Saturday, 04 July 2020 00:00

“የሰሞኑን ግርግር የፈፀሙና ያስፈፀሙ ሁሉ ለህግ ይቀርባሉ” - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የፌደራል ፖሊስ በድርጊቱ ላይ መጠነ ሠፊ ምርመራ ጀምሯል

                               በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ ግድያ ፈጽመዋል ተበለው የተጠረጠሩ 2 ሰዎች ተይዘዋል

           የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ግድያ ተከትሎ፣ የተፈጠረው ሰሞነኛ ግርግር ለረዥም ጊዜ ታቅዶበት የተፈፀመ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ይህን ድርጊት የፈፀሙና ያስፈፀሙ በሙሉ ለህግ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት፣ ሀገሪቱን ወደ አጠቃላይ የእርስ በእርስ ጦርነት የመክተት ዝግጅት ሲካሄድ እንደነበረ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በጦር መሣሪያ፣ በሚዲያ እንዲሁም በገንዘብ በመታገዝ ግርግሩ መፈፀሙን ጠቁመዋል፡፡
ሁከትና ግርግሩ ሰፍቶ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ የፀጥታ ሃይሎች በገለልተኝነት የተወጡትን ሃላፊነት ያደነቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህም ሀገሪቱ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማትን እየገነባች ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ሁከትና ግርግር በቀጥታ የተሳተፉ ብቻ ሳይሆን አስፈፃሚዎችና ፈፃሚዎች እንዲሁም ብሔርን ተገን አድርገው ለእኩይ አላማ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ይህ የህግ ማስከበር ተግባር ሲከናወንም የተጠርጣሪዎች ሙሉ ሰብአዊ መብትና ክብር ተጠብቆ እንደሚሆን አረጋግጣለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህልውና አሳልፎ የሚሰጥ ጉዳይ ሲፈጠር እዚህ ያለው ሃይል ራሱን መስዋዕት አድርጐ ኢትዮጵያን ማስቀጠል ይኖርበታል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በሚወሰዱ ጠንካራ እርምጃዎችም ማንም ከሠላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ ውጭ አማራጭ እንደሌለው እናሳያለን ብለዋል፡፡
አርቲስቱን ግድያ ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከትና ግርግር ጋር በተያያዘ ፖሊስ ፖለቲከኞንና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካቶችን በቁጥጥር ስር እያዋለ ሲሆን ዋነኛ ተጠርጣሪዎች ፍ/ቤት ቀርበውም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ብሄርን ከብሄር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሲሰሩ ነበር በተባሉት ኤምኤን፣ አስራት ቲቪ፣ ድምፂ ወያኔ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይም ምርመራ መካሄድ መጀመሩንና በአዲስ አበባ የሚገኘው ስቱዲዮአቸው መዘጋቱም ተገልጿል።
የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በቀጥታ በግድያው ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አንዲት ሴትና ሁለት ወንዶች ከትናንት በስቲያ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው፣ ፍ/ቤት ይሁንታ የሰጠባቸው መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ያስረዱት የፌደራል ጠ/አቃቤ ሕግ፣ የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ፤ ከወንጀሉ ጋር የተገናኙ ኤግዚቢቶች ተይዘው ምርመራ እየተጣራ መሆኑንና የአርቲስቱን ግድያ ሁኔታ ፍንጭ የሚሰጡ ማስረጃዎች መሰባሰባቸውን አስረድተዋል።
ፖለቲከኞቹ አቶ ጀዋር መሀመድና አቶ በቀለ ገርባ ጨምሮ አስክሬን በመቀማት ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል፤ ለሰዎች ሞት ምክንያትም ሆነዋል በሚል በተጠረጠሩት 38 ያህል ግለሰቦች ላይም ምርመራ እየተጣራ መሆኑንና ተጠርጣሪዎቹም ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርበው የተለያየ የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ያለመ ቅስቀሳና እንቅስቃሴ አድርገዋል የተባሉት የባልደራስ ሊቀ መንበር አቶ እስክንድር ነጋና ባልደረቦቻቸውም ፍ/ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። የአቶ እስክንድር መኖሪያ ቤት ላይ ብርበራ ተካሂዶም ለወንጀል መፈጸም ፍንጭ የሚሆኑ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አመልክቷል።
እነ አቶ ጃዋር መሀመድ ላይ የሚካሄደው የምርመራ ማጣራት ውጤትን ፖሊስ ለሐምሌ 9 ይዞ እንዲቀርብ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን አቶ ጃዋር መሃመድ በጥቅምት 2012 በኦሮሚያ ከተፈፀመውና ለ97 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ከሆነው ጥቃትና ግጭት ጋር በተያያዘም ምርመራ እንደሚጠራባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስገንዝቧል።
ከሰሞነኛው ክስተት ጋር በተያያዘ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ የኦኤምኤን፣ ድምፂ ወያኔና አስራት ቴሌቪዥን ላይ ምርመራ መጀመሩን፣ ወደኋላ ተሂዶም በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ የጠቆመው ጠ/አቃቤ ሕግ፤ በእነዚህ ጣቢያዎች ስቱዲዮም ላይ ብርበራ መካሄዱን አስታውቋል።

Read 3181 times