Saturday, 18 July 2020 15:36

ፖሊስ በአቶ ጀዋር መኖሪያ ቤት የተገኘውን የሳተላይት መቀበያ ለማስመርመር ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደለት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

    “የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን የመለስነው መንገድ ስለተዘጋ ነው ከአስከሬን ሽኝቱ ጋርበተያያዘ የተተኮሰ ጥይትም ሆነ የሞተ ሰው የለም”
                             - አቶ ጃዋር መሐመድ

                 የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ሁከትና ግርግር እንዲፈጠር በዚህም የሰው ህይወት እንዲያልፍና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል በሚል ተጠረጠሩት ፖለቲከኞቹ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ እስክንድር ነጋ እና ግብረአበሮች ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
የፖሊስ የምርመራ ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ባለፉት ቀናት ያደረጋቸውን ምርመራዎችና ያሰባሰባቸውን ማስረጃዎች በዝርዝር ጉዳዩን ለሚመለከቱት ለልደታ እና አራዳ ምድብ ችሎት ያቀረበ ሲሆን  የማከናወናቸው ተጨማሪ ምርመራዎች አሉኝ በማለትም በእያንዳንዳቸው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡
የፖሊስ የምርመራ ቡድን በአቶ ጀዋር መሐመድ እና ግብረአበሮቻቸው ላይ የ30 ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ለፍ/ቤቱ አስረድቷል::
የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ በአቶ ጀዋር አማካይነት በኦኤም ኤን የተላለፈውን የአመጽ ጥሪ መልዕክት ማስረጃን ከብሮድካስት ባለስልጣን ማግኘቱን፤ የአርቲስት ሃጫሉን አስከሬን ከቡራዩ ከተማ በመቀማት ወደኋላ መመለሱን ይህን ለማድረግም በከተማው ፀጥታ ሃይሎች ላይ ተኩስ መክፈቱን በተመለከተ የምክክሮች ቃል መቀበሉን አመልክቷል፡፡
አስከሬኑን ይዞ በመመለስም ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ያመራው በአቶ ጀዋር የሚመራው ቡድን በጽ/ቤቱ ውስጥ ተኩስ በመክፈቱ የአንድ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባል ህይወቱ ማለፉንና ሌሎች ሶስት መቁሰላቸውን  በተመለከተ የሰው ምስክር እና የፎረንሲስ ሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡንም የምርመራ ቡድኑ አመልክቷል፡፡
ከአንደኛ ተጠርጣሪው አቶ ጀዋር እና ግብረ አበሮቻቸው ላይ 10 ሽጉጥ፣ አንድ ቺቺ መሣሪያ እና 10 ክላሽ፣ 9 የሬዲዮ መገናኛ በሚመለከተው አካል ህጋዊ አለመሆናቸው እንዲረጋገጥ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
ተጠርጣሪው ያስተላለፋቸውን መልዕክቶች ተከትሎ በአዲስ አበባ የ14 ሰዎች በኦሮሚያ ክልል 167 ሰዎች ህይወት ማለፉን እንዲሁም በአዲስ አበባ ከ2 መቶ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙንና የኦሮሚያ ንብረት ውድመት አሃዝ ተሰልቶ እስኪቀርብ እየተጠበቀ መሆኑን የምርመራ ቡድኑ ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡
በቀጣይም በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት የተገኘውን የሳተላይት መቀበያ ጨምሮ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን በባለሙያ ማስመርመር፣ ተጠርጣሪው ከኦኤም ኤን ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠ ር ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር በቀጥታ ያለውን ግንኙነት ለመመርመር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል - የፖሊስ የምርመራ ቡድኑ::
ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተሰማነው የምርመራ ቡድን የሚያመጣውን ውጤት መጠባበቅ፣ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም የምርመራ ቡድኑ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው ጀዋር መሐመድ በበኩሉ ለችሎቱ “የተተኮሰም ጥይት ሆነ የሞተ የለም፣ የአርቲስቱን አስከሬን ወደ አምቦ ለመውሰድ መንገድ ስለተዘጋጋ ወደኋላ ተመለስን እንጂ ሌላ ተልዕኮ አልነበረንም ጉዳዩ ፖለቲካዊ ነው ችግሩ የሚፈታው በፖለቲካ ውይይት ነው ሲል መናገሩን የኢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ጠበቆችም ከደንበኛቸው የእስር ሁኔታ አለመመቸት ጋር በተያያዘ እንዲሁም ቤተሰቦች እየጠየቋቸው አይደለም፣ ከፍርድ ውጪም የደንበኛችን ስም ያለ አግባብ እየጠፋ ነው የሚሉ አቤቱታዎችን አቅርበዋል።
የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ ተጠርጣሪው ያረፈበት ቦታ ንጽህናው የተጠበቀ መሆኑን፣ ተጠርጣሪዎች ከሰዎች ጋር እንዳይገናኙ የተደረገውም በኮሮና ምክንያት መሆኑን፣ በፖለቲካ አመለካከቱ ሳይሆን ወንጀል ስለመፈፀሙ ማስረጃ በመገኘቱ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ ለችሎቱ አስረድቷል።
ችሎቱ የግራ ቀኙን አስተያየት ካዳመጠ በኋላም የተጠርጣሪው ከጠበቆቹና ቤተሰብ ጋር መገናኘት እንዲችል ይደረግ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስ የጠየቀውንም 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ጉዳዩ ለሐምሌ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ተቀጥሯል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም የዋለው ችሎት የእነ አቶ በቀለ ገርባ እና እስክንድር ነጋ ጉዳይንም ተመልክቷል።
በእለቱም በአቶ እስክንድር ነጋ ላይ ፖሊስ ያከናወነውን የምርመራ ውጤት አቅርቦ ቀሪ ያላቸውን ተግባራት ለማከናወንም ተጨማሪ 14 ቀን ጠይቋል።
አቶ እስክንድር ነጋ “አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ ይጠናቀቃል” በሚል ሃሳብ በአዲስ አበባ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል፤
ለወጣቶች ገንዘብ እና መሣሪያ በማከፋፈል፤ በሃሰተኛ ወሬ ህዝብን በማሸበር ሁከትና ብጥብጥ እንዲከሰት አድርገዋል፣ በዚህም የ14 ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል በሚል መጠርጠራቸውን ፖሊስ አመልክቷል።
የምርመራ ቡድኑ ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ ከጠየቀው 14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ውስጥ 13 ተፈቅዶለት መዝገቡ ለሐምሌ 21 ቀን 2012 ተቀጥሯል።
በተመሳሳይ በአራዳ ምድብ ችሎት በቀረቡት አቶ በቀለ ገርባ ላይም ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ በፖሊስ ተጠይቆ ፍ/ቤቱ 11 ቀናትን ፈቅዷል፤ የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለሐምሌ ለ20 ቀን 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Read 12145 times