Saturday, 04 July 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


                    “ራስን ሳይችሉ ነፃነትን ማሰብ ላም አለኝ በሰማይ ሆኖ ይቀራል”
                         

           ድሮ የሰማነው ጨዋታ ነው፡፡
“እኛ ሀገር” …አለ አንድ የተበሳጨ ህንዳዊ::
“በጄ”
“ድንች ብትተክል ድንች፣ ቲማቲም ብትዘራ ቲማቲም ታመርታለህ”
“ሌላስ ቦታ ቢሆን ያው አይደል” ተባለ።
“እናንተ ሀገር ሩዝ ዘርተህ ጤፍ ሊበቅል ይችላል”
“እንዴት ሆኖ" ተጠየቀ ህንዳዊው።
“ከሩቅ ጠላት የጉያ እሳት ያንገበግባል” እንደሚባለው ነበር፡፡…ለምን ይሆን? “ሩዝ ዘርተህ ጤፍ ሊበቀል ይችላል” ያለው? መጨረሻ ላይ እነግራችኋለሁ።
*   *   *
በልጅነት አእምሮ በፍቅር ካነበብናቸው መጽሐፍት አንዱ የማሪዮ ፑዞ “God Father”  አይረሳም፡፡ እዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የሆሊውድ ተዋናይ መሆን የፈለገ አንድ ገፀ ባህርይ አለ፡፡ ጆኒ ፎንታኔ የሚባል፡፡ ሆሊውድ ደግሞ በቀላሉ የሚገባበት ቦታ አልነበረም:: ጆኒ የወጣትነት ህልሙን እንዲፈቱለት ለክርስትና አባቱ ለዶን ኮሮሊዮኒ ነገራቸው - ረዥም እጅ ላላቸው የማፊያዎች አለቃ፡፡ እሳቸውም በሲኒማ ኢንዱስትሪው ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ለሆነው ባለፀጋ ፕሮዲዩሰር ደውለው፣ አበልጃቸው ወደ ተመኘው ጐዳና እንዲመራው “ይነግሩታል” ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ የሆነው ሰውዬ ማንነታቸውን አያውቅም፡፡ ሰምቶ እንዳልሰማ ይሆናል፡፡ ጆኒም ሰውዬው ችላ እንዳለው ኒውዮርክ ለሚኖሩት ክርስትና አባቱ ነገራቸው፡፡
ዶን ኮሮሊዩኔ ሰውየውን መልሰው አላናገሩም፡፡ ነገር ግን ሁሉን ነገር በፍጥነት አመቻችቶ ጆኒ የፈለገውን አገኘ፡፡ ምክንያቱም በዛ ሰሞን አንድ ምሽት ሰውየው ቤቱ ገብቶ ወደ መኝታው ክፍል ሲዘልቅ አልጋው ውስጥ ተጋድሞ የጠበቀው ከምንም ነገር በላይ የሚወደውና የሚሳሳለት፣ ውድ ንብረቱ የሆነውን ፈረስ አንገት ነበር፡፡ በዛ በተከበረ ግቢ፣ በተቆለፈ መኝታ ቤት እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ትርኢት ማየት ማለት “በሚቀጥለው የሚቆረጠው ያንተ አንገት ነው” ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ ደቂቃ አልፈጀበትም፡፡ አሁን የሰውየውን ማንነት አወቀ፡፡ ሐዘኑን ዋጥ አድርጐ የተባለውን ፈፀመ፡፡ ምርጫ አልነበረውም፡፡
ወዳጄ፡- ዕውቀት፣ ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ፍርክስክሱን ያወጣው የማፊያ ኔትወርክ፣ ህጋዊውን የመንግስትና የግል ተቋማት በቅጥረኞቹ በኩል እንደፈለገው የሚያሽከረክር “ሌላ” ድብቅ መንግስት መሆን ችሎ ነበር፡፡ ያኔ፡፡ “በውጦ ዝም” መርህ (cod of silence Omerta) የተጠፈረ የወንጀለኞች ድርጅት፣ ከመንግስት ባለስልጣናት እስከ መንደር “አስተኳሾች” እና ወሬ አቀባዮች የተዋቀረው ያ ረዥም ክንድ፣ ለፍትህ በቆሙ የህሊና ሰዎችና ህግ አስከባሪዎች ትግል ተቆራርጦ፣ ዛሬ የልብ ወለድ ድርሰቶች ማጣቀሻ ሆኗል፡፡
ወዳጄ፡- ድህነትና ራስን ያለመቻል ካለ ማወቅና ከኋላቀርነት ጋር ሲዳመር፣ ለጥቅምና ፕሮፓጋንዳ እጅ የሚያሰጡ ጥገኛ አስተሳሰቦች መዛመት ምክንያት ይሆናል፡፡ ጥገኛ አስተሳሰብ ደግሞ በፖለቲካ ንቅናቄ ሽፋን ለተለያዩ ወንጀሎች መራባት መንገድ ያመቻቻሉ፡፡ የተባበረው አሜሪካ መንግሥት፣ ማፊያ ያቆሸሸውን ማህበራዊ ስርዓት ጠራርጐ ያስወገደው፣ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ የፖለቲካ ማህበራት መሪዎች ሊዘውሯቸው በማይችሉ፣ በህግና ህግ ብቻ የሚተዳደሩ ነፃ የፍትህና የአስተዳደር ተቋማት በመገንባት ነው፡፡
ወዳጄ፡- ማናቸውም ዓይነት ማህበራዊ ችግሮች መነሻ ሰበብ አላቸው፡፡ ባርነትና የዘር መድልዖን ጨምሮ የብዙዎቹ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሐዊነት የፈጠራቸው ማህበራዊ ምስቅልቅና ጉስቁልና ሲሆን፤ ፍትሃዊ መዳረሻ ሊሆን የሚገባው ደግሞ በሁሉም መንገድ ራስን ችሎ የመገኘት (Self sufficient የመሆን) ብቃት ማዳበር ነው:: ራስን ሳይችሉ ነፃነትን ማሰብ “ላም አለኝ በሰማይ” ሆኖ ይቀራል፡፡
የሰው ልጅ እንደ ዕቃ መሸጥና መለወጥ ቢቀርበትም አስተሳሰቡ ግን እንደ ማፊያዊው ስርዓት ሙሉ በሙሉ ተጠራርጐ አልተወገደም፡፡ አጉል አስተሳሰብ እንደ ድርጊት በህግና በአዋጅ ብቻ የሚገታ አይደለም፡፡ ስር የያዘ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ይጠይቃል፡፡
የጆርጅ ፍሎይድን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ወንጀሉን የፈፀመው ፖሊስ ጥቁር ቢሆን ኖሮ ጉዳዩ ህግን ከማክበርና ካለማክበር ጋር ብቻ የተያያዘ፣ የአንድ ህገወጥ ፖሊስና የአንድ ጥፋተኛ ዜጋ ታሪክ ሆኖ ይመዘገብ ነበር፡፡ ነገር ግን “ዘረኝነት አለ” የሚል አስተሳሰብ ከዜጐች አእምሮ ውስጥ ነቅሎ ባለመውጣቱ አጋጣሚውን አስከፊ አድርጐታል፡፡
ወዳጄ፡- የባርነትን ጉዳይ ካነሳን አይቀር፣ አሲምባ ተራራ በሚገኝበት የኢሮብ አካባቢ የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ የሆነውን ጉዳይ “ከደምቢያ እስከ ዋሽንግተን ዲሲ” እና “ኢህአሶ” የተባሉ መጽሐፍትን ያዘጋጀው ወዳጄ አስማማው ሃይሉ (አያ ሻረው)፤ በሸገር ሬዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ያጋጠመውን ነገር ምስክር ሆኖ አጋርቶናል፡-
ሰውየው በአካባቢው የታወቁ የአገር ሽማግሌ ናቸው፤ የቀድሞ ባላንባራስ:: ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ሌላ ቦታ ስለሄዱ እሳቸው የሚኖሩት ለረዥም ዘመን ሲያገለግላቸው ከነበረ “ባሪያቸው” ጋር ነበር፡፡ ይህን የሰማው አስማማውና ጓደኞቹ ባላንባራስን፡-
“በዚህ ዘመን ሰውን በባርነት መግዛት ተገቢ አይደለም፤ ይህን አገልጋይዎን ነፃ ይልቀቁት” ይሏቸዋል፡፡ ባላምባራስም ደንግጠው፡-
“ኧረ ይሂድ፣ ቤትም እሰራለታለሁ፣ ከብቶችም ይውሰድ” ይሏቸዋል፡፡ ታጋዮቹም ባላምባራስን አመስግነው እንደተሰናበቱ ሰውየውን ፈልገው “ነፃነት” የተጐናፀፈበትን “የምስራች” ሲነግሩት ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ፡፡
“‘እንዴት እንዲህ ትሉኛላችሁ?’ ሲለን እኛም ደነገጥን” ይላል አስማማው።
“ምነው" ሲባል
“ስንት ዘመን አብሬአቸው ኖሬ አሁን ዕድሜአቸው በገፋበት፣ ጉልበታቸው በደከመበት ሰዓት እንዴት ጥዬአቸው እሄዳለሁ " እግዜርስ ምን ይለኛል፤ ፍፁም አላደርገውም’ ብሎ ነበር የመለሰን” በማለት አጫውቶናል፡፡ ሰዎቹ’ኮ አንተ ትብስ አንተ የሚባባሉ ወንድማማቾች ሆነዋል፡፡ እንደ ስካርለትና እንደ ማሚዋ!
ወዳጄ፡- የአስተሳሰብ ነፃነት በየአንዳንዱ ግለሰብ ነፃ ምርጫና ፍላጐት የሚወሰን አእምሯዊ ጉዳይ ነው፡፡ አካላዊ ባርነት ተረት በሆነበት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን “እንደኔ ካላሰብክ” ብሎ የዜጐችን አስተሳሰብ መጫን፣ የሃሳብ ባሪያ ፈንጋዮችና የፀረ - ዴሞክራቶች መገለጫ ነው፡፡
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሰውዬአችን “እዚህ አገር ሩዝ ዘርተህ ጤፍ ይበቅላል” በማለት የተበሳጨው ባለቤቱ የወለደችው ህፃን እሱ እየረዳ የሚያስተምረውን ጐረምሳ እንደሚመስል ተመልክቶ ነበር፡፡ ወዳጄ የአስተሳሰብ ዲቃላ ደግሞ የበለጠ የሚያበሳጭ አይመስልህም?
በጉያችን ካሉ እጅ ነካሾች ይሰውረን!
ሠላም!!


Read 1101 times