Print this page
Saturday, 04 July 2020 00:00

ሲዳማ ክልል ዛሬ ርዕሰ መስተዳድሯን ትመርጣለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 “ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደው በጋራ እየለሙ የሚኖሩበት ክልል ይሆናል

        የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 10ኛው በህገ መንግስቱ ያልሠፈረ የፌዴሬሸኑ አባል ሆኖ ዛሬ የሚመሠረት ሲሆን የክልሉ ም/ቤት ይዋቀራል፣ ርዕሰ መስተዳድርም ይመረጣል፡፡
119 ወንበሮች ያሉት የክልሉ ም/ቤት በይፋ የሚመሠረት ሲሆን የዚህ ምክር ቤት አባላት ቀደም ሲል የሲዳማ ዞን ተወካዮች ሆነው በደቡብ ክልል ም/ቤት ውስጥ የነበሩና የሃዋሳ ከተማ ም/ቤት አባላት እንደሚሆኑ አዲስ የሚመሰረተው የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በእለቱም የክልሉን ም/ቤት የሚመሩ አፈጉባኤና ም/አፈጉባኤ ይመረጣል ያሉት ኃላፊው፤ ከዚሁ ስነስርዓት ጋር የክልሉ ህገመንግስትና የክልሉ ሰንደቅ አላማ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የክልሉ ሰንደቅ አላማ እንዲሆን የተመረጠው ከላይ አረንጓዴ፣ መሃል ሶስት ትናንሽ እና 1 ትልቅ ኮከብ ያረፈበት ሰማያዊ መደብ እንዲሁም ከታች ቀይ ሲሆን አረንጓዴው ልማትን፣ ልምላሜንና ሰማያዊ መደቡ የሲዳማ ህዝብ በፈጣሪው እንደሚያምን፣ እውነትን እንደሚናገር ለማመላከት ሲሆን በላዩ ላይ ያለው ከፍ ያለ ኮከብ ተስፋን፣ ትናንሾቹ ከዋክብት የሲዳማ የቀን አቆጣጠርን ይወክላሉ ብለዋል:: ቀዩ ደግሞ የተከፈለን መስዋዕትነት እንደሚያመለክት አቶ ገነነ ተናግረዋል፡፡
ከ7 ሰአት ጀምሮ ደግሞ የተለያዩ ክልሎች አመራሮች የሚሳተፉበትና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቶች የሚተላለፉበት የደስታ መግለጫ ክብረ በአል እንደሚደረግም አክለው ገልፀዋል፡፡
ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል ሲሆን ከቀድሞ ክልል ጋር በሚኖረው የንብረት ክፍፍል ጉዳይ ከሁለቱም የተዋቀረ ኮሚቴ ጥናት እያደረገ መሆኑንና በጥናቱ ውጤት መሠረት ክፍፍሉ እንደሚፈፀም አቶ ገነነ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ የሲዳማ ክልል ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደው በጋራ እየለሙ የሚኖሩበት ይሆናል ሲሉ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

Read 3593 times