Saturday, 27 June 2020 15:45

ተራማጁ ገጣሚና አብዮታዊ ድርሰቶቹ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

  ሩሲያዊው አብዮተኛ ኮንድራቲን ፌዎዶሮቪች ክሪሎቭ፤ በፔተርቡርግ ከተማ የታኀሣሣውያን መሪ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 14 ቀን 1825 በሴናት አደባባይ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ያደራጀው ክሪሎቭ ነው፡፡ ዐመፀኞቹ በመንግሥት ትእዛዝ በቁጥጥር ሥር ሲውሉና ሲበታተኑ እሱም ተይዞ ታሠረ፡፡ በመጨረሻም በንጉሠ ነገሥቱ በቀዳማዊ ኒኮላይ ውሳኔ በ1826 የበጋ ወቅት የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ተገደለ፡፡ ከእርሱ ጋር የዐመፁ ጠንሳሾች ናቸው የተባሉ አምስት ወጣቶችም ተገድለዋል፡፡
ታኀሣሣውያን አብዮታዊ ግጥሞችን በመጻፍ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ የግጥሞቻቸው ርእስ ጉዳይ፤ አብዮትና እናት ሀገር የሚሉ ናቸው፡፡ ታኀሣሣውያን ዘውዳዊ ሥርዓትንና ገባርነትን በመቃወም፣ የፖለቲካና የሐሳብ ነጻነት ተግባራዊ እንዲሆን የታገሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በድርሰቶቻቸው ውስጥ ለአገራዊው ፖለቲካ ዋና ትኩረት የሰጡት፤ የሀገር ነጻነትና የሕዝቡ አርነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ የሀገራቸው ጥቅም እንዲጠበቅ በግንባር ቀደምትነት የታገሉትና  መሥዕዋትነት የከፈሉትም፡፡ ሌላው ርእስ ጉዳያቸው ደግሞ ሀገርን ከጣልቃ ገብ ጠላት መከላከል ይገባል የሚለው ሐሳባቸው ነው፡፡ ታኀሣሣውያን ይህንን ሁሉ ፖለቲካዊና አገራዊ ምኞታቸውን /አጀንዳቸውን/ ተግባራዊ ለማድረግ ሥነ ጽሑፍን የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ለዚህም የራሳቸው የሆነ የሥነ ጽሑፍ ልሣን ነበራቸው:: ‹‹ሰሜናዊ ኮከብ›› እና ‹‹አልማናህ›› የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የታኀሣሣውያን ገናና ገጣሚ ኮንድራቲን ክሪሎቭ፤ በታሪክ ላይ የተመሠረቱ ድርሰቶችን መጻፍ ይወድድ ነበር:: ከድርሰቶቹ ውስጥ ‹‹አስብ›› /ዱማይ/ የሚለው ይገኝበታል:: መቼም የሰው ልጅ ሆኖ ክፉውንና ደጉን ለይቶ ካልተራመደና በቅን ኅሊናው ካልተመራ፣ የአውሬነትና የአረመኔነት ጠባይ የተላበሰ እንስሳ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ እናም ማኅበረሰብ ልለወጥ፤ ልደግ ልሻሻል ሲል፤ የሩሲያ ገዥ መደቦች ቅን ኅሊና አጥተው፣ ሕዝብን እየረገጥንና እያታለልን እንኖራለን ቢሉም አልሆነላቸውም:: እናም ክሪሎቭ ከሩሲያ ነባራዊ ሁኔታ ተነሥቶ ‹‹አስብ›› /ዱማይ/ በተሰኘው በዚህ ግጥሙ፤ የሩሲያ ማኅበረሰብና ታሪክ መለወጥ እንዳለባቸው አጸህይቷል፡፡ የዱማይ ገጸ ባሕርይም በጣም ደፋር፣ ሁሉን ነገር ወሳኝና በራሱ የሚተማመን፣ አብዮተኛና ተዋጊ ነው፡፡ ለሕዝቡ ጥቅም ሲልም ለመሞት የተዘጋጀ ነው:: በክሪሎቭ ድርሰት ገጸ ባሕርይው ኢቫን ሱሳኒን የሩሲያ ገበሬ ነው:: ይህ አርሶ አደር በዐሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የሩሲያን የንጉሠ-ነገሥት ሚሃይሎቭን ከፖላንድ ወራሪዎች ጥቃት ሲያድነው እናያለን፡፡ ፖላንዶች ንጉሠ ነገሥቱን የከበቡት ለመግደል ፈልገው ነው፡፡ እናም ሱሳኒን ሚሃይሎቭን ከፖላንድ ወራሪዎች አዳነ ማለት ደግሞ መላ ሩሲያን ታደጋት ማለት ነው፡፡
ሱሳኒን ፖላንዶችን ለመምታትና ንጉሡን ለማዳን የቻለው በመጀመሪያ የፖላንዶች አስተርጓሚ ሆኖ ነው፡፡ በአስተርጓሚነቱ እየመራ መንገድ የሚያሳይ መስሎ የፖላንድ ወታደሮችን ወደ ጫካ ከወሰዳቸው በኋላ ሁሉንም ተረረም አድርጎ ይገድላቸዋል:: ሌሎች ፖላንዶች ደግሞ እሱን ይገድሉታል:: ክሪሎቭም ሕዝብ ከዳር ዳር የጠላውን የሩሲያ ዘውዳዊ ሥርዓት አስወግዶ፣ ሪፐብሊክ መንግሥት /ሕዝባዊ መንግሥት/ እንዲመሠረት ያለውን ፍላጐት፣ በፈጠራቸው ገጸ ባሕሪያትና በራሱም ትግል መሥዋዕትነት በመክፈል አሳይቷል፡፡ ታጋይ ቢሞት ትግል አይሞትም እንደሚባለው፣ ክሪሎቭ በዛሩ መንግሥት ወታደሮች በግፍ ቢገደልም፣ የሐሳብ ጠላቶቹ በጥቅምት ሶሺያሊስት አብዮት ተጠራርገው ሲጣሉ፣ የእርሱና የጓደኞቹ ዓላማ የሆነው፣ የደሀው ሕዝብ ምኞት በድል ተረጋግጧል፡፡
‹‹አስብ›› /ዱማይ/ የሚለውንና በጀግንነት ላይ የተመሠረተውን የክሪሎቭ ግጥም፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ የሩሲያ ቀይ ጦር እንደ መዝሙር እየዘመረ ይጠቀምበትና ወኔም ይገዛበት ነበረ፡፡ ክሪሎቭ ተራማጅና አብዮተኛ፣ የሮማንቲዝም ገጣሚ ሲሆን የክላሲዝም የአጻጻፍ ፈለግን ይከተል ነበር፡፡
ክሪሎቭ ‹‹ቮይናሮቭስኪ›› የተሰኘና እ.ኤ.አ በ1825 የታተመ ግጥም አለው፡፡ ይህን ግጥም የጻፈው ለጓደኛው ለአሌክሳንደር ቤዝስቱዤቭ ነው፡፡ ክሪሎቭ ‹‹እኔ ዜጋ እንጂ ገጣሚ አይደለሁም›› የሚል ሥራም አለው፡፡ በግጥሙ ውስጥ በዩክሬይን ታዋቂ ስለነበረው ስለ ጌትማን ማዜፕ የቀዳማዊ ጴጥሮስን መንግሥት ተቃውሞ ውጊያ ለማካሄድ ያስባል፡፡ በመሆኑም በምሥጢር ከስዊድን ንጉሠ ነገሥት ካርል ጋር ተመካክሮ ሩሲያን ለመውረር ይዘጋጃል:: በምክክሩ መሠረት ማዜፕና ካርል ሩሲያን በመውጋት ላይ እያሉ በቀዳማዊ ጴጥሮስ ጦር ተከበውና ተመትተው ይባረራሉ፡፡ የማዜፕ ዋና አላማ ዩክሬይንን ከሩሲያ ግዛት ለመገንጠልና ራሱ ንጉሠ ነገሥት ለመሆን ነው፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ዋና ገጸ ባሕርይ ማዜፕ ሳይሆን የወንድሙ ልጅ አንድሬይ ቮይናሮቭስኪ ነው፡፡
በጦርነቱ ፍጻሜ ላይ ማዜፕ ስለተሸነፈ ጓደኞቹ በሩሲያ ንጉሠ ነገሥት ውሳኔ ወደ ሳይቤሪያ ይላካሉ፡፡ አንድሬይ ቮይናሮቭስኪም ወደ ሩቁና ቀዝቃዛው ቦታ ከእነ ባለቤቱ ካዝያችካ ጋር ይላካል:: በመጨረሻ ካዝያችካ ትንሽም ሳትቆይ ሳይቤሪያ ውስጥ ትሞታለች፡፡ እርስዋን ተከትሎ ደግሞ ከብርድና ከቅዝቃዜ የተነሣ ቮይናሮቭስኪ ይሞትና አብረው ይቀበራሉ፡፡
  የታኅሣሣውያን የስቃይ  ገጽታ
በክሪሎቭ እምነት፤ ቮይናሮቭስኪ ለዩክሬይን ሕዝብ ነጻነት ሲል ግዳጁን የተወጣና መሥዕዋትነትን የከፈለ ጀግና ነው:: የቮይናሮቭስኪ ባለቤት ካዝያችካ ደግሞ የታኀሣሣውያንን ሚስቶች ትወክላለች፡፡ ታኀሣሣውያን የዛሩን መንግሥት በነቀነቁበት ወቅት ታሥረው ወደ ሳይቤሪያ ሲጋዙ፣ ሚስቶቻቸውም ባሎቻቸውን ተከትለው በመጋዝ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
ፔተርቡርግ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የታኅሣሣውያን መታሰቢያ ሐውልት


Read 720 times