Saturday, 25 July 2020 14:56

የዶሮ አርቢዎች ማህበር ኮቪድ ለኪሳራ ዳርጐኛል አለ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

   በቀጣዮቹ ወራት የእንቁላልና የዶሮ ዋጋ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል
                          
             የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ የዶሮ እርባታ ስራ ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል ተብሏል::
የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቅራቢዎች ማህበር ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ዘርፉ ወረርሽኙ ባስከተለባቸው ቀውስ ሳቢያ የእሴት ሰንሰለቱ ስለታወከና የግብአት አቅርቦት ችግር በመፈጠሩ እንዲሁም አዳዲስ የሚፈለፈሉ ጫጩቶችን ተረካቢ በመጥፋቱ ምክንያት ጫጩቶቹን በመግደል ለማስወገድና በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከውጪ አገር ተገዝተው የገቡትን የዘር እንቁላል ጣይ ዶሮዎች በማረድ ለማስወገድ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
በማቀነባበሪያ ድርጅቶች የተመረተው የዶሮ ስጋ ከሆቴሎች እንቅስቃሴ መገደብ የዩኒቨርሲቲዎች መዘጋትና አንዳንድ ዝግጅቶች መቋረጥ ጋር ተያይዞ ምርታቸውን የሚረከባቸው በመጥፋቱና ከጥቅም ውጪ በመሆኑ ዘርፉ ባለፉት 6 ወራት 124 ሚሊዮን ብር ለሚጠጋ ኪሳራ መዳረጉን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማህበር ሊቀመንበር ዶ/ር ምስጋናው ፍፁም ብርሃን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ አስራ አሪት አባላቱን እንደማሳያ በመውሰድ መረጃ ማሰባሰቡንና ጥናት ማድረጉን ያመለከቱት ዶ/ር ምስጋናው ድርጅቶቹ ጫጩቶች የማምረት ስራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን፣ ከውጪ አገር በከፍተኛ ወጪ የተገዙ ዶሮዎችን በማረድ ማስወገዳቸውንና ከሶስት ሺ ኪሎ ግራም በላይ የዶሮ ስጋ ተበላሽቶ እንዲወገድ ማድረጋቸው በመግለጽ ይህም ድርጅቶቹን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡
ወረርሽኙ አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ዘርፉ ለከፋ አደጋ እንደሚጋለጥ የጠቆሙት ሊ/መንበሩ፤ በመጪዎቹ ወራት የእንቁላልና የዶሮ ዋጋ በእጅጉ ሊያሻቅብ እንደሚችል  ገልፀዋል፡፡ መንግስት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው የተለያዩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ለዶሮ እርባታና ማቀናበር ዘርፍም ሊያደርግ እንደሚገባው ዶ/ር ምስጋናው ገልፀው፤ ይህ ካልሆነ ግን ዘርፉ ክፉኛ እንደሚጐዳ ተናግረዋል - ከፍተኛ ደረጃ አምራች ድርጅቶች ጉዳቱን ለመቋቋም አቅም እንደሚያጥራቸውና አነስተኛ አምራቾች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከስራ ለመውጣት እንደሚገደዱ በመግለጽ  መንግስት ሊደርስልን ይገባል ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡
የበሽታውን ስርጭት በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ካልተቻለ ለስራው የሚያስፈልጉ ግብአቶች፣ መኖ የክትባት መድሃኒቶችና መሳሪያዎች እጥረት ሊከሰት እንደሚችልና ድንገተኛ የዶሮ በሽታ ቢከሰት ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሚሆን መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዶሮ ስጋ ክምችት ስላለ በትንሽ ትርፍ ለበላተኛው እንዲደርስ ከከተማ መስተዳድሮች፣ እንዲሁም ከሆስፒታሎች ማቆያ ጣቢያዎች ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል፡፡

Read 6534 times