Saturday, 25 July 2020 14:53

2618 አዲስና ነባር የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    ድርጅቶቹ ገቢ ለማግኘት በንግድና ኢንቨስትመንት መሰማራት ይችላሉ

             በአሁኑ ወቅት 2618 አዲስና ነባር የበጐ አድራጐትና ማህበራት ድርጅቶችን መመዝገቡን ያስታወቀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፤ አብዛኞቹ ድርጅቶች በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ናቸው ብሏል፡፡
በኤጀንሲው የመረጃ ቋት ውስጥ አስቀድሞ 3512 ድርጅቶች ተመዝግበው እንደሚገኙ እና በድጋሚ እንዲመዘገቡ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት በድጋሚ ምዝገባው 1789 ነባር ድርጅቶች መመዝገባቸውን ከእነዚህ ውስጥ 1464 ያህሉ ሀገር በቀል ሲሆኑ፤ 325 የውጭ ድርጅቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ 1043 አዳዲስ ድርጅቶች ለመመዝገብ አመልክተው፣ 829 ያህሉ መመዝገባቸውን ኤጀንሲው ጠቁሞ፤ቀሪዎቹ ካመለከቱ በኋላ በራሳቸው ምክንያት መቅረታቸውን አውስቷል:: በየወሩ   በአማካይ 70 ድርጅቶች ለምዝገባ እያመለከቱ ነው የተባለ ሲሆን ከሐምሌ 1 እስከ 15 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 25 ድርጅቶች መመዝገባቸው ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ከተመዘገቡት ውስጥ 417 ያህሉም የውጭ ድርጅቶች መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ ድርጅቶች በበጐ አድራጐትና መሠል ዘርፎች የተመዘገቡ ሲሆን በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ይሰራሉ ተብሏል፡፡ በአዲሱ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ መሰረት፤ ተቋማቱ ከገቢያቸው 20 በመቶ ብቻ ለአስተዳደራዊ ወጪ  የሚጠቀሙበት ሲሆን 80 በመቶው ለተሰማሩበት በጐ አድራጐት በቀጥታ የሚውል ነው፡፡  
ተቋማቱ ቴሌቶንን ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን ተጠቅመው ገቢያቸውን ማደራጀት እንደሚችሉ የሚገልጸው የኤጀንሲው ህግ፤ ገቢ በሚያስገኝላቸው ማንኛውም ንግድ እና ኢንቨስትመንት ላይ መሠማራት እንደሚችሉ በህጉ መቀመጡ ተመልክቷል፡፡ ማንኛውም ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅቶች፣ በምርጫ ጉዳይ በታዛቢነት መሳተፍ እንደሚችሉም በህጉ ተቀምጧል፡፡


Read 871 times