Print this page
Saturday, 18 July 2020 15:35

በኢትዮጵያ ከኮሮና የበለጠ ረሃብ የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ ይችላል - ኦክስፋም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

   • 10 የዓለም አገራት በኮሮና ሳቢያ ለከፋ ረሃብ ይጋለጣሉ
         • መንግስታት የረሃብ አደጋን ለመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃን መውሰድ አለባቸው
                  
          የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ሣቢያ በዓለማችን የከፋ ረሃብ እንደሚከሰት የጠቆመው ኦክስፋም፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 10 አገራት በከፋ ረሃብ ምክንያት ለአደጋ እንደሚጋለጡ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ የሚከሰተው ረሃብ ከዚህ ቀደሞቹ የከፋ ነው ብሏል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አስር አገራት ውስጥ በወረርሽኙ ከሚሞቱ ሰዎች በላቀ መጠን በርካቶች በረሃብ ሳቢያ ለህልፈት ሊዳረጉ ይችላሉ ተብሏል፡፡
እንደ ኦክስፋም መግለጫ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወትሮውንም በረሃብ እየተሰቃየ ያለውን በርካታ የአለማችንን ህዝብ ለከፋ ረሃብ እያጋለጠው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት 10 የዓለማችን አገራት እጅግ ለከፋ ረሃብ እንደሚጋለጡ ያመለከተው ድርጅቱ፤ ከእነዚህ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ ናት ብሏል፡፡ ከወረርሽኙ በበለጠ በረሃብ ሳቢያ በርካታ ዜጎቻቸውን ያጣሉ የተባሉ ሌሎች አገራት ደግሞ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዌላ፣ ምዕራብ ሳዕልና ሄይቲ ናቸው፡፡
አንደ ኦክስፋም መግለጫ፤ በዓለማችን ቀደም ሲል ለረሃብ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ሲሆን ወረርሽኙ ረሃብ ተከስቶባቸው በማያውቁ አዳዲስ አካባቢዎችንም እየፈጠረ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ከወራት በኋላ በዓለማችን በየቀኑ ከ6ሺ እስከ 12ሺ የሚደርሱ ሰዎች በኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ ሳቢያ በሚከሰት ረሃብ ለሞት ሊዳረጉ አንደሚችሉ አመልክቷል - ድርጅቱ፡፡  ይህ አሃዝም የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ዙርያ ከሚገድላቸው ሰዎች ቁጥር በእጅጉ የሚልቅ ነው ተብሏል፡፡
ስራ አጥነት፣ በእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ፣ ምግብ አምራቾች መስራት አለመቻላቸውና እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እርዳታ ለማከፋፈል አመቺ ሁኔታዎች አለመኖራቸው የሚከሰተውን ረሃብ እንደሚያባብሰውና የሚያስከትለውን ጉዳትም የከፋ እንደሚያደርገው ሪፖርቱ አመላክቷል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ እየጨመረ የመጣውን የረሃብ ችግር አባባሽ ምክንያት ሆኖል ብሏል - የድርጅቱ መግለጫ፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት በአለም ዙርያ 821 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትና ችግር የገጠማቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በከባድ ወይም በከፋ ረሃብ ሳቢያ ለስቃይ የተዳረጉት 149 ሚሊዮን እንደነበሩ ይጠቁማል - መግለጫው። መንግስታት የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋትን ለመግታት ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የተጋረጠውን የረሃብ አደጋ ለመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም ነው ኦክስፋም ያሳሰበው፡፡        


Read 684 times