Saturday, 11 July 2020 00:00

የአርቲስት ሃጫሉ ገዳዮች ተያዙ - አቃቤ ሕግ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 •  ግድያውን ያስፈፀመው “ኦነግ ሸኔ” ነው ተብሏል
  •  ሦስተኛው ተጠርጣሪ በፖሊስ እየታደነ ነው
  •  "ከዚህ በኋላ ብጥብጥና አመፅ ማካሄድ የማይሞከር ነው"


           የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሶስት ተጠርጣሪ ገዳዮች ተለይተው የታወቁ ሲሆን ሁለቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሶስተኛው በፖሊስ እየታደነ ነው፤ ግድያውን ያስፈጸመውም “የኦነግ ሸኔ” ቡድን ነው ተብሏል፡፡
አርቲስቱን በመግደል ወንጀል ተጠርጥረው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለምርመራ ቡድን የሰጡት አብዲ አለማየሁና ጥላሁን ያሚ የተባሉት ሁለቱ በቁጥጥር  ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች፤ ድርጊቱን መፈጸማቸውን በዝርዝር ማስረዳታቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል:: አርቲስቱን በቀጥታ ተኩሶ የገደለው ጥላሁን ያሚ የተባለው ተጠርጣሪ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
አርቲስቱን በቀጥታ ተኩሶ በመግደል የተጠረጠረው ጥላሁን ያሚ፤ ተልእኮውን የሰጡት ሰዎች በሰኔ ወር ለሦስት ጊዜ ሲያነጋግሩት በኦሮሚኛ ቢሆንም እርስ በእርሳቸው ግን በትግርኛ ቋንቋ ይነጋገሩ እንደነበር ማስረዳቱን ከአቃቤ ህግ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡    
“የኦሮሞ ህዝብ እንዲያልፍለት ለአንተም ለቤተሰቦችህም እንዲያልፍላቸውና አሁን ያለው መንግስት የተዳከመ ስለሆነ አጋጣሚውን ለመጠቀም የምትገድላቸው ሰዎች አሉ” ተብሎ ማንነታቸውና የመኪናቸው ታርጋ ቁጥር እንደተሰጠውም ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ተናግሯል፡፡
ከሶስቱ ተጠርጣሪዎች አንደኛው፤ ከበደ ገመቹ፣ ለጊዜው መሰወሩንና ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርግ አቃቤ ህግ ጠይቋል፡፡ የፌደራል መንግስቱ የመዳከም ምልክት እየታየበት ነውና ኦሮሚያን መታደግ በሚል ሽፋን፤ ኦነግ ሸኔ ለገዳዮቹ ተልዕኮ መስጠቱም በአቃቤ ህግ መግለጫ ተመላክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ አመፅና ብጥብጦች እንዲፈጠሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዳው መግለጫው፤ መንግስት ከአሁን በኋላ ማንኛውም የአመፅና ብጥብጥ እንቅስቃሴን በትዕግስት እንደማይመለከት አስጠንቅቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ብጥብጥና አመፅ  በሃገሪቱ ማካሄድ የማይሞከር ነው ያለው መግለጫው፤ ህብረተሰቡም ልጆቹን ከአመፅ ተሳታፊነት ሊጠብቅ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡
የህግ ማስከበር ጉዳይ ከዚህ በኋላ በቸልታ እንደማይታይና መንግስት ሃገሪቱን ከጥፋትና ከሁከት የመታደግ ተግባሩን ከምንጊዜውም የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከዚህ በኋላ ወንጀለኞችን እንደማይታገስ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስጠንቅቋል፡፡  

Read 862 times