Print this page
Saturday, 18 July 2020 15:33

63 ዓመታትን ያስቆጠረው ታሪካዊው የጎባ ከተማ ሆቴል ሙሉ በሙሉ ወደመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ከፊል ንብረቱ ተዘርፎ፤ የተቀረው በእሳት ወድሟል
                          
           የባሌ አርማ በመባል የሚታወቀውና ለጎባ ከተማ የመጀመሪያ የሆነው ይልማ አምሳ ሆቴል፤ ሰሞኑን በተፈጠረው ሁከትና ግርግር እንደተዘረፈና በእሳት ቃጠሎ  እንደወደመ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሆቴሉ የወደመዉ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተነሳ ረብሻና ግርግር እንደሆነ የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ይልማ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
በ1950 ዓ.ም በስራ ፈጣሪው አቶ ይልማ አምሳ ተመስርቶ፣ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጎባ ከተማ የመጀመሪያውን የሆቴል አገልግሎት ያስተዋወቀው ይህ አንጋፋ ሆቴል፤ ሰኔ 23 ለነውጥ በተሰማሩ ወጣቶች በደረሰበት ቃጠሎ ከ62 አመት የአገልግሎት ዘመን በኋላ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ተጠቁሟል፡፡ ይልማ አምሳ ሆቴል በባሌ ጎባ ከተማ በርካታ ነገሮችን በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ እንደነበር የገለጹት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ፤ በአካባቢው መብራት ባልነበረበት ዘመን ጄኔሬተር በመትከል፣ ለስላሳ መጠጦችንና ጋዜጦችን ለአካባቢው ያስተዋወቀ ሲሆን የመጀመሪያውን የውበት ሳሎን በመክፈት የአካባቢው ፈርጥ ሲባል የኖረ ቅርስ ነበር ብለዋል፤ አቶ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ፡፡ ሆቴሉ በዓለም ዙሪያ በተሰራጩና የኢትዮጵያ መዳረሻን በሚገልጹ ቀደምት የቱሪስት ጋይዶች ላይ  ስሙ ሰፍሯል ተብሏል፡፡  
ከ25 አመታት አገልግሎት በኋላ በ1977 ዓ.ም ዳግም በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው አምሳ ሆቴል፤ በእሳት ቃጠሎ የወደመ ሲሆን በአጠቃላይ  10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት መድረሱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ይሄን ተከትሎም  ከ33 በላይ ቋሚ ሰራተኞችን ለመበተን መገደዱን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሀገር ቅርስ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስበት እንደቆየ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ በዚህ ቃጠሎ የሆቴሉ ልዩ ልዩ መገልገያ ክፍሎች ማለትም፣ ባርና ሬስቶራንት፣ኬክ ቤት፣መናፈሻና መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን በሆቴሉ ካዝና ውስጥ የነበረውን ገንዘብ ጨምሮ ልዩ ልዩ ሰነዶች፣ ዘመናትን ያስቆጠሩ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሰራተኞች አልባሳትና መገልገያዎች ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡  የተቀረው ደግሞ ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲወድም ተደርጓል ብለዋል፡፡  ለባሌ ጎባ እድገትና ስልጣኔ ከስድስት አስርት አመታት በላይ ለፍተው አገር ያቀኑት የሆቴሉ መስራችና ባለቤት አቶ ይልማ አሞሳ፣ ይህን ቅርስ ለትውልድ ትተው ከጥቂት አመታት በፊት ያለፉ ሲሆን በህይወት ሳሉ ለጎባ ከተማ እድገትም ሆነ በባሌ ዞን በሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ሆቴሉን ተረክበው ሲያስተዳድሩ የነበሩትም የአቶ ይልማን ቃል በመጠበቅ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ለአካባቢው ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን፣ ለዚህም በጎ ተግባራቸው የተለያዩ የእውቅና ሽልማቶች እንደተበረከቱላቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሆቴሉ ውድመት በእጅጉ ያዘኑ የአካባቢው ነዋሪዎችና በውጪ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ሆቴሉን በማስተዳደር ላይ ለሚገኙት ቤተሰቦች እያጽናኑ  እንደሚገኙ የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል። ምንም እንኳን ከጥቃቱ በፊትም ሆነ ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት በከተማው የጸጥታ አካላት የነበሩ ቢሆንም፣ ከለላ ለመስጠት ባለመቻላቸው ግን  ሆቴሉ ለታሪክ አንዳይቀር ሆኖ መውደሙን ስራ አስኪያጁ በሃዘን ገልጸዋል፡፡ ለአገር አሳፋሪ የሆነና በታሪክ ፊት ተወቃሽ የሚያደርግ እንዲህ ያለ ጥፋትና ውድመት፤ ዜጎች በየአገሩ ተንቀሳቅሰው ሥራ ለመፍጠር በሚያደርጉት ጥረት ላይ ጥቁር ጠባሳ እንዳይተው መንግስት በትኩረት መሥራት ይገባዋል ብለዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡

Read 1225 times