Saturday, 11 July 2020 00:00

የፖለቲካ ልሂቃን የአመፃ መንገድን እንዲያወግዙ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

       የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ምሁራንና ሚዲያ ላይ የሚሰሩ አገርን ወደ ለየለት ትርምስና ብጥብጥ የሚከት የአመፅ ጥሪ ከማቅረብ እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከሰሞኑ የተከሰተው ሁከትና ግርግር ያስከተለውን ጥፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከዚህ በኋላ ሀገርን ወደ ለየለት ትርምስና ብጥብጥ  የሚከት የአመፅ ጥሪ ከማቅረብም ሆነ በአመፅ ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ጥሪ አድርገዋል፡፡
የፖለቲካ ልዩነትን በአመፅ ለመፍታት የሚደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ሀገሪቱን ለተደጋጋሚ ምስቅልቅል እየዳረገ መሆኑን ያስገነዘቡት ኮሚሽነሩ፤ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ  ማንኛውንም የፖለቲካ አስተሳሰብ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ማራመድ የሚቻልበት እድል የተፈጠረ በመሆኑ ከአመፃ መንገድ መቆጠብ ይገባል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመፃ መንገዶችን መጠቀም ማቆም ብቻ ሳይሆን ይሄን መንገድ የሚጠቀሙትንም በአንድ ድምጽ ማውገዝ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ዶ/ር ዳንኤል፤ ልዩነትን በውይይት የመፍታት ባህልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም  መክረዋል፡፡

Read 649 times