Saturday, 25 July 2020 14:53

በሰሜን ጐንደር ዞን የግጭ ማህበረሰብ አባላት፣ መንግስት እንዲደርስላቸው ተማጸኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  "ከቦታችን ተነቅለን ስንመጣ የተገባልን ቃል አልተፈፀመም
                          

                በሰሜን ጐንደር ዞን የአበርጊና ቀበሌ የግጪ ጐጥ ነዋሪ የነበሩት አርሶ አደሮች፣ በረሃብ ማለቃችን ነው በማለት መንግስት ይድረስልን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ አርሶ አደሮቹ ግጪ በሚባለው ቦታ ከልጅነት እስከ እውቀት ትርፍ በማምረትና ለማዕከላዊ ገበያ ምርት በማምረት ጥሩ ኑሮ ሲመሩ የነበረ ቢሆንም፣ ቦታቸው በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በመሆኑ ለፓርኩ ደህንነት ሲባል በ2008 ዓ.ም ከቀዬአቸው ተነስተው ደባርቅ ከተማ መስፈራቸውን ይናገራሉ፡፡
ይሁን እንጂ ከቀያችን ስንነሳ የተገባልን ቃል አልተፈፀመም፤ የካሳ ክፍያውም በተገባልን ቃል መሰረት አልተከናወነም፣ ለእኛም ሆነ ለወጣት ልጆቻችን ፕሮጀክት ተቀርፆ ስልጠና ተሰጥቶ የስራ እድል ይፈጠራል የተባለው እውን ባለመደረጉ ያለ ስራ ተቀምጠን በረሃብና እርዛት ተጐድተናል ሲሉ ለአዲስ አድማስ ቅሬታቸውን ገልጠዋል፡፡ የካሳ ክፍያውም ቢሆን ከፍተኛው 2ሚ ብር፣ ዝቅተኛው ደግሞ 1 ሚ ብር እንደሆነ ቢነገረንም፣ የተገባው ቃል አልተፈጸመም፤ በዚህም የተነሳ በተሰጠን መሬት ላይ ጐጆ ቀልሰን የተረፈንን ቀለብ ገዝተን ጨርሰን፣ ላለፉት አራት አመታት ያለ ስራ በመቀመጣችን ለረሃብ ተዳርገናል ሲሉ አማርረዋል፡፡
 የ70 ዓመት የእድሜ ባለፀጋው ኡስማን አደም እንደሚናሩት፤ ራሳቸውን ጨምሮ 10 ቤተሰብ ይዘው በደባርቅ ከተማ ያለ ስራ መቀመጣቸው ለችግር እንደዳረጋቸው ይናገራሌ፡፡ ከቀያችን ስንለቅ ትከርማላችሁ ተረጋጉ ካሉን በኋላ ድንገት ተነሱ ብለው ረመዳን ጦም ላይ እያለን ነው የተነሳነው፤ በዚህም የተነሳ ከብቶቻችን፣ እህላችን በጐተራ እንደሞላ በጐቻችን ሁሉ የትም ወድቀው ቀሩ::" ይላሉ-በቁጭት፡፡ ያም ሆኖ መንግስት የገባልንን ቃል ባለማክበሩ፣ ነዋሪው የ5 እና 10 ሺህ ብር ካሳ ብቻ ተሰጥቶን በከተማው ላይ ፈስሰን፤አሁን በረሃብ እየተሰቃየን እንገኛለን ብለዋል አዛውንቱ፡፡
የግጭ ማህበረሰብ ወጣቶችን በመወከል አቤቱታውን የነገረን ወጣት አደም ሙላት በበኩሉ፤ በከተማው በርካታ የስራ እድሎችና አደረጃጀቶች ቢኖሩም፣ የግጭ ማህበረሰብ ወጣቶችን ዞር ብሎ የሚያየን በማጣታችንና ለከፍተኛ ችግር በመጋለጣችን፣ ሃይማኖታችን ወደማይፈቅደው ሥርቆት እንድንገባ እየተገፋፋን ነው ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁሟል፡፡  
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው እንደሚሉት፤ እነዚህን 252 አባወራዎች አወያይቶና አሳምኖ ደባርቅ እስከ ማስፈር ድረስ የነበረው ሂደት ትክክል ነበር:: የቦታና የሀብት ግመታውም በፌደራል ካሳ ግመታና አከፋፈል መመሪያ መስት የተከናወነ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡ እንደ ሃላፊው ገለፃ፤ ሁሉም አርሶ አደሮች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ከፍተው የተገመተላቸው ካሳ መግባቱንና የቤት መስሪያ ለእያንዳንዳቸው 250 ካ.ሜ የከተማ ቦታ ማግኘታቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይላሉ አቶ አበባው፣ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች የተሰጣቸው ብርና ቦታ ብቻ ነው፤ በዚያ ላይ ለከተማ ኑሮ አዲስ በመሆናቸው የአነስተኛና ጥቃቅን ስልጠና ለመስጠት፣ የብድር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት አመቻችቶ ወደተለያየ ሥራ ለማስገባት ፕሮጀክት ተቀርፆ እቅድ መያዙንም ያወሳሉ:: ይህ በሂደት ላይ እያለ በ2008 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በተነሳ ቀውስና አለመረጋጋት ሳቢያ  ሁሉም አገርን ወደማረጋጋት በመግባቱ አርሶ አደሮቹ መዘንጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አርሶ አደሮቹ በተሰጣቸው ቦታ ቤት ሰርተው የተረፋቸውን ገንዘብ ቀለብ እየገዙ በመብላት በመጨረሳቸውና ያለ ስራ በመቀመጣቸው ችግራቸው መጠነ ሰፊ፣ ቅሬታቸውም ትክክል ነው፤ ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል:: ስለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል ብለዋል፤ ሃላፊው፡፡  Read 763 times