Saturday, 11 July 2020 00:00

12 የፖለቲካ አመራሮች ታስረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በሰሞኑ ሁከትና ግርግር የተጠረጠሩ ናቸው ተብሏል

          የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከትና ግርግር ጋር ተያይዞ 12 የሚደርሱ የተፎካካሪ  ፓርቲ አመራሮች መታሰራቸው ታውቋል፡፡
በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ለሰዎች ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ናችሁ እንዲሁም የሁከቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ናችሁ ተብለው የተጠረጠሩ የአራት ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት እንደታሰሩ ተጠቁሟል፡፡  የኦሮሞ ፌዴራሊስት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዲሁም ከወራት በፊት ፓርቲውን በአባልነት የተቀላቀለው አቶ ጃዋር መሐመድ በከፍተኛ አመራር ደረጃ እንደታሰሩ ለአዲስ አድማስ የገለጹት የፓርቲው ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ሌሎች ፓርቲው ገና ማጣራት እያደረገባቸው ያሉ በርካታ አባሎቹም በኦሮሚያ መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢህን) ሊቀ መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና የፓርቲው የምክር ቤት አባል አቶ ወንዳለ አስናቀው መታሰራቸውንም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰሞኑን ፍ/ቤት ከቀረቡ በኋላ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸው ለሐምሌ 11 የተቀጠረ ሲሆን መኖሪያ ቤታቸው ተፈትሾ የፓርቲያቸው ማህተምና ሌሎች ሰነዶች መወሰዳቸውን ጠበቃቸው አቶ አዲሱ ጌታነህ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሦስት ከፍተኛ አመራሮች መታሰራቸውን የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ሰሞኑን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ወጣቶች ወደ ሁከትና ግርግር እንዲገቡ ቀስቅሰዋል በሚል የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ሊቀ መንበር አቶ እስክንድር ነጋና የህዝብ ግንኙነት ተጠሪው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ቀደም ብለው መታሰራቸው የሚታወቅ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ የፓርቲው አባላት ከሰሞኑ እንደታሰሩ ተነግሯል፡፡

Read 284 times