Saturday, 04 July 2020 00:00

የአርቲስቱ አሟሟት በህግ ባለሙያ ዓይን

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

“መንግስት የአርቲስቱን ግድያ እንደ አንደ ሰው ግድያ ሊመለከተው አይገባም”
                  (አቶ ቶማስ ታደሰ፤ የህግ ባለሙያ)


            የአርቲስት ሃጫሉ የግድያ ሁኔታ አንድምታው ብዙ ነው፤ ልጁ ካለው ታዋቂነት፣ ተቀባይነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት አንፃር ትልቅ የሚባል ነው፤ ያሳደረውም ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር በህልፈቱ አዝነናል፤ ነገር ግን ግድያው ትልቅ ሀገራዊ አንድምታ አለው፡፡ ይህንን በጥልቀት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መንግስትም ጉዳዩን ሲመለከተው እንደ አንድ ግለሰብ ግድያ ሊመለከተው አይገባም፡፡ ግድያው የአንድም ሰው አይደለም፡፡ ምርመራውም እንደ አንድ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እንደገደሉት ሰው ወይም የጠሉት ሰዎች እንዳስገደሉት ተደርጐ መመርመር የለበትም፡፡ ግድያው ሰፋ ያለ አንድምታ እንዳለው ሁሉ ምርመራውም በዚያው ልክ ሰፋ ተደርጐ መያዝ አለበት፡፡ መንግስትም ይህንን ይዘነጋዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ስለዚህ ዋናው ወንጀለኛ ላይ ወይም አንድምታው ላይ ለመድረስ ከጀርባ ያሉትን በርካታ ታሪኮች ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ምርመራው ተጠናቆ በግል ጠብ ነው የተገደለው ቢባል እዚያ የግል ጠብ ላይ ብቻ ልናተኩር እንችላለን፡፡ በግል ጠብ ካልሆነና ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ከሆነ ምርመራው ማተኮር ያለበት ከጀርባ ያሉ በርካታ ታሪኮች ላይ መሆን ይገባዋል። ለምን? ግድያው ከአንድ ግለሰብ ባሻገር ስለሆነ ማለቴ ነው።
መንግሥት ከምርመራው ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ አለበት? ምን ምን የሕግ አካሄዶችንስ መከተል አለበት ለሚለው፣ መርማሪዎች ይህን ጉዳይ በሚረከቡበት ጊዜ ፕሮፌሽናል መርማሪዎች መሰረታዊ የሆኑ ጽንሰ ሀሳቦችን ይመሰርታሉ። ለምሳሌ ይህንን ሰው ማን ሊገድለው ይችላል? በመግደሉስ ምን ሊጠቀም ነው የፈለገው? ምን አይነት ሪስክ ወስደውና ተጋፍጠው ነው ሊገድሉት የቻሉት? የሚሉና መሰል ጽንሰ ሀሳቦችን መጀመሪያ ይመሰርታሉ።
አሁን ላይ በተለያዩ አካላት የተለያዩ ፅንሰ ሀሳቦች እየተነሱ ነው ያሉት። ስለዚህ እነዚህ ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ተመርኩዘው መረጃዎችን መሰብሰብና ማስረጃዎችን ማጠናቀር ብሎም የተለያዩ ቴክኒኮችንና ዘዴዎችን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። ከዚያ ባሻገር ይህ ጉዳይ ከተፈፀመበት ጊዜ በኋላ ሌሎች የሆኑ የተከሰቱ ነገሮች አሉ። በግልጽ እንደሚታየውና እንደተነገረው፤  ወደ 100 የሚጠጉ ንፁሃን ተገድለዋል፣ የከባድና ቀላል ጉዳት እንዲሁም የበርካታ ንብረት መውደም ደርሷል፤ ይህ በመንግሥት የተለገፀው ነው።
በሌላ በኩል፤ የአስክሬን መሰረቅና መንገላታት መድረስም ሌላው ትዕይንት ነው። ታዲያ መርማሪዎች እነዚህ ሁሉ ከአርቲስቱ ግድያ በኋላ የተፈጠሩ ችግሮች ከግድያው ጋር ይገናኛሉ አይገናኙም የሚለውን ይፈትሻሉ። ለምሳሌ ግድያው ይህንን ውድመት ለመፈፀም የተደረገ ነው ወይስ ውድመቱ የደረሰው በአርቲስቱ ግድያ ተበሳጭተው ነው ወይስ የሁለቱም ቅልቅል ነው የሚለው ሁሉ መተንተን አለበት። በዚህ ሁሉ መሃል ተጨማሪ ሞት፣ የንብረት ውድመት፣ የአካል መጉደል እንዳይፈጠር መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረገ ምርመራው ሰፋ ብሎ ይቀጥላል ማለት ነው።
አርቲስቱ በመገደሉ ምክንያት የእሱ አድናቂዎች የእሱ ደጋፊዎች በብስጭት ተነሳስተው ከላይ የተገለፁትን ውድመቶች ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፤ ይህንን በማረጋጋት በኩል ሀላፊነታቸውን ያልተወጡ፣ ይባስ ብለው ነገሩን ወደ ማጋጋል የገቡ ካሉ በምርመራ ውስጥ ተካትተው ጉዳያቸው ይታያል። አርቲስቱን በመግደል ውድመቱ እንዲዳርስ አቅደውም ከሆነ ይሄ ሌላ ጉዳይ ስላለው የምርመራ ቅርፁም ስልቱም ይለያል ማለት ነው።
ጠቅለል ስናደርገው ሀጫሉን በመግደል ማን ምን ለመጠቀም አልሞ ነው የገደለው? የዚህ ሁሉ ሰው ሕይወትና መጥፋትና የንብረት መውደም የልጁን ቁጭት ለመወጣት ብቻ ነው ወይስ ሌላ ከጀርባው የተደበቀ አላማ አለው? የሚለው ሁሉ መፈተሽ አለበት።
መንግሥት በዚህ ላይ ማድረግ ያለበት ዋናው ነገር፤ በጉዳዩ ላይ ሌት ከቀን ሰርቶ ሕዝቡ የራሱ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት አጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው በሚገደልበት ጊዜ በምርመራው የማይጠበቁ ሰዎችን ሁሉ መመርመር የግድ ይላል። መርማሪዎቹም ሲጠረጥሩ ሰፋ አድርገው ነው የሚጠረጥሩት፤ በዙሪያው ማን ነበር? የዛን ቀን ውሎው ምን ይመስላል? ምን ብሎ ነበር እያሉ ብዙዎችን መጠርጠርና እየመረመሩ ሰፋ አድርገው የጀመሩትን እያጠበቡ ትክክለኛው ነገር ላይ ይደርሳሉ። በግልጽ በመንግሥትና በፍርድ ቤት ባልተገለፀበት ሁኔታ ድረስ ወደ መበየን እንዳንገባ እንጂ የተቀነባበረና የታቀደ ግድያ ስለመሆኑ መርማሪዎች ሊጠረጥሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ጉዳዩ ማህበራዊ አንድምታ ያለው በመሆኑ የተለያዩ ሃይሎች የተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ግለሰቦች የየራሳቸውን ጽንሰ ሃሳቦች ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ምርራውም ወደዚያ አቅጣጫ እንዲሄድላቸው መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በሰፊው ሁኔታ እየተንፀባረቀ ያለን ሃሳብ መርማሪዎች ምስክሮችን ቢጠይቁ ሊሰጉ ይችላሉ፡፡ እኔም ላይ መዘዝ ሊመጣ ይችላል በሚል ማስረጃ መደበቅና ማጥፋት ሊጀምሩ ስለሚችሉ መንግስት መፍጠን ነው ያለበት፡፡ ምክንያቱም የልጁ ግድያ በርካታ ሰዎችን ያሳተፈና ያካተተ ኦፕሬሽን ሊሆን ይችላል የሚለው ሃሳብ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ይህንን ሴራ የሸረቡት ግብጽ፣ ህወሓትና ሸኔ የተባለው የተደራጀ ቡድን ነው ብለዋል፡፡
የርዕሰ መስተዳድሩን ጉዳይ ከህግ አንፃር ስንመለከተው፤ እሳቸው ይህንን ጉዳይ ከሰፊው ህዝብ በበለጠና በቅርበት የሚከታተሉት እንደመሆኑ ፊት ለፊታቸው አስተማማኝ የሆነና ያዩት መረጃ እንዳለ መገመት ይቻላል፡፡ ያም ባይሆን ደግሞ ግለሰቡ ሃላፊነት ያለባቸው ሰው በመሆናቸው፣ እሳቸው የሚመሩት ክልል አብዛኛው ህዝብ የሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት በጣም እንዳስቆጣና እንዳሳዘነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ህዝባቸውን ለማረጋጋትና ህዝቡም የየራሱን ድምዳሜ እንዳይሰጥ ተጠርጣሪዎችን ጠቆም ጠቆም የማድረግ ሃላፊነት እንደሚኖርባቸው ግልጽ ነው፡፡
ነገር ግን ግለሰቦችን ወይም ተቋማትን በሚጠቁሙበት ጊዜ ምንም መሰረት ላይ ያልተቀመጠ ከሆነ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ ወደፊት ጉዳዩ እየጠራ በሚመጣበት ጊዜ ከባድና አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ እሳቤዎችና ጥርጣሬዎች ነው ይህ ሁሉ ህይወት ሲጠፋም፣ አካል ሲጐድልና ንብረት ሲወድም የነበረው፡፡ እነዚህን ምክንያቶችና እሳቤዎች ጋብ ለማድረግና ህዝብ ለማረጋጋትም ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል፤ የፌደራል ወንጀል ምርመራ፣ የፌደራል አቃቤ ህግ፤ ፌደራል ፖሊስ፤ ኦሮሚያ ፖሊስና አዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩን በጥብቅ ይዘውታል፡፡ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ኮሚሽነር ጀነራሉም እነዚህን እነዚህን አካላት ጠርጥረናል፤ እየመረመርን ነው ብለው ሲገልፁ ሰምተናል::
ከዚህ አንፃር የርዕሰ መስተዳድሩም ጥቆማ መሰረተ ቢስ ነው ለማለትና ያለ ፍንጭ ተናግረዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ የፌደራል አቃቤ ህግንና የፌደራል ወንጀል ምርመራን ሃሳብ አስተጋብተውም ስለሆነ መርማሪዎች ሥልጣን ስላላቸው ብዙ የሚያመጣው ችግር የለም፡፡
ነገር ግን በተቻለ መጠን ምን መደረግ አለበት መሰለሽ፤ ለምሳሌ አስከሬን ከመቀማትና ተጨማሪ ሰው እንዲሞት በማድረግ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉና ፍርድ ቤት የቀረቡ ግለሰቦች አሉ:: እነዚህ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ከጉዳዩ (ከግድያው ጋር) ቀጥተኛ ግንኙነት አለው ተብለው ሳይሆን ከላይ በገለጽኩልሽ ምክንያት ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ነጣጥሎ መመልከትም ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ፖሊስ ከ48 ሰዓት በላይ ማቆየት ስለማይችል እነዚህን ሰዎች በዚህ በዚህ ጠርጥሬ በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ፤ እኔ ጋር ናቸው ብሎ ለማሳወቅ ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት ማለቴ ነው፡፡
ከዚህ በፊት በተለይ በለውጡ ሰሞን ሰው ተዘቅዝቆ እስከ መገደልና ሌሎችም ዘግናኝ ድርጊቶች ሲፈፀም ያጠፋውን ሰው ተጠያቂ ማድረግና ለህዝብ ይፋ ባለማድረጉ አሁን ለሚከሰቱ ወንጀሎች የልብ ልብ መስጠቱን ህዝብ ይናገራል ለተባለው እንግዲህ የመንግስት ዋነኛና ተቀዳሚ ስራ የሰዎችን ሰብአዊ መብት መጠበቅና የማይገሰሰውን የሰው ልጅ የመኖር መብት ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ ሌሎች ሥራዎች በሌሎች አካላት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ የፋይናንሱ፣ የጤናው፣ የመሰረተ ልማቱ ሁሉ ነገር ማለት ነው፡፡ እነዚህን ከላይ የተገለፁትን የትኛውም የግል ተቋማት ሊሰጠን ይችላል:: በአብዛኛው መንግስት እየሰጠን ቢሆንም፡፡ በፍፁም በግለሰቦች ሊሰጡን የማይገቡትና በግለሰብ እጅ ሊገቡ የማይገባቸው የፖሊስ፣ የፍርድ ቤትና የመረጃና ደህንነት ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት በተለያየ ጊዜ መጠናከር የሚያስፈልግባቸው ምክንያት በሁሉ ነገር ዝግጁ ሆነው፣ ቢችሉ ቀድመው መተንበይ፤ ማክሸፍ ባይችሉ ችግር ሲፈጠር ብዙ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ስር ማዋልና ያንን መምራት እንዲችሉ ነው፡፡ ሌላው የምርመራው ክፍል ምንም እንኳን ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ቢሆኑም ምንም እንኳን የሚደግፏቸው ቢኖሩና ባይኖሩም በህልፈት ሁሉም ሰው እኩል ነውና እኩል መስተናገድ አለባቸው፡፡
በሌላ በኩል፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተለየ ሃሳብ የሚያራምዱና የማንደግፋቸውም ቢሆኑ እነዚህ ግለሰቦች ሊታሰሩልን ይገባል ሊገደሉን ይገባል፤ ብሎ ማሰብ ከህግ አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ የማንደግፈውም ቢሆን ነፃ ሊሆን ይችላል፡፡ የፈለገው ያህል ብንደግፈውና ብንወደውም ሲያጠፋ መጠየቅ አለበት፡፡ ማህበረሰቡ ይህ መዘንጋት የለበትም፡፡ መንግስትም  ግለሰቦች ሲያጠፉና ሲጠየቁ በማሳየት በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ በህግ ፊት ሁሉም እኩል እንደሆነ፣ ከምንም በላይ ህግ የበላይ እንደሆነ ማሳየትና የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማረም ተቀዳሚ ስራው ሊሆን ይገባል፡፡ አሁንም መሆንም ያለበት ይሄው ይመስለኛል፡፡
ስለሆነም የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ የደረሰውን የንብረት ውድመት አጣርቶና መርምሮ ለህግ በማቅረብ፣ ለሌሎች የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦችም ንብረታቸውን ላጡትም ባጠቃላይ መንግስት የሚክስበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡


Read 765 times