Wednesday, 29 July 2020 00:00

ሕዳሴ እምቢ ብሎ ሞላ፤ የግብጽ “ቬቶ” ተሰበረ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  ግብጽና ሱዳን አንድ አይነት ስምምነት ሳይደረግ፣ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የሕዳሴውን ግድብ ውኃ መሙላት እንዳትጀምር ማስጠንቀቂያ አከል ማሳሰቢያ ሲሰጡ ቆይተዋል:: የአሜሪካ መንግሥትም አንዱ ማስጠንቀቂያ ሰጪ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የዋሽንግተን ድርድር ከፈረሰ በኋላ ወደ አምስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ መደራደሩ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በአሜሪካ የተዘገጀውን ሰነድ ለመፈረም ፈቃደኛ ያልነበረችው ሱዳን፤ ኢትዮጵያና ግብጽ ወደ ደርድሩ እንዲመለሱ አደረገች:: ድርደሩ ቢጀመርም ያስገኘው ውጤት ‹‹በቴክኒክ ጉዳዮች ዘጠና ከመቶ መስማማት ተችሏል›› የሚል ተደጋጋሚ መግለጫ ከመስጠት በላይ እንዳልወጣ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ‹‹ከአንቺ ፈቃድ አልወጣም›› እንድትላት የፈለገችው ግብጽ፤ ለማግኘት የተመኘቸውን ማግኘት ባለመቻሏ፤ ‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ሶስቱ አገሮች ከስምምነት ሳይደርሱ የሚሞላ ከሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም ሰጋት ይሆናል›› በማለት ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ወሰዱት፡፡  በጽሑፍ ለቀረበበት ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽሑፍ መልስ ሰጠ፡፡  ምክር ቤቱ አገራቱ በጀመሩት የሦስትዮሽ ድርድር ላለመስማማታቸው መፍትሔ እንዲፈልጉ መክሮ ግብጽን መለሳት፡፡
ድርድሩ ከአጠቃላይ ጉዳይ አስር ከመቶ ድርሻ በተሰጠው የድርድሩ ሃሳብ ላይ ሦስቱ አገሮች ተቀምጠው ቢመክሩም፣ ግብጽ እንደፈለገችው ኢትዮጵያን ከአንድ አስገዳጅ ውል ማስገባት ሳትችል ቀረች፡፡ እጅ መጠምዘዝ የፈለጉት ግብጾች የሚጠመዘዝ እጅ አጡ፡፡ በአገራቸው በሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በኢትዮጵያ ቅን ፍላጎት ማጣት መቋረጡን ገልጠው፣ አሁንም  ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ተጓዙ፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዮ ላይ በቪዲዮ (ቨርቹዋል) ስብሰባ ተቀመጠ፡፡ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴን ግድብ ከግብጽና ከሱዳን ጋር አንድ ውል ሳታስር ውኃ መሙላት ጀመረች ማለት ከሰማይ በታች ያለ መከራ በሙሉ በግብጽ ሕዝብ ላይ እንዲወርድበት አደረገች የማለት ያህል መሆኑን ተናገሩ፡፡ ዘጠና በመቶ የሚሆነው የግብጻዊያን ሕይወት በዐባይ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ግማሽ ሰዓት ያህል ወስደው አስረዱ፡፡ ከእሳቸው ቀጥለው የተናገሩት የሱዳኑ አምባሳደር፣ ሰሚህ ሽኩሪ ነገሩን ያጋነኑትን  ያህል አገር ይያዝልን  ለማለት አልፈለጉም፤ የስምምነቱን አስፈጊነት በማሳየት ነገራቸውን ጨረሱ፡፡
የኢትዮጵያን ጉዳይ ለማስረዳት የተገኙት  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ናቸው፡፡ ታዬ ያተኮሩት፤ የግብጹ ሳሚህ ሽኩር ሲተነትኑት ወደ ከረሙት የ1902 ዓ.ም የአፄ ምኒልክና የእንግሊዝ ውል፣ እ.ኤ.ኣ የ1929 እና 1959 የግብጽና የሱዳን ስምምነት በመግባት ዋጋ ቢስነቱን ለማሳየት አልፈለጉም፡፡ የመረጡት ኢትዮጵያ የምትከተለውን  በሌላው ላይ የጎላ ጉዳት አለማድረስና  ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት መርህ በማስረዳትና ምክር ቤቱ ይህን ጉዳይ የማየት ሕጋዊ መብት የሌለው መሆኑን በማስገንዘብ ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ  እንዳትገባ እየተባለ ከገባ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም አድርጎት የማያውቀውን ስለሚያደርግ ያልታሰበና ያልተጠበቀ ሁኔታ (precedent) ስለሚፈጥር በመጪ የሥራ ዘመኑ ላይ ችግር እንደሚሆንበት አሰጠነቀቁ:: ጉዳዩን ለአፍሪካ ኀብረት እንዲተወው አጥብቀው ጠየቁ:: የሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል ባይጫነው ኑሮ ለታሪክ የሚጠቀስ ክርክር እያደረጉ ላሉት  አምባሳደር ታዬ አንድ ነገር ትዝ አላቸው፡፡
ሰኔ 23 ቀን 1929 ዓ ም ነው፡፡ ቦታው ጀኔቭ የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ጉባኤ አዳራሽ ፊት ቆመው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ንግግር እያደረጉ ናቸው፡፡ የኢጣሊያ ወራሪ ጦር በሕዝባቸው ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ እየረዘሩ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ይዣለሁ ብትልም ከከተሞች ውጭ ያለው አገር ባርበኞች ቁጥጥር ስር መሆኑንና ከአርበኞች ጋርም ያላቋረጠ ግንኙነት እያደረጉ መሆኑን እየገለጡ ናቸው፡፡ እሳቸው ምንም ቢናገሩ የሚያዳምጣቸው አልነበረም:: "ለሕዝቤ ምን ይዤለት ልሂድ?" ብለው ቢማጸኑም፤ መልስ የሰጣቸው  አንድም ሰው አልነበረም:: ስለዚህም ንጉሡ ዓለም ሲያስታውሰው የሚኖር ንግግር አደረጉ፡፡
"--እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ-" ብለው ንግግራቸውን በመቋጨት ከአዳራሹ ወጡ፡፡ አምባሳደር ታዬ ይህንን ደገሙት፤ ‹‹በመንግሥታቱ ማኅብር ብቻዋን የቆመችው አገሬ፤ ዛሬም በጸጥታው ምክር ቤት ፊት ብቻዋን ቆማለች:: እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ›› በማለት፡፡
በኢትዮጵያ ላይ አንድ አይነት አስገዳጅ ውሳኔ እንዲተላለፍ አለፎም ገደብ እንዲጣል የፈለገቸው ግብጽ፤ የተመኘቸውን ሳታገኝ ቀረች፡፡ እንዲያውም ድርድሩ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አፍሪካ ኅብረት መጣ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፕሬዜዳንት ሰርሊ ጆንሰን ራማፎዛ መሪነት፣ ከአፍሪካ እነ ማሊ፣ አውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በታዛቢነት በተገኙበት ድርድሩ እንደተለመደው ቀጠለ፡፡
ሁለት ብልጥ ኑግ አያደቅም ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ከያዘቸው መርህ ፍንክች ለማለት አልፈለገችም፡፡ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂኒየር ስለሽ በቀለ ደጋግመው እንደተናገሩት፣ የግብጽ ዋና ጉዳይ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ ውኃ ሙሊት ሳይሆን ኢትዮጵያ ለወደፊት በተፋሰሱ ልታካሂድ የምትችለው ልማት በመሆኑና ኢትዮጵያ ደግሞ በምንም አይነት ውል መታሰር የማትፈልግ በመሆኗ ደርድሩ አስር ቀን ያህል ጨርሶ ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ፡፡ የግብጽና የኢትዮጵያ ድርድር አልሰመረም በተባለ ቁጥር እንደማደርገው ሁሉ፣ አሁንም  እራሴን .‹“እንኳ ደስ አለህ” አልሁት፡፡
ኢትዮጵያ ከግብጽ የምትፈልገው የላትም:: ድርድሩ ያለ ስምምነት ተቋረጠ ማለት፤ ኢትዮጵያ ጥቅሟን አሳለፋ ለግብጽ ለመስጠት አልፈለገችም ብቻ ሳይሆን ተደራዳሪዎቿም ለሀገራቸው ዘላቂ ልማት ጠንክረው እየሠሩ ናቸው ማለት ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙሪያ ድል እያስመዘገቡም ነው ማለት ነው፡፡
እነሆ "ከመስማማታችን በፊት ውኃ አትሞሉም" የተባለው የሕዳሴው ግድብ፤ ምንም አይነት ስምምነት ሳይደረግ ተሞላ:: ትልቁ ድል! ኢትዮጵያ የማትገዛበት ቢሆንም፣ አ.ኤ.አ 1959 የግብጽና የሱዳን ስምምነት አስገኘልን የሚሉት በላይኛው የ!ተፋሰሱ አገሮች ላይ  የበላይነት ድምጽ (ቬቶ ) መሰበሩ መሰባበሩ ነው፡፡ ይህ  ደግሞ ፈረሱም የእኛ፤ ሜዳውም የእኛ ብቻ ሳይሆን ልጓሙም በእኛ እጅ ነው ማለት ነው:: እዚህ ላይ ለተደራዳሪዎቻችንና ለመንግሥት ከፍ ያለ አክብሮት እንዳለኝ የምገልጠው በትህትና ነው፡፡
አለቃ እንባዐቆም የሚባሉ ቅኔ አዋቂ ነበሩ:: ቅኔ ዘርፈው ሰሚው አልተረዳኝም ወይም አይረደኝም ብለው ባሰቡ ጊዜ ‹‹እደግመዋለሁ›› እያሉ ቅኔውን  ይደግሙ ነበር፡፡ እኔም የምደግመው አለኝ፡፡
‹‹በዓባይ ጉዳይ ግብጽ በረጅም ገመድ የታሰረች ዕቃ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል ገመዱን ከእጇ መልቀቅና ከመጎተትም ማቋረጥ የለባትም፡፡ የፈለገውን ያህል ጊዜ ይወስዳል እንጂ ግብጽ ተጎትታ በኢትዮጵያ ፈቃድ ሥር ማደሯ አይቀርም:: ብቻ መንግሥት ገመዱን አጥብቆ ይያዝ!››
ይህንኑ ነው ደግሜ ደግሜ የምናገረው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ እምቢ ብሎ  ከተሞላ በኋላ፤ ግብጽ ገበሬዎቿ ውኃ በቁጠባ እንዲጠቀሙ እየመከረች መሆኑ እየተዘገበ ነው፤ እሰይ! ማሸነፍ አንድ አለ እንበል!!!
በነገራችን ላይ ሱዳን ሰሞኑን ለአፍሪካ ኅብረት ባቀረበችው የድርድር ሃሳብ፤ ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ ውጭ ሌሎች ግድቦችን እንድትገነባ እውቅና እንዲሰጣት መጠየቋን “ግብጽ ኢንዲፔንዳንት” የተባለው ጋዜጣ በሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትሙ ዘግቧል:: ኢትዮጵያ እንደምታጠናው ለአፍሪካ ኅብረት መጠቆሟ የተመለከተው ይህ ሃሰብ፣ ኢትዮጵያ ትቀበለዋለች ተብሎ ባይታሰብም  የታችኛዎቹ አገሮች በሕዳሴው ግድብ ላይ  አሰተዳደር ሚና እንዲኖራቸው ይጠይቃል። ግብጽ ደግሞ ታሪካዊ የውኃ መብቷ ከማስከበር ውጭ እንደማታስብ  ተያይዞ መዘገቡ ይጠቀሳል፡፡
ግብጽና  ሱዳን ከሰሙ የምንነግራቸው፤ ከገንዘብ አቀም በስተቀር ኢትዮጵያ ወንዞችዋን ለማልማት የሚከለክላት ምንም ነገር የሌለ መሆኑን ነው።


Read 1148 times