Saturday, 18 July 2020 16:19

የቱሪስት ታክሲ አገልግሎት ሊጀመር ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

አሮጌ ታክሲዎች ያላቸው ሰዎች በአዲስ ሊለውጡ ይችላሉ
                              
         ለአገር ውስጥና ለውጪ አገር ቱሪስቶች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ቱሪስት የታክሲ  ሥራ ሊጀምር ነው።
“ሄሎ ታክሲ” ከአክሎክ ጀነራል ሞተርስ ጋር በመተባበር፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገር ውስጥና ለውጪ አገር ቱሪስቶች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ የ2020 ሞዴል መኪኖችን 25% ቅድመ ክፍያ በመክፈልና ቀሪውን በ5 ዓመት ተከፍሎ እንዲያልቅ በማድረግ ለህብረተሰቡ ማቅረቡ ተገልጿል።
ትናንት በሸራተን አዲስ በተካሄደ ፕሮግራም ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው እንደተናገሩት፤ መንግስት የቱሪዝም ዘርፍን ለመደገፍ ባለው ፍላጐት እነዚሁ ለቱሪስት አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖች ከቀረጥ ነፃ ገብተው፣ በአገር ውስጥ እንዲገጣጠሙና በአነስተኛ ዋጋ ለአገልግሎት ሰጪዎቹ እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመው፤ ባለመኪኖቹ መኪኖቹን ለተፈቀደላቸው አገልግሎት ብቻ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል። ከህጉ ውጪ ሲሰሩ በተገኙት ላይ መንግስት ጠበቅ ያለ እርምጃ የሚወስድ መሆኑንም ዶ/ር ሂሩት ተናግረዋል።
የእነዚህ የቱሪስት ታክሲ አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ቱሪስቶቹ የሚፈልጓቸውን መረጃዎች ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው የገለፁት ሚኒስትሯ፤ መ/ቤታቸው ለእነዚህ አሽከርካሪዎች የአገሪቱንና የቱሪዝም መዳረሻዎችን አቀባበል፣ የቋንቋ ስልጠናና የእንግዳ አያያዝ ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ከ172,500  ብር ቅድመ ክፍያ ጀምሮ መኪናዎችን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መጀመሩን የገለፁት የሄሎ ታክሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ዮሐንስ ለብዙ ጊዜ ያገለገሉ አሮጌ ታክሲዎች ያሏቸው 250 ሰዎች አሮጌ መኪኖቻቸውን ብቻ እንደ ቅድመ ክፍያ በዋጋ ተቀብሎ አዳዲስ ሞዴል ዘመናዊ መኪኖችን ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ህብረተሰቡን ለረዥም ጊዜ በታክሲ ስራ ሲያገለግሉ ሊቆዩ ሰዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።
ሄሎ ታክሲ የትራንስፖርትና የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ፣ አውሮፕላኖችን አስገብቶ የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመርና ቱሪስቶችን በሄሊኮፕተር ለማመላለስ በዝግጅት ላይ መሆኑንና የዚህ ሥራ ሂደት ከግማሽ በላይ መጠናቀቁን ገልፀው፤ ከውጪ ኢንቨስተሮች ጋር በጋራ በመሆን በቅርቡ አገልግሎቱን ለመጀመር እየሰሩ መሆኑን አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።

Read 3090 times