Saturday, 11 July 2020 00:00

በሻሸመኔ ከተፈጸመው ግድያና ውድመት ጋር በተያያዘ የከተማው ከንቲባና የፀጥታ ሃላፊው ታስረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   •  በተፈጠረው ሁከትና ግርግር 229  ሰዎች ተገድለዋል
         •  ሻሸመኔ 50 ዓመት ወደ ኋላ ተመልሳለች - ነዋሪዎች
         •  ከ4ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል ተብሏል

              በሰሞኑ ሁከትና ግርግር ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት የደረሰባት የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ ተማም ሁሴንና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ናደው አምቦ የታሰሩ ሲሆን በአጠቃላይ ከሁከቱ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ከተሞች  ከ4 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች ተይዘው መታሰራቸው ታውቋል፡፡ በተፈጠረው ሁከትና ግርግርም 229 ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ  ጠቁሟል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት ከፍተኛ የሰዎች ጉዳትና የንብረት ውድመት ከደረሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ በንግድ መናኸሪያነቷ የምትታወቀው ሻሸመኔ፣ ዝዋይና አርሲ ነገሌ ዋነኞቹ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡  
የሻሸመኔ ከተማን እንዳልነበረች ያደረገ ከፍተኛ ውድመት መፈጸሙን የሚገልፁት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በመንገድ ዳርና ዳር የሚገኙ በርካታ የንግድ መደብሮች መዘረፋቸውንና መቃጠላቸውን ተናግረዋል:: ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መዘረፋቸውን፣ ከፊሎቹም በእሳት መውደማቸውን ገልጸዋል፤ነዋሪዎቹ::  
በዝዋይ (ባቱ) ከተማም በተመሳሳይ በርካታ የንግድ መደብሮች፣ ሬስቶራንቶችና የሃይሌ ገ/ስላሴ ሪዞርትን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ ሆቴሎች የዘረፋና የቃጠሎ ሰለባ እንደሆኑ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በሻሸመኔ ከተማ ከዚህ በፊትም አጋጣሚን እየጠበቁ ሁከትና ግርግር በመፍጠር ንብረት ማውደም የተለመደ ነበር ያሉት ነዋሪዎች፤ ሰሞኑን የተፈፀመው ውድመት ግን ከተማዋን በ50 አመት ወደ ኋላ የመለሰ ነው ብለዋል፡፡
በሻሸመኔ የደረሰውን የሰዎች ህይወት መጥፋትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከትሎም፣ የከተማዋ ከንቲባና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊው የታሰሩ ሲሆን በድርጊቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም መታሰራቸው  ታውቋል፡፡

Read 947 times