Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የሰው ልጅ ቁጥር ሆነ!
የመጀመሪያዋ ሴትዮ በኮቪድ ሲሞቱ ለሁላችንም ሰው ነበሩ፡፡ እናት ነበሩ:: ለሁላችንም ሃዘን ነበሩ፡፡ ለሁላችንም ድንጋጤ ነበሩ፡፡
ከሁለተኛው ሰው በኋላ ግን፣ ሰው ቁጥር ሆነ፡፡
ስንት ሰው ሞተ? ብለን እንጠይቅና ፣ ወደ ዕለት ጉዳያችን እንሄዳለን፡፡ የሞተው ሰው ቁጥር ሲነገረን እንሰማና፣ ወደ ጉዳያችን እንገባለን፡፡ ያ ቁጥር ነገ እኛ ልንሆን እንደምንችል ማሰብ ከተውን ቆየን፡፡
ስድስት ሰው ሞተ… አስር ሰው ሞተ… አስራ… ይቀጥላል፡፡ ባለአንድ፣ ባለሁለት፣ ባለሶስት፣ ባለአራት ዲጂት እስኪደርስ ድረስ ሰው ቁጥር ሆኗል፡፡
ወደፊት ቁጥሮች ከፍ ይላሉ፡፡ እያንዳንዳችን ቤት እስኪደርሱ ድረስ ሰዎች ቁጥር መሆናቸው ይቀጥላል፡፡
ቤታችን ሲገባ ግን፣ አንድ ቁጥር ሺህ ነው፤ ከሺህም በላይ ነው፤ ከሚሊዮንም በላይ ነው…  ያ ቁጥር አባት ነው፤ እናት ናት፤ ወንድም ነው፤ ሚስት ናት፤ ባል ነው፤ ሚስት ናት፤ ልጅ ነው፤ ዘመድ አዝማድ ነው:: ያ ስም ሌላው ሰው ጋ ሲሄድ ቁጥር ነው፤ እኛ ጋ ግን ከስጋችን ቦጭቆ የሚወጣ… ትልቅ ቁስል የሚሆን ህመም ነው፡፡
አስበነው እናውቅ ይሆን?
ከቁጥር አንጉደል!
ቁጥር እንዳንሆን እንጠንቀቅ!
እንጠበቅ!
እንጠብቅ!
(ከመላኩ ብርሃኑ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ)
*   *   *
እንዴት ዝም ልበል?!
(የአንድ አጥፊ ኑዛዜ)
ፍቅር በሚሉት ቃል
የጨለፍኩላችሁ፣ መርዜን ስታረክሱት
ሳቆመው የባጀሁ
የዘር ድንበር ኬላ፣ አጥሬን ስታፈርሱት
የተንኮል ጎጆዬን
ወጋግራ ነቅላችሁ፣ ስታደርጉት ዘመም
እያየሁ ልታመም?...
ትተራረዱበት
የሳልኩት ቢላዋ፣ በእጃችሁ ሲመከት
በዋይታችሁ ፋንታ
ጆሮዬን ስትነድሉት፣ በፍቅር መለከት
ዝም ብዬ ልመልከት?...

ዘመናት ፈጅቶብኝ
የተከልኩትን ቂም፣ ነቅላችሁ ስትጥሉት
የጥላቻ እሾሄን
ከየጀርባችሁ ላይ፣ በድንገት ስትነቅሉት
የማናከስ ልክፍት
ስንት የደከምኩበት፣ ከንቱ ሲቀር ህልሜ
ልያችሁ ዳር ቆሜ?...

የቂሜን ጥቅርሻ
ይቅርታ በሚሉት፣ እንዶድ ስታጸዱት
የዘር ስናጾሬን
በአንድ የፍቅር ቋንቋ፣ ከስሩ ስትንዱት
ዘመናት ያለፈ
የጥፋት ድግሴን፣ የደም ጽዋ ጸበል
ድንገት ባደባባይ
ባንድነት ሱባኤ፣ ስታደርጉት ከንበል
እንዴት ዝም ልበል!?...
(ገጣሚ - ፊያሜታ)


Read 1123 times
Administrator

Latest from Administrator