Saturday, 25 July 2020 14:55

ኢትዮጵያ ለ36 ቀናት ኢንተርኔት ዘግታ 130 ሚ. ዶላር አጥታለች

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ለ36 ቀናት ያህል ኢንተርኔት በማቋረጧ ሳቢያ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማጣቷን የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የመረጃ ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ትብብር የተሰኘው ተቋም አመለከተ፡፡
ተቋሙ ባወጣው የጥናት ውጤት፤ ኢትዮጵያ ለ36 ቀናት ያህል ኢንተርኔትን በማቋረጧና ለሰባት ቀናት ያህል የማህበራዊ ሚዲያዎች በአግባቡ አገልግሎት ባለመስጠታቸው በአጠቃላይ ከ130 ሚሊየን ዶላር በላይ ማጣቷን ጠቁሟል፡፡
የተቋሙ ጥናት አገሪቱ ኢንተርኔት በዘጋችበት በእያንዳንዱ ቀን ከ3.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ የመልዕክት መተግበሪያዎች በታወኩበት አንድ ቀን ደግሞ ከ870ሺ ዶላር በላይ እንደምታጣ አመልክቷል፡፡ በዚሁ የጥናት ውጤት ላይ እንደቀረበው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢንተርኔት ለቀናት እንዲዘጉ ያደረጉ አገራት የሚገጥማቸው ኢኮኖሚያዊ ጠባሳ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮአቸው ይቆያል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በብሔራዊ ፈተናዎች ወቅት የፈተና ጥያቄዎች ሾልከው እንዳይወጡ በሚል ምክንያት ለቀናት ኢንተርኔት መዝጋቷን ያስታወሰው ተቋሙ፤ ተቃውሞ፣ አገራዊ አለመረጋጋቶችና ረብሻዎች በተነሱባቸው ጊዜያትም ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ተደርጓል ብሏል፡፡ ኢንተርኔቱን የሚያስተዳድረው ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ መንግስት ስለ ክስተቱ ይፋዊ መግለጫ እንዳልሰጡ ያመለከተው የተቋሙ ረፖርት፤ የኢንተርኔት መዘጋት ከሚያስከትለው የኢኮኖሚ ኪሳራ በተጨማሪ የመረጃ ተደራሽነትንና የመናገር ነፃነትን በማወክ፣ የዜጐችን መሠረታዊ መብቶች እንደሚገድብ ይጠቁማል፡፡
ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት በአስራ ሁለቱ ኢንተርኔትን የመዝጋት መንግስታዊ እርምጃ መወሰዱን ያተተው ተቋሙ፣ እነሱም ቻድ፣ ጋቦን፣ ኢትዮጵያ፣ ጋምቢያ፣ ኮንጐ፣ ኡጋንዳ፣ ካሜሩን፣ ማሊ፣ ኒጀርና ቶጐ ይገኙበታል፡፡
ካሜሮን በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ93 ቀናት ኢንተርኔቷን የዘጋች ሲሆን ኢትዮጵያ ለ36 ቀናት ያህል የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጧን መረጃው ያመልክታል፡፡



Read 5379 times