Saturday, 04 July 2020 00:00

“የተሸነሸነች ሀገር!” በበላይ ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

  ግጥም የእልፍኝና የአደባባይ ቋንቋችን ነው ብለን በምንኮፈስበት ሀገር፤ በተለያዩ ዘመናት የተወለዱ ገጣሚያን በርካታ ስንኞች ቢደረድሩም፣ ዘመን የዘለቁት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በግዕዝ ስነፅሁፍ ውስጥ ያደጉ ቃላት ይዞ በዜማ እየሰለጠነ የመጣው ግጥማችን፤ በ14ኛው ክ/ዘመን ተወልዶ ከሺ ዓመታት በላይ ዘልቋል ስንል በወጉ አድገው ተሰጥኦዋቸውን ጠብቀው ለታሪክ የበቁት ግን ያን ያህል የሚያስፎክሩ አይደለም፡፡
ጥሎብን እኛም በተረት እንደለመድነው ከጆሮ ወደ ጆሮ እየተቀባበልን መጣን እንጂ በግጥም ምሉዕ መልክ፣ በዚህና በዚያ መመዘኛ ልብ ያስቆረጥማል፤ ጆሮ ያስደንሳል! የምንለው ግጥም እምብዛም ነው!
በዚህኛውም ዘመን እንደ ሌላው ዘመን ገጣሚዎች ተወልደዋል፡፡ አንዳንዶቹ ራሳቸውን “ገጣሚ ነን” ብለው ኮፍሰዋል፡፡ መዝኖና ለክቶ በዚህ ምክንያት “እገሌ ድንቅ ነው!” ያላቸውም አልጠፉም፡፡ መንግስቱ ለማ እንደሚሉት፤ ግጥም ሚዛንና መለኪያ አለው፡፡ ስድ አይደለም፣ ደነዝ አይሆንም፤ ስሜትን ታጥቋል!
በግሌ በዚህ ዘመን ግጥሞች የተሻለ መልክ ይዘው መጥተዋል የምልበት የራሴ መመዘኛ፤ አተያይና የሃሳብ ጥልቀት ነው:: ደረቅ ግድግዳ ያልሆኑ፣ መስኮትና ሽንቁር የተፈጠረላቸው፤ ብርሃን የሚያስገቡ ግጥሞች ያላቸው ወጣቶች አሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ብዙዎቹ ብቅ ብለው መጥፋታቸው ነው፡፡ በተለያዩ ሰበቦች ታይተው ሳይጠገቡ ይከስማሉ፡፡ ንባብ ትተው ጭብጨባ ሲያዳምጡ፣ በራሳቸው ሰክረው ሳይጠኑ የጠወለጉ፤ ንባብ ሸሽተው በአንድ አካባቢ መሀረቦሽ ሲጫወቱ ያበቃሉ፡፡ በዘመኑ የንስር ዓይን አላቸው፣ ሃሳቦችን በተለየ ዓይን ያያሉ ብዬ ተስፋ ከማደርጋቸው ገጣሚያን መካከል በላይ በቀለ ወያ አንዱ ነው፡፡ በላይ ማለትም ሃሳብ ዘርግቶ፣ ሴራ ገጣጥሞ ማስደነቅ ይችላል፡፡ አብዛኛው ሃሳቡ ስሜት ላይ ቢሆንም ስለ ሀገር ሲያሰናኝ፣ ስለ አገር ሲያውጠነጥን ግሩም ነው፡፡ አተያይ ደሞ በግጥም አዋቂዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ አሮጌውን ነገር አዲስ አድርጐ ማምጣት ምናብ፣ ስልትና ተሰጥኦ ይጠይቃል፡፡
ዛሬ ለዳሰሳ ያሰብኳት ሰሞኑን ያነበብኳት “ኩልና ጥላሸት” የተሰኘች መፅሐፍ በ110 ገፆች ተደጉሳ፤ በርካታ የህይወት ዳናዎችን፣ የተስፋ አድማሳትን የጨለማ ግርዶሽን የሰቀቀን ፍቅርን፣ የመለየት ዐፀድን ይዛለች፡፡ የትኛውም ስነፅሁፍ ዘመን ረግጦ እንደሚቆም ሁሉ የበላይ ግጥሞችም የዘመኑን ፖለቲካ የፍልስፍና አስተሳሰብ ቋጥረዋል፡፡ በተለይ ለሀገራችን እንቆቅልሽ የሆነውን የብሄር ግጭትና ጦስ የጐሪጥ እያየ የሚተችባቸው ስንኞች ቀልብ ይስባሉ፡፡ የዛሬ የኔም ትኩረት ከዘመናችን ጋር ከንፈር ገጥሞ ከተሳሳመው የጐጥ ስላቅ ግጥሞች ላይ ነው፡፡ እንቆቅልህ… እንቆቅልሽ
ለጠየቅሽኝ እንቆቅልሽ፣ ሲጠፋብኝ እኔ
መልሱ
“ሀገር ስጠኝ” የምትዪኝ፣ መልስ
አታውቂም አንቺ ራሱ!
ሁሉ ሀገሩን ተከፋፍሎ፣ ክልሎችን
እያጠረ
ኬት አምጥቼ ሀገር ልስጥሽ ሀገር ማለት
ሰው ነበረ
ገድሎ መኖር ተበራክቶ፣ ሞቶ ማኖር
ከሀገር ጠፍቷል፡፡
መነሻው፤  ነባራዊው ዕውቀት - የሀገር ባህል ጨዋታ ነው፡፡ የ “እንቆቅልሽ” መልስ ሲጠፋ ሀገር ስጠኝ/ስጪኝ ይባላል፡፡ በላይ በቀለ ከዚህ ያንጠለጠለው መንጠቆ እዚያው አያበቃም፡፡ በውን ወደምንኖረው ሕይወት፣ ወደ ከረረው የብሔር ፖለቲካችን ደጅ ይመጣል፡፡ “ሀገር የሚባል ነገር ድሮ ቀረ! የሌለውን፣ ያበቃውን፣ የተረሳውን ነገር አትጠይቂኝ” እያለ ነው፡፡
ክልሎች እንጂ ሀገር የለም፡፡ ሀገር ማለት ሰው መሆኑን እናውቅ ነበር፤ አሁን ግን ሰው በዘር ተደራጅቶ ሀገር መሆን ተሳነው:: ጠበበ፤ ቀጨጨ፣ ከሳ! ወረደ! ዘቀጠ ነው የሚለው፡፡
ድሮማ ቢሆን ሰው ሞቶ ሀገር ይኖር ነበር፡፡ አሁን ግን ሌሎችን ገድሎ የመኖር ፈሊጥ ተጀምሯል ይላል፡፡ ይህ ግጥም የብዙዎቻችንን የልብ ቁስል የሚነካ ነው:: “ሰው” ያልነው ሁሉ ወደ ዘሩ ወርዶ፣ ጐስቁሏል…ባይ ነው፡፡ በላይ በቀለ ወያ በስሜቱ ቀዝቀዝ ብሎ በተረጋጉ ስንኞች አንዲት እንቆቅልሽ አጫዋች እንስት ገፀ ሰብ ጋ ነገር አለኝ የሚለው ግዙፍ ሃሳብ ይዞ ነው::
የግጥሙን መቋጫ ስንኞች ስንመለከት፣ የሚሰጠን ሃሳብ ትውልድን ከትውልድ ጋር እንድናነፃጽር ግድ የሚለን ይመስለኛል፡፡
ሰውም በዘር ተደራጅቶ፣ ሀገር መሆን
አቅቶታል
ገድሎ መኖር ተበራክቶ ሞቶ ማኖር
ከሀገር ጠፍቷል፡፡
የሀገራችንን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን፣ ዘመናይቱ ኢትዮጵያ ከተመሰረተች በኋላ እንኳ ስናይ፣ ነገስታቶቻችን ሳይቀሩ የሞቱት ለሀገር ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ዮሐንስና ሌሎቹም ነገስታት የሞቱት  ለሀገር ነው፡፡ ሌሎች በክብር እንዲኖሩ እነርሱ ሞተዋል፡፡
ዛሬ ግን ነገሩ የግሪምቢጥ ነው፡፡ ሰዎች ሌሎችን ገድለው ወይም አስገድለው ይኖራሉ እንጂ የቀደመውን ዓይነት መስዋዕትነት አይከፍሉም፡፡
ጐሰኝነት የጋርዮሽ ባህል አንዱ ገጽታ ቢሆንም፣ በቡድናዊነት ውስጥ፣ ብዙ ጊዜ ሰዎች ለቡድናቸው ይሞታሉ፡፡ በተለይ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካና እስያን የመሳሰሉት ሀገራት በዚህ  ይታወቃሉ፡፡ በላይ የሚላቸው ሰዎች ግን ቡድናቸውንም ለራሳቸው ጭዳ አድራጊዎች ናቸው፤ ክልል ክልል ካሉ በኋላ ወደ ዞንና ወረዳ፣ ከዚያም ወደ ጐጥ፣ ለጥቀውም ቆላና ደጋ ወደ ማለት ይወርዳሉ:: ስለዚህ እዚህ ሀገር ውስጥ ሀገር የለም፣ “ሀገር ስጠኝ” አትበዪኝ እያለ ነው፡፡
እንዲህ ያገርን - ቁስል፣ እንዲህ የወገንን እህህህ-ሰምቶ በዜማ ቀለም፤ በቃላት ዳንስ መልሶ ካላመጣ - ገጣሚ ምን ያደርጋል!...በተለይ ደግሞ ምሠላው ከፍ ቢል፣ ቃላቱ፣ የሰማይ ላንቃ ቢቧጥጡ ምንኛ ያስደምመን ነበር! ቢሆንም ወጣት ተስፋ አለው፤ ይጨምራል፣ ይቀጥላል! ኤስ ኤች በርተን የግጥም ኳሶች በሚል መጽሐፋቸው እንዳሉትና ሌሎችም እንደሚስማሙበት፤ ገጣሚው ማዕከላዊ ሃሳቡን ከግብ ለማድረስ የሄደባቸው ስልቶች፣ የተጠቀመባቸው ቃላት፣ ካላደናቀፉበት “ይበል” የሚያሰኝ ነው፡፡
ጥበብ፣ ከግርድፏ ዓለም ነቅሳ የምታመጣው መልክ፣ መራራውን በሳቅ እንድንቀበለው የሚያደርግ ነው፡፡
ገጣሚው፣ የጀመርኩትን ሃሳብ የሚያዳብርልኝ ሌላም ግጥም አለው - “እቴ ምን ሆነሻል?” ይላል፡፡
ሥራ በሌለበት
ሥለ ሥራ ቋንቋ፣ የሚነታረኩ
የትውልድ ልብ ላይ
ቂምን ለመጋገር፣ ጥላቻ ‘ሚያቦኩ
በነፃነት ምድር
“ነፃ አውጪ ነኝ” ብለው፣ ባርነት ‘
ሚሰብኩ
ትውልዶችን ፈጥሮ፣ ዝም ሲል ፈጣሪው
“ትናገር አደዋ!”
እያልሽ በድፍረት፣ ‘ምንታጐራጐሪው
ምን ነክቶሽ ነው እቴ!

ከኔ ቋንቋ በቀር፣ ለማይናገሩ
መግባባት አይኖርም፣ መስማማት
ኢንጅሩ
ገለመለ እያለ
ቋንቋ ተከፋፍሎ፣ ሲፎክር ሀገሩ
ሀገር መንደር ሲሆን፣ ውቅያኖሱ ኩሬ
አንቺ ባለማወቅ
“ትናገር አደዋ፣ ትናገር ሀገሬ”
ብለሽ የምትዘፍኚው
ወይ ደሞ በድፍረት፣ ‘ምታቀነቅኚው
ምን ነክቶሽ ነው እቴ!
ይህ ግጥም ከቀድሞው ጋር ሃሳቡ ቢመሳሰልም፣ የተለየ መንገድና ስልት ተጠቅሞበታል፡፡ እዚህ ግጥም ውስጥ ያለችውን ዘፋኝ እናውቃታለን፡፡ እሷን የሚያዋራትን ገፀ-ሰብ ደግሞ ገጣሚው ፈጥሮታል፡፡ የሚጠይቃት በመገረም ነው:: ቀደም ያለው ግጥም ላይ እርግጠኛ ሆኖ ሀገር የለም ሲል የነበረው አይነት ሰው፤ እዚህ ደግሞ “አንቺ ምን ሆነሻል? አንቺ ስለ ሀገር አድዋ ትናገር እያልሽ ስታወሪ፣ ስለ ቋንቋና ልዩነት የሚያወሩ፣ አንቺ ለውቅያኖሱ ስትዘፍኚ ኩሬ ጨልፈው፣ኩሬ ላይ የሚከራከሩ ባሉበት፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ብቻሽን እየጮህሽ ነው” የሚል ዐይነት ነው፡፡
በድሮ በሬ ያረሰ የለም፡፡ አሁን ስለ ብሔር ስለ ክልል እንጂ ስለ ሀገር አይወራም! ዘርሽን በድንጋይ ላይ አትበትኚ፤ “አድዋ” የምትያትን የጥቁር ሕዝቦች ጌጥ፣ የነፃነታቸውን አርማ ሰው ረስቶ ጀርባውን ሰጥቷል፡፡ አንቺ ግን ብቻሽን “ሀገሬ አድዋ ትናገር” ትያለሽ እያለ ይወቅሳል ይሳለቃል፡፡
ገጣሚው ያለንበትን ግራ መጋባት፣ የጠበብንበትን ልክ ሲያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሳይታክቱ፣ ለሚሰማውም ለማይሰማውም የማይቀለበሰውን ታሪክ፣ የማይታጠፈውን የታሪክ ቃል ኪዳን ከማወጅ ወደ ኋላ እንደማይሉ በውክልና የሚናገር ይመስላል፡፡ “አንቺ አትናገሪ፤ ዝም ብዪ የሚለው ገፀ-ሰብ፤ አቀንቃኝዋን የሚመክራት ነገር አለ፡፡ እንዲህ፡-
ለብዙ ሺህ ዘመን
እጇን ወደ አምላኳ
ዘርግታ ስትኖር፣ ሰርቀዋት ፀሎቷን
የቆጡን ለማውረድ፣ ጥላ የብብቷን
የፉክክር ሀገር
የሚዘጋት አጥታ፣ እያደረች ክፍቷን    
ሌባና ቀማኛ ለጉድ ተንሰራፍቶ
ፍቅር ያግባባቸው
ያያት ቅድመ አያቶች፣ ታሪክን አንስቶ
ቋንቋ ላያግባባን
እውነት እየሰቀልን፣ ለምንፈታ በርባን
“ትናገር አደዋ”
የሚል አጉል ቅኔ ከምትደረድሪ
አደዋ ዝም ብላ፣ አንቺ ተናገሪ፡፡
ገፀሰቡ አቀንቃኝዋን የሚመክራት አድዋ ብትጮህ የሚሰማት የለም፤ ስለዚህ አደዋ ትናገር አትበይ እያለ ነው:: “ነገራችን ዝብርቅርቅ ብሎ ክርስቶስን ሰቅለን ባርባንንን በምንፈታበት ሀገር፣
እውነትን የሚያደምጥ ታሪክን የሚቀበል የለም፡፡
አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እያለ ነው፡፡ ታሪክን መስማት፣ ታሪክን በቀጥታ መቀበል ቀርቷል፡፡ አዲስ ትርክት፣ አዲስ ወሬ፣ ካልሆነ የሚሰማሽ የለም፡፡ ስለዚህ አደዋን ተይና ራስሽ ተናገሪ!
አድዋ እውነት ናት፤ አድዋ ሁሉም በጋራ የሠራት ሀውልት ናት፡፡ ግን ደግሞ የጋራ የሆነ ነገር የማይፈልጉ፣ የክልል ንጉሥ መሆን ያማራቸው ጠባቦች አድዋ ደመኛቸው ናት፡፡ የሚንቀለቀለውን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ ፍም ማጥፋት ቢችሉና መቀልበስ ቢሆንላቸው ሌት ተቀን እንቅልፍ የሚያጡ ጠባቦች አሉ:: ስለዚህ ዘፈንሽ የገደል ማሚቶ፣ ጩኸትሽ የሞኝ ዘፈን ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ እያለ ነው የሚወተውተው ገጣሚው፡፡

Read 3451 times