሰውም፡፡
“የተጠራጠርክ ይመስለኛል” አሉ ሽማግሌው፣ “መድኃኒቶቹ ፍቱንነታቸው የተረጋገጠ ነው። ብዙ ዕቃዎች በውጤታቸው ረክተውባቸዋል። አወሳሰዳቸውም በብዛት፣ ያለማቋረጥና እስከ ዘለቄታው መሆን አለበት፡፡”
“ይገርማል” አለ አውስተን፣ ሳይንሳዊነታቸውን ለማመን እያጠራጠረው፣ “እንዴት አስደናቂ ነገር ነው?”
“በመንፈሳዊ ረገድ ምን ይመስልሃል?” አሉ ሽማግሌው
“ጠቀሜታቸው ነው ጎልቶ የሚታየኝ” አለ አውስተን፡፡
“አዎን” አሉ ሽማግሌው፣ “ግዴለም አሉ … አንድ ማንኪያ መድኃኒት በብርቱካን ጭማቂ፣ ወይም በአልክሆል መጠጥ አድርገህ ብትሰጣት ጣዕሙ ተለይቶ አይታወቅም:: ታዲያ ምንም ያሀግል ደስተኛና ፍንዱቅ ብትሆን በጭራሽ ትለወጣለች፡፡ ሌላው ሁሉ ነገር ሁሉ ነገር ያስጠላትና አንተን ካጣች ብቸኝነትን ትመርጣለች፡፡
“ይህንስ በፍጹም ላምንዎት አልችልም፡፡ የኔይቱስ ወደ ፓርቲ መሄድ በጣም አድርጋ ትወዳለች” አለ አውስተን፡፡
“መድኃኒቱን ከቀመሰች በኋላ በጭራሽ ትጠላዋለች። ወደ ፓርቲ ከሄድን ከእኔ የተሻለ ሴት ያገኛል ብላ ስለምትፈራ!” አሉ ሽማግሌው፡፡
“ከእኔ ጋር ባላት ፍቅር የተነሳ በቅንኣት ትብከነከናለች ማለት ነው?” ብሎ ጮኸ አውስተን፣ ከመደሰቱ ብዛት፡፡
“አዎን! አንተን ለብቻዋ ጥቅልል አድርጋ ልታይህ ትፈልጋለች”
“ይህንንማ አሁንም የምትፈጽመው ጉዳይ ነው፡፡ ብቻ አውቃውና ተገንዝባው አይደለም፡፡
“መድኃኒቱን ከቀመሰች በኋላ የግዷን ታደርጋለች፡፡ አጥብቃም ትጠነቀቅብሃለች:: በሕይወቷ ውስጥ ካንተ ሌላ ምንም ነገር አትፈልግም”
“በጣም ግሩም ነው!” አለ አውስተን፣ ጮክ ብሎ፡፡
“የምትሰሪውን ሁሉ ለማወቅ ትፈልጋለች” አሉ ሽማግሌው፣
“ከእሷ ተለይተህ ሳለ ምን እንደደረሰብህ እያንዳንዱን ድርጊት ለማወቅ ትፈልጋለች:: ለምን እንዳዘንክ፣ ወይም ለምን ፈገግ እንዳልክ፣ ስለምን ጉዳይ እያሰብክ እንደሆነ ይህን ሁሉ ለማወቅ ትፈልጋለች፡፡”
“ይህማ ፍቅር ነው፡፡” አለ አውስተን፡፡
“አዎና” አሉ ሽማግሌው፣ “እንዴት አድርጋ መሰለህ በጥንቃቄ የምትይዝህ! ፀሐይ ላይ፣ ወይም ብርድ ላይ፣ እንድትቀመጥ ወይም ደክሞህ ከሆነ እረፍት እንድታደርግ ወይም ምግብ ላለመመገብ አትፈቅድልህም:: አንድ ሰዓት ያህል ዘግይተህ ከመጣህ በጣም ትበሳጫለች፡፡ ሰው የገደለህ ወይም ቆንጆ ሴት የጠለፈችህ ይመስላታል፡፡
“የኔይቱ ዲያና ይህን ያህል ታስብልኛለች ብዬ በጭራሽ አላስብም” አለ አውስተን፣ በደስታ ስካር፡፡
“ለግምት አስተሳሰብህ እዚህ ቦታ የለውም፡፡” አሉ ሽማግሌው፡፡
“እና በነገራችን ላይ መቼም ቆንጆ ሴቶች አልፎ አልፎ ማጋጠማቸው አይቀርምና የኋላ ኋላ አንዷ ውብ ካጋጠመችህ አትስጋ:: ያንተይቱ ዲያና መጨረሻ ላይ ይቅርታ ማድረጓ አይቀርም፡፡ ከፍተኛ ብስጭት ላይ መውደቋ አይጠረጠርም፡፡ የኋላ ኋላ ይቅርታ ታደርግልሃለች፡፡
“ይህ ሊሆን አይችልም” አለ አውስተን፣ በገነፈለ ስሜት፡፡
“አዎን ሊሆን አይችልም” አሉ ሽማግሌው፣ ነገር ግን ባጋጣሚ ሆኖ ከተገኘ መጨነቅ አይኖርብህም። በፍፁም ልትፈታህ አትፈልግም፡፡ እና ታዲያ እፎይ የምትልበት የደቂቃ ፍንካች ጊዜ እንኳን አትሰጥህም፡፡ ሆነ ብላ ልታበሳጭህ ግን አትፈልግ፡፡”
“ታዲያ ይህን ሁሉ ታምር የሚፈጥረው መድኃኒት ዋጋው ስንት ነው?” አውስተን ጠየቀ፡፡  
“ዋጋው” አሉ ሽማግሌው፣ “እንደ ጓንት ማጠቢያው ወይም እንደ ሞት መድኃኒት (መርዝ) የሕይወት ማጠቢያ የሚለውን ስም ያወጣሁለት እኔ ነኝ፡፡ ውድ አይደለም፡፡ አዎን አይደለም፡፡ የሞት መድኃኒት (መርዝ) አንዱ ብልቃጥ አምስት ሺ ብር ያወጣል፡፡ አንድ ሳንቲም እንኳን አይቀንስም፡፡ ይህን መድኃኒት ለመግዛት የሚፈልጉት ወጣቶች ሳይሆኑ ባመዛኙ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ እሱን ለመግዛት ሲሉም ብዙ ጊዜ ))ገንዘብ ማጠራቀም አለባቸው፡፡”
“የፍቅር መድኃኒት!” አሉ ሽማግሌው፣ ከጠረጴዛ ስር መሳቢያውን እየጎተቱ ከውስጡ አንዲት ቆሻሻ ብልቃጥ እያወጡ፣ “ዋጋው አንድ ብር ብቻ ነው”
(ለትውስታ ከአዲስ አድማስ ድረገጽ የተወሰደ፤ July 2018)


Read 2225 times