Saturday, 27 June 2020 15:49

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

     “ችግኝ እንትከል” ሲባል “ባንዳፍ!” የማይል ያልሰማ ብቻ ነው
                            
                ጋሼ ተስፋ ሰካራም ቢጤ ነው፡፡ የመንደሩ ሰዎች “ቀና፣ ሃይማኖተኛና አገር ወዳድ ሰው ነው” እያሉ ያዝኑለታል፡፡ ሰውየው የባህል ስዕሎችንና ቅርፃቅርፆችን እየሰራ በመሸጥ ይተዳደራል፡፡ ወደ ማናቸውም የዕምነት ተቋም ጐራ ብሎ አያውቅም፡፡ ብቸኛ ቢሆንም ግን ደስተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ጋሼ ተስፋ በየቀኑ የሚያጋጥመውን ነገር ይድረስ “ለማላውቅህና ለማታውቀኝ አምላክ” በሚል ርዕስ ማታ ማታ ለእግዜር ደብዳቤ እየፃፈ ያስቀምጣል፡፡
ጋሼ ተስፋ በዚህ ሰሞን ሃሳብ የገባው ይመስላል፡፡ የቤቱን ግድግዳ ቀዳዳዎች በአንድ በኩል ሲደፍን፣ በሌላኛው ጐን ቆፍራ እየገባች የተጠራቀሙትን ደብዳቤዎች እየቦጨቀች የምታናድደው ዓይጥ እንኳ ያወቀችበት ይመስል ሰሞኑን ጠፍታለች፡፡ ያፈዘዘው እግዜርን የት አግኝቼ የፃፍኩለትን ደብዳቤ በሰጠሁት” የሚል ሃሳብ ካልሆነ በቀር ምን ሊሆን ይችላል?...ምናልባት ነው እንግዲህ፡፡ እንደዛ ደግሞ ለማለት በሰውየው መዝገበ ቃላት ውስጥ “ተስፋ መቁረጥ” የሚባል ነገር ተፈልጐ አይገኝም፡፡
የዘንድሮ ክረምት ከባድ ነው፡፡ እኛ ሰፈር ደግሞ በዚህ ሰሞን መብራት የለም:: “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፣ በእንትን ላይ እንትን” እንደሚባለው ሆኖብናል፡፡
ዛሬ ሰውዬአችን በነበረው ገንዘብ ሻማ ስለገዛ ፉት ማለት አልቻለም፡፡ ሞቅ ሲለው “ገንዘብ ብታጣ ተስፋ አለህ” እያለ መፎከር ቀርቶበታል፡፡
የሰፈር ልጆች “ጋሼ ተስፋ” ብለው ስም ያወጡለት ለዚህ ነው፡፡
ጋሼ ተስፋ በርዶታል፡፡ ቤቱ እንደደረሰ ከነልብሱ አልጋው ውስጥ ተወሸቀ፡፡ እንደ ወትሮው ከወገቡ ቀና ብሎ ለግዜር የሚልከውን ደብዳቤ መፃፍ ቢጀምርም የደነዘዘው እጁ አልታዘዝ እያለ አስቸገረው:: አልጋው አጠገብ ካለው ካርቶን ውስጥ ወረቀት አወጣና በሻማው ብርሃን ለኮሰ፡፡
እጆቹ ሲፍታቱ ደስ ስላለው ደብዳቤዎቹን እያወጣ በላይ በላዩ በማቀጣጠል ቤቱን አሞቀው፡፡
ብርዱ ለቆት ምቾት እየተሰማው ሲመጣ “ችግኝ እንትከል” ሲባል “ባንዳፍ!” የማይል ያልሰማ ብቻ ነው ዕንቅልፍ ተጫጫነውና ለጥ አለ፡፡ ንጋት አካባቢ የሚቆረቁር ድምጽ አነቃው፡፡ ዓይጧ ግርግዳውን እየቆፈረች ነው:: ሻማ ለማብራት ከማሰቡ በፊት መተንፈስ አቅቶት ነፍሱ ተጨንቃለች:: ያነደዳቸው ወረቀቶች የቤቱን አየር መርዘውታል፡፡ ለዚህ ነው መተንፈስ ያቃተው፡፡ ሰውነቱ ስለተዳከመ መገላበጥም ሆነ መጮህ አልቻለም፡፡ ጆሮው ግን ዓይጧ ግድግዳውን ስትቧጥጥ እየሰማ ነው:: ያቺ በመርዝ ሊገድላት፣ በወጥመድ ሊይዛት ሞክሮ ያቃተችውን ዓይጥ “በርቺ፣ ተስፋ እንዳትቆርጪ” ሊላት ፈለገ፡፡ ከንፈሮቹ ገን አልላቀቅ አሉ፡፡ ትንፋሹ መለስ ሲል “እየቃዠሁ ነው ወይስ በውኔ ነው የጮህኩት” ብሎ አሰበ፡፡ ዓይኖቹን ሲገልጥ ዓይጧ በቀደደችው ግድግዳ የሚገባው ብርሃን ቤቱን ሞልቶታል፡፡
ቆሻሻውም አየር ወጥቶ ንፁህ አየር በመግባቱ ህይወቱ እንደተረፈ ለመረዳት አልዘገየም፡፡ ወደ ቀዳዳው ሲመለከት ከትንሽቱ ዓይጥ ዓይን ጋር ዓይኖቹ ተገጣጠሙ፡፡ ተስፋን ውስጡ ተመለከተ፡፡ …ከዚያስ?
*   *   *
ወዳጄ፣- ከትናንት በስቲያ “በንጽጽር” አስተሳሰብ፣ አገራችን የዳቦ ቅርጫት ነበረች የተባለለትን ጊዜ አስታወሰኝ፡፡ ልጆች እያለን በአንድ ብር ሃያ ዳቦዎች እንገዛ ነበር። ያውም ከየሱቁ። ዳቦ ቤት ከሄድን ሀያ አራት ይሆናል። “በኛ” ዕድሜ የሕዝብ ቁጥር በአራት፣ የዳቦ ዋጋ በሁለት ሺ እጥፍ ጨምሯል። ከትናንት ወዲያ ጀምሮ ግን የዳቦ ታሪክ የተቀየረ ይመስላል። ያዝልቅልን እንጂ። እንጀራ በልቼ ስለማላውቅ የልጅነት ጓደኞቼ፡- “ተመስገን ወርቁ አንድ ዳቦ ስንቁ…” እያሉ ይቀልዱብኝ ነበር።… ብራቮ ! ሸገር ዳቦ!   
አንዳንድ አልሚዎች የአገርን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት ሲታትሩ፣ የብዙሃን ልብ በተስፋ ብርሃን ይሞላል። ከልማት ባንክና ከመሳሰሉት ላይ ቢሊዮን ብሮችን በልማት ስም ተበድረው እንደተሰወሩት ዓይነቶች ደግሞ በዜጎች ጉሮሮ ላይ ይቆማሉ።
ወዳጄ፡- በልማት ስም የተፈፀሙ ወንጀሎች ብዙ ናቸው፡፡ የደን ጭፍጨፋው ግን ይከፋል:: በደቡብ የአገራችን ክፍሎች በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች፣ ለግብርና ልማት በሚል ፕሮጄክት ሰበብ፣ ሰፋፊ መሬቶችን ተረክበው ዛፎቹን አስቆርጠው፣ መሬቱን አራቁተው፣ ግንዶቹን ወደ አዲስ አበባ ካጓጓዙ በኋላ ደብዛቸው የጠፋ ‘ኢንቨስተሮች’ ጥቂት አይደሉም።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የአገራችን የደን ሽፋን ከ15 በመቶ ያነሰ መሆኑ ያሳዝናል። በሚጨፈጨፉት ደኖች ምትክ ከስር ከስር፣ በቂ ችግኝ ባለመትከላችን ከአንድም ሁለት ጊዜ በተፈጥሮ ድርቅና ረሃብ ተቀጥተናል። በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ሳንዘናጋ በመትከል ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ እንደ ዜጋ ለአገር፤ እንደ ሰው ለህሊና ያስደስታል።
“ኑ ችግኝ እንትከል” ሲባል “በአንዳፍ!” የማይል ያልሰማ ብቻ ነው። ውጭ አገር የሚኖሩ የአገራችን ሰዎች እንኳን ‘በስማችን ትከሉልን’ እያሉ ሲለምኑ አያስቀናም? ዓባይ ላይ እንዲህ የምንረባረበው’ኮ በችግርና በድንቁርና የባከነውን ጊዜ በማካካስ፣ የዜግነት ዕዳችንን ለማወራረድ ነው። የድሃ አገር ልጆች ጥያቄ፤ “አገሬ ምን አደረገችልኝ?” ሳይሆን “ላገሬ ምን አደረግሁላት?” እንደሚሉት የሚሆነው በምክንያት ነው።
ወዳጄ፡- ከዕዳ ሁሉ የሚከብደው ደግሞ የሀሳብ ዕዳ መሸከም ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ለመስረቅ ፈልጎ ባይመቸው ወይም ሞክሮ ባይሳካለት ‘ሌባ’ መሆኑን ሌሎች አያውቁም፣ እሱ ግን ያውቀዋል። ሌላም ነገር እንዲሁ ነው። መጥፎ ሀሳቦች ሁሉ መወራረድ አለባቸው። በያንዳንዱ መልዓክ ውስጥ የተደበቀው ሰይጣን ወይም በሰይጣን ውስጥ የታሰረው መልዓክ ነፃ መሆን አለበት። እንደ ሚቲያ ካራማዞቭና ሌላው ሚቲያ ካራማዞቭ ወይም ኢቫንና ሌላው ኢቫን። በጥፋትና በጎነት መሀል መስመር ካልተበጀ ተያይዞ ገደል ይሆናል። እንደ ዶ/ር ጀኪልና ሚስተር ሃይድ!!   
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- በኦክስጂን እጥረት ሞት አፋፍ ላይ ደርሶ የነበረው ጋሼ ተስፋ ህይወቱ የተረፈው ዓይጧ በቆፈረችው ቀዳዳ በኩል በገባው ንፁህ አየር እንደሆነ አውግተናል። ከዚያን ቀን በኋላ ጋሼ  ተስፋ ለዓፍታ ያያትን አይጥ ምስል ከእንጨት ቀርፆ፣ አበባ በነሰነሰበት መደርደሪያ ላይ አስቀመጣት፤ ሲወጣና ሲገባም እጆቹን ግንባሩ መሀል አድርጎ…
“እግዜርን ያየሁት ባንቺ ውስጥ ነው”
እያለ ዝቅ ብሎ እጅ ይነሳታል።… እዚህ ጋ እግዜርና ብራህማን አንድ ይሆናሉ።
ነመስቴ!!


Read 733 times