Saturday, 18 July 2020 16:20

አዲስ ዐመል

Written by  ደ.በ
Rate this item
(6 votes)

  ፍቅሯ ውስጤ እየገፋ ሲመጣ ይታወቀኛል፡፡ ነጋ መሸ እንደ ዳንስ ውስጤ የሚላወስ፤ ነፍሴን እንደ ጡጦ የሚጠባ ምትሃት፤ አጠገቤ ተቀምጣ እንድትናፍቀኝ የሚያደርግ ምትሃት እንደሆነ ይታወቀኛል፡፡ አሁን አራት ወራት አልፈናል ብዬ ሳሰላው፣ ነገሩ ይደንቀኛል፡፡ የናፍቆት የሰቀቀን ጊዜ ይሆንብኛል፡፡ ነገሩ ሁሉ እንደተገናኘን ሰሞን አይደለም፤ በተለይ የእርሷ ፀባይ ድብልቅልቅ ይላል፡፡ አሁን ሣቀች  ሲባል፣ በማይረባ ሰበብ፣ ፊትዋን ትዘፈዝፈዋለች፡፡ እንደሱ የሚያስጠላኝ ነገር የለም፤ ለዚያውም ከፍ ያለ ከንፈር እንኳን የላትም፤ ያለቻትን ያችኑ ስስ ከንፈር ልትከምራት ትሞክራለች፡፡ እንደ ፈርጥ የሚንቦገቦጉት ዓይኖቿዋ ናቸው - የማይለወጡት፡፡ የባሰባት ቀን በደም ካልነከረቻቸው በቀር  ሁሌም አግባቢና አባባይ ናቸው፤ ብ-ል-ጭ ስታደርጋቸው ልቤ እግሬ ስር ትወድቃለች፡፡
ስልክ ስደውልላት አንዳንዴ በጥሩ መልስ፣ ሌላ ጊዜ ደሞ ኩርፊያ በወጠረው ድምፅ ትኮፈስብኛለች፡፡ በዚያ ላይ ድምፅዋ ብዙም ውብ አይደለም፤ የሆነ ፍሬ የዋጠ ወንድ አይነት ጐርናና ነው፡፡ እርሷ ግን ያወቀች አይመስለኝም፡፡ ያንኑ ድምፅ ሥታሻግረው ጆሮን እንደ ማጭድ ይከረክራል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ አብዝታዋለች፤ በሆነው ባልሆነው ትነጫነጫለች፤ ቀጠሮ ይዘን ቀድማ ትመጣ የነበረችው ሴትዮ ሰበብ እየደረደረች አንድ ሰዓት ሁለት ሰዓት ታስጠብቀኛለች፡፡ አንጀቴ እያረረ ጥርሴን ነክሼ እታገሳታለሁ፡፡
“ምን ሆነሽ ነው?“ ስላት
“የደላው ሙቅ ያኝካል!” ብላ ሌላ ሰበብ ትደረድራለች፡፡
በቅርቡ ያመጣችው ሰበብ ደግሞ መኪና ለመግዛት ደላላ ጋር ሄዳ በየጊዜው እያለቃቀሰች መመለስ ነው፡፡ ያሪስ አግኝቻለሁ ትልና ትሄዳለች፤ ስትመለስ አንዳች ምክንያት  ትሰጣለች፤ በኋላ ደግሞ ወደ ቪትሱ ትመለስና ከደላሎች ጋር ስትቀጣጠር ከአስር ጊዜ በላይ ይሆናል:: አንዳንዴ ደግሞ መኪናውን በመካኒክ እስከ ማስመርመር ትደርስና ወጭ ካወጣች በኋላ በዋጋ ሣይስማሙ ይቀራሉ፡፡ ወይም የሚጠገንበትን ዋጋ ሻጩ መሸፈን አለበት ስትል ሻጮቹ “በፍፁም! ራስሽ ቻይ!” ይሏትና ይፋረሳሉ፡፡
መኪና ፍለጋ ወጥታ የተመለሰች ቀን በድምፅዋ አውቃለሁ፡፡ ከዚያ ቀድማ ስልክ ቶሎ አታነሳም፤ በመከራ ካነሳችም ቁጣ ቁጣ ይላታል፡፡ እኔም ነገሩ ስለሚገባኝ አግባብቼ ስልኩን እዘጋለሁ፡፡ ሠሞኑን ደግሞ አዲስ ፀባይ አምጥታለች፡፡ ለሁሉም ነገር መልሷ ቁጣ ነው፡፡ በቀደም ምሣ እንብላ ብያት በራሷ ምርጫ ሜክሲኮ ገብተን ስንት ጊዜ እንደተበሳጨች መቁጠር እንኳን ይከብዳል፡፡
መጀመሪያ ሜኖውን አይታ እየተሰላቸች “እስቲ የቱ ነው ጥሩ? “አለቻቸው፤ አዛውንቱን አስተናጋጅ፡፡
“የፈረንጅ ወይስ የሀበሻ ምግብ?”
“የሀበሻ”
“ዓሳ ኮተሌ ይሻልሻል”
“እሺ” ብላ መለስ አለች፡፡
እኔም የራሴን አዘዝኩ፡፡ እኔ የፈለግሁት ላዛኛ ነበር፡፡
“ለምን ኮተሌ አትበላም?”
“አልፈልግም”
“ፀባይህ ከሰው አይገጥም!”
እንዳልሰማሁ አለፍኳት፡፡
ትንሽ ቆየችና “ይሄ ቤት ወደቀ መሰለኝ” አለች፤ ዝንቦቹን በመፀየፍ በእጇ እያባረረች::
“አይ ሠዓቱ ነው፤ የምሳ ሰዓት አልፏልኮ"
“አንቺ አስረፈድሽኝ ለማለት ነው?”
“እንደዚያ አላልኩም ግን ዘጠኝ ሰዓት ሆኗል”
“እኔ እንደቆየሁ አውቃለሁ፤ ምን ላድርግ ያ ሰውዬ ቤት መጥቶ አልወጣ አለ" ብዬ አልኳት ብዙ ጊዜ እኔም እያለሁ ይደውልላታል፡፡ ደስ ባይለኝም ዝም እላለሁ፡፡
“ከኔ ጋር ማውራት ይወድዳል፤ ወሬውን ደግሞ ቶሎ አይቆርጥም"
ሣቄ መጣ፤ ምን አገባኝና ነው ለኔ የምታወራው፤ ካልፈለገችው በደወለላት ቁጥር ምን ያሮጣታል? ሽፋን ፍለጋ ይሆናል ብዬ ምግቡን መጠበቅ ጀመርኩ፡፡
“የሚጠጣ ምን ላምጣ?”
“ለኔ ግማሽ ሊትር ውሃ ያምጡልኝ”
“ቀዝቃዛ ይሁን ከውጭ?”
“መካከለኛ”
ዐይኖችዋ እንደ አምቡላንስ መብራት ሲገለባበጡ አንጀት ይበላሉ፡፡ ልብን አገላብጠው ይጋረፋሉ፤ ግን ደግሞ ውበታቸው ላይ ንጭንጭዋ ጭቃ እየመረገበት ነው፡፡ የሆነ ነገርዋን እየነጠቃት ነው፤ እንደ ዐውደ ዓመት ይነጠፍላት የነበረ ልቤ እምቢ እያለኝ ከመጣ ቆየ፡፡ እንደ በፊቱ ሣያት አልደነግጥም፡፡ አንዳንዴ “ኤጭ ደሞ ምን ልትል ነው?” ማለት ጀምሬያለሁ፡፡
እርሷም እንደ ሰው መለወጧ ያስታውቅባታል፡፡ ምክንያቱ ግን አልገባኝም:: መጀመሪያ እገዛለሁ ያለችው መኪና ገበያ ያማረራት ይመስለኛል ነበር፡፡ በኋላ ግን - ሣየው - ያ- ብቻ አይደለም፡፡ የማትበሳጭበት ነገር የለም፡፡ አንዳንዴ የአፍና የአፍንጫ ጭንብሏን ሥታወጣ “አድርጊው” ስላት እንኳ ትበሳጫለች “ሕፃን አደረከኝ እንዴ? እኔ እንደ ምክር የሚያስጠላኝ ነገር የለም !” ብላ ነብር ትሆናለች፡፡
በፊት ግን እንዲህ አትመልስም ነበር:: ገና እንደተዋወቅን ስልክ ስትደውልልኝ፣ የድምፅዋ ዜማ፣ የሳቅዋ መፍለቅለቅ ልዩ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ በዚያ ላይ በዕውቀት ማማ ላይ የተንሳፈፈች ትመስል ነበር፡፡ ብዙ ሀሳቦችን አንስታ ታወራኝ ነበር:: አቤት ያኔ የሚሰማኝ ዕድለኝነት … ይህችን እጄ ያስገባኋት ዕለት ወደ ገነት እንደ መግባት እቆጥረዋለሁ ብዬ አስብ ነበር፡፡
ስሟም ቀለል ያለ ነው - “ሊ” ነው፡፡ እንግዲህ ሊሊ- ከሚለው ቆርጠውት ይሁን፤ አይሁን ባላውቅም ስሟ የመጨረሻው አጭር ነው፡፡ ታዲያ ስሟ ከሙዚቃ የበለጠ ልቤን ያስደስታት ነበር፡፡
“ላንቺስ የሚጠጣ ነገር?”
“ስፕራይት”
አስተናጋጁ  ሲሄዱ፤ “ንቁ አይደሉም” አለች
ዝም አልኳት፡፡ እንደ ዛሬ ዘንጣ አታውቅም፤ እጅዋ ሣይቀር በጌጣጌጥ ተሞልቷል፤ ከንፈሯም ቅንድቧም ተቀባብቷል፤ ጠይም ፊቷን በምን እንዳቀላችው ባላውቅም አበባ መስላለች፡፡ ምናልባት ስቲም ገብታ ይሆናል፡፡
ከአንድ ሰዓት በፊት ደውዬ ገላዋን ታጥባ እንደወጣች እንደሆነ ነግራኝ ነበር፡፡ ወደ ምሳ እንሂድ ስላት ደግሞ “ቆይ ልለባብስ” አለችኝ
ምሳዋን እየተነጫነጨች በልታ፣ እንደ ህፃን ልጅ ባለ ኩርፊያ ድንገት “እንውጣ” አለችኝ
“ቆይ እንጂ ትኩስ ነገር እንጠጣ” አልኳት
ትንሷን ከንሯን እንዳንጠለጠለች “መሄድ እፈልጋለሁ” አለች
“አብረን እንሄዳለን!”
ስልክ አስሬ ታወራለች፡፡ እየሰለቸኝና እየታከተኝ መሄዱን ያወቀች አይመስለኝም፡፡
“አሁን ወዴት ነው የምንሄደው?”
“ደራሲው ጓደኛዬ ጋ”
“ምን ልናደርግ?”
“ለራሴ ጉዳይ”
“ዝባዝንኬያችሁን ልታወሩ?”
“አዎ”
እንደ መደንገጥ አለችኛና “ያው ነገር ለመፍተል ማለቴ ነው”
“አንቺ ምን ልትፈትይ ነው?”
ፈገግ እንደ ማለት አለችና  “ይሄ ኔትወርክ ደግሞ ራይድ መጥራት አይቻል ነገር”
“ለምን ደንበኛሽን አትጠሪውም?”
“ልጠራው ነው”
“እኔ ልሂድ;
"የተወሰነ መንገድ ከኔ ጋር መሄድ ትችላለህ”
“መንገዳችን ለየቅል ነው”
“ጥሩ ደንበኛ አስተዋወከኝ”
"መነሻው ሰፈርሽ ስለሆነ መቼም ቢሆን ይጠቅምሻል"
“ዋው በጣም! በዚያ ላይ ፀባዩስ--”
“ስለ ፀባዩ አላውቅም!... የሾፌር ፀባይ ላይ ብዙ ትኩረት የለኝም፡፡ ፀባይ ከሌለው ልቀይረው ስለምችል ደንታ የለኝም”
ዝም አለች፡፡
“ቢሆንም ፌሊሞን ፀባዩ የተለየ ነው”
“ነገርኩሽ… ለኔ የሾፌር ፀባይ አሣሣቢ አይደለም”
“አሳሳቢው ምንድን ነው?”
“ያንቺ ፀባይ”
“የኔ ፀባይ …ምን ያደርግልሀል?”
“የያዝነውን ከግብ ለማድረስ”
“ኳሷ ግቧ ደርሳለች፤ አንተ ራስህ ኳሷን ለፌሊሞን አቀብለሀታል"
“እንዴት?”
“ሹፌሩን ወድጄዋለሁ …ምንም ማድረግ አይቻልም! አንተ አበሳጭተኽኝ ስሄድ የምፅናናው በርሱ ነው”
“እንኳን ደስ አለሽ!”
“እንደውም መጣ ልሂድ--”
“ዐይኔ እያየ በራይዱ ገብታ ሄደች”
“ትራንስፖርት አጣሁ” ያለችኝ ጊዜ ሺህ ቦታ ደውዬ ሠፈሯ የሚገኝ የራይድ ሹፌር ስልክ ብሰጣት ባሏ አድርጋው አረፈች…ወይ ዕድል!Read 2133 times