Saturday, 25 July 2020 14:50

በአማራ ዩኒቨርስቲዎች የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በደባርቅ ዩኒቨርስቲ 21ሺህ ችግኝ ሲተከል፤700 ሰው ተሳትፏል
                      
                የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምክንያት በማድረግ በአማራ ክልል በሚገኙ አስር  የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው፡፡ የችግኝ ተከላው ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣በጮቄ ተራራ የተጀመረ ሲሆን በዚህ መርሃ ግብር ከእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ 20 አባላት መሳተፋቸው ታውቋል:: በነጋታው ሰኔ 10 ደግሞ በአጠቃላይ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ከመጠበቅ አንፃር ዩኒቨርስቲዎቹ ምን ማድረግ አለባቸው በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡
የችግኝ ተከላው በባህርዳር ዩኒቨርስቲ አስተባባሪነት፣ በባህርዳር ከተማ የቀድሞው ቤተ መንግስት አካባቢ የተከናወነ ሲሆን ቀጣዩ መርሃ ግብር በደባርቅ ዩኒቨርስቲ አስተባባሪነት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ “ምጭብኝ” በተሰኘ ቦታ ከ21ሺህ በላይ አገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል:: በዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ሁሉም የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች እንዲሁም የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡
በዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የሰሜን ጐንደር ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የደባርቅ ከተማ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ከችግኝ ተከላው በኋላ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ባደረጉት ንግግር፤ የክልሉ ዩኒቨርስቲዎች የአረንጓዴ አሻራን መርሃ ግብር ለማሳካት  የወሰዱትን ተነሳሽነትና ጥምረት አድንቀው፣በዕለቱ የተተከሉት ከ21ሺህ በላይ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበትን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በመታደግም ሆነ ለአባይ ግድብ ዘላቂ ልማት የላቀ አስተዋጽ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጀጃው ደማሙ በበኩላቸው፤ የዛሬ 3 ዓመት የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ዩኒቨርስቲው ሲገነባ ጀምሮ የአካባቢውን የተፈጥሮ ዛፎች ባሉበት አስቀጥሎ ከመንከባከቡም በላይ አረንጓዴ ዩኒቨርስቲ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤አሁንም በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተተከሉትን ችግኞች በጋራ በመንከባከብና የፓርኩን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የችግኝ ተከላው በቀጣይ በደብረ ብርሃን፣ በወሎና በወልዲያ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ፎረም አስታውቋል፡፡


Read 988 times