Saturday, 25 July 2020 15:01

በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያጋልጥ ኔትዎርክ ተመሠረተ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችንና መገናኛ ብዙሃንን እየተከታተለ የሚያጋልጥና ማህበራዊ ገፆች የሚያዘጋ ኔትዎርክ  ተመሠረተ፡፡
በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመሠረቱት ይህ የፀረ - ጥላቻ መልዕክቶች ቁጥጥርና ክትትል ኔትዎርክ፤ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጩትን የዘረኝነትና የጥላቻ መልዕክቶች እየተከታተለ ለህግ ለህግ የሚያቀርብ ሲሆን ማህበራዊ ገፆችንም ያዘጋል ተብሏል፡፡
ኔትዎርኩ መስራቾች አንዱ የሆኑት የቀድሞ “የግንቦት 7 ንቅናቄ” አመራር አቶ ነአሞን ዘለቀ፤ የተቋቋመው የክትትል ኮሚቴ በህግ፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሠፊ እውቀትና ልምድ ባላቸው ግለሰቦች የሚመራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኔትዎርኩ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን አክቲቪስቶችን፣ መቀመጫቸውን በአሜሪካ፣ ካናዳና አውሮፓ ያደረጉ የሲቪክ ተቋማትን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡
በዋናነት የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦችን፣ መገናኛ ብዙሃንንና ሌሎች በተቋም ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አካላትን እየተከታተለ የጥፋት እንቅስቃሴያቸውን ለማክሸፍ የተመሰረተው ኔትዎርኩ፤ ኢትዮጵያን ከብጥብጥና ትርምስ የመታደግ አላማ እንዳለውም ተገልጿል፡፡   
በዋናነት የዘር ፍጅት እንዲቀሰቀስ ይሠራሉ የሚላቸውን መገናኛ ብዙሃንም የማዘጋት አላማ እንዳለው የኔትዎርኩ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ ላለፉት 3 ሳምንታት ተዘግቶ የቆየው የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት ከትናንት በስቲያ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የቀጠለ ሲሆን ኢንተርኔት ተዘግይቶ በቆየባቸው ሳምንታት አገሪቱ በየቀኑ ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ስታጣ እንደነበር መዘገቡ ይታወቃል፡፡


Read 10280 times