Saturday, 18 July 2020 15:42

የኢንተርኔት መዘጋት ሃገሪቱን በቀን ከ4 ሚ. ዶላር በላይ ገቢ እያሳጣት ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  በኢትዮጵያ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው ሁከትና ግርግር ሳቢያ የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋቱ በየቀኑ ሃገሪቱን ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያሳጣት መሆኑን ያስታወቀው ዓለማቀፉ የኢንተርኔት ክትትል ቡድን ‹‹ኔት ብሎክ››፤                ዜጎች ስለ አንገብጋቢው የኮሮና  ወረርሺኝ ተገቢውን መረጃ እንዳያገኙም ገድቧቸዋል ብሏል - ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት፡፡
መንግስት ከሁለት ሳምንታት የኢንተርኔት መዘጋት በኋላ በያዝነው ሳምንት  አገልግሎቱን እንደለቀቀ የጠቆመው  ሪፖርቱ፤ የተጀመረው የኢንተርኔት አገልግሎት ግን ከቀድሞው አንጻር የ1 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለውና አነስተኛ ቁጥር ያለውን ዜጋ ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብሏል፡፡
በመላ ሀገሪቱ የኢንተርኔት መቋረጥ በየቀኑ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ከማሳጣቱም  በተጨማሪ ዜጎች ስለ ወቅታዊው  የኮሮና ወረርሺኝ  መረጃ እንዳያገኙ ማድረጉንና የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት መገደቡን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ኢንተርኔት ተቋርጦ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ አለመታወቁ ዳግም ጉዳዩን የበለጠ አጠያያቂ ያደርገዋል ያለው ሪፖርቱ፤ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አህጉር አቀፍና  ዓለማቀፍ ተቋማትም የሃገር ውስጥ መረጃ ልውውጦችን ለማከናወን መቸገራቸውን አትቷል ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ልዩ ፀሃፊ ዴቪድ ካያ በበኩላቸው፤ መንግስት ኢንተርኔት መዝጋቱ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን ገልፀው፤ እርምጃው የሀገሪቱን የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ለማጥበብ የሚደረግ ጥረት አካል ነው ሲሉ መተቸታቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች  ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ መንግስት የዜጎችን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብት መገደቡ ተቀባይነት የለውም ብሏል::
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የኢንተርኔት መዘጋት ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽን መረጃን ከመገደብ ጋር እንደማይገናኝ በመጠቆም፤ እርምጃው በሃገር ደህንነት ላይ የተጋጠን አደጋ ከመከላከል ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቋል ማንኛውም አገር መሰል የአገር ደህንነት ስጋት ሲገጥመው የሚወስደው እርምጃ መሆኑን በመግለጽ፡፡  

Read 10903 times