Saturday, 04 July 2020 00:00

የኮሮና ታማሚዎችን በቤታቸው እንዲቆዩ ማድረግ ለወረርሽኙ መባባስ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)


              በኮሮና ቫይረስ ኮቢድ 19 የተያዙ ሰዎችን በቤታቸው እንዲቆዩ ማድረግ የበሽታውን ወረርሽኝ በማባባስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡ መንግስት ህሙማኑን ለይቶ ማቆየት የሚቻልባቸውን ሌሎች አማራጮች ሊመለከት ይገባል ብለዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያውና የጽኑ ህሙማን ሃኪሙ ዶ/ር ቴዎድሮስ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ የማድረጉ ተግባር በተለያዩ የአለማችን አገራት የተለመደና ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ጉዳይ ቢሆንም፤ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ለማድረግ መሞከሩ የበሽታውን ስርጭት በእጅጉ እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡
የብሔራዊ ስታትስቲክ ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርገው ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳብራሩት፤ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ መኖሪያ ቤቶች ከሰማንያ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት ባለ አንድ ወይም ባለ ሁለት ክፍል ናቸው፡፡ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ በአማካይ ከአራት እስከ አምስት የቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች የምግብ ማብሰያ፣ መኝታና ሳሎናቸውን በእነዚህ ክፍሎች ተወስነው የሚኖሩ በመሆናቸው ታማሚውን ለብቻው ለይቶ ለማቆየት የሚችሉበት ምንም ዓይነት መንገድ አይኖራቸውም፡፡
አሁን በጤና ሚኒስቴር ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በቤታቸው እንዲቆዩ የማድረጉ ውሣኔ አዋጭ አማራጭ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግስት ህሙማኑን ለይቆ ለማቆየት የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮችን ሊመለከት ይገባል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ አማራጮች መካከልም የግል ሆስፒታሎችና ከፍተኛ ክሊኒኮች ህሙማኑን ተቀብለው ህክምና መስጠት የሚችሉባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ህክምናውን በክፍያ ማግኘት የሚችሉ ወገኖችን በግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ህክምና ማግኘት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት፣ ወቅቱ ት/ቤቶች የተዘጉበትና በአገሪቱ ያሉ በርካታ ት/ቤቶች ነፃ የሆኑበት ወቅት በመሆኑ ብዙም ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በት/ቤቶች ውስጥ ተለይተው የሚቆዩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል::
የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ዳግማዊ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን እጅግ የጠበቀ የእርስ በርስ ግንኙነትና የማህበራዊ ኑሮ ትስስር ያላቸው በመሆኑ በቤታቸው ራሳቸውን ለይተው ከሌሎች ጋር ሳይነካኩ በመቆየት ከበሽታው አገግመው ይወጣሉ የሚለው አመለካከት በእጅጉ የተሳሳተ ነው ብለዋል:: በዚህ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ አምስትና ስድስት እየሆኑ በሚኖሩበት አገር፤ አንድ ሰው ራሱን ከቤተሰቦቹ አግልሎ ለብቻው ሊቆይ የሚችልበት ቤት ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው ብለዋል:: መንግስት በጽኑ ያልታመሙና ራሳቸውን መርዳት የሚችሉ ህሙማንን በተለያዩ ቦታዎች ለይቶ ማቆየት የሚችልባቸውን አማራጮች ሊያየና ሊጠቀም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ሊደረጉ የሚችሉበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡  

Read 2810 times Last modified on Thursday, 16 July 2020 20:05