Sunday, 26 July 2020 00:00

ዓባይ አቢይ፣ ዓባይ ግዮን

Written by  በአዲሱ ዘ.
Rate this item
(2 votes)

        “እኛ አባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም፤ የውጭ ሀገራት ደግሞ አባይን ለመገደብ እርዱን ብንል ግብጥን ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡                             ቀጣዩ ትውልድ ግን በራሱ ንዋይ (ገንዘብ) ይገነባዋል፡፡ ጥናቱ በክብር ይቀመጥ!” ቀ.ኃ.ሥ
                               
            የምድረ ግብጽ የሥነ-መንግሥት መርህ ሃይማኖታዊ ካባ የደረበ ነው፡፡ ይህ ካባ ግን ከዘመን ዘመን መልኩንና ቅርጹን እንዳሻው የመለዋወጥ መብቱን አስከብሮ ኖሯል፡፡ ጥንታዊት ግብጽ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ሃይማኖታዊ ቀኖናን እንደደነገጉ የሚታመንባቸው ፫፻፲፰ ሊቃውንት ጠርታ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር አባዊ (Patriarchy) ሥልጣን እንደተሰጣት አሳምና ትኖር ነበር፡፡ ከአራቱ ወንጌላውያን መናብርት አንዱ የቅዱስ ማርቆስ መንበር መቀመጫውን በአሌክሳንደርያ ሲያደርግ፣ ከአራቱ አፍላጋት አንዱ አባዊ ወንዝ ደግሞ መንበሩ ያለበትን ምድር እንዲያለማ ተቀየሰ፤ ተገደበ፡፡ ይህን ኃላፊነት በታማኝነት የሚመሩ “ማደንዘዣ መርፌ” የሚወጉ ግብጻዊ አቡኖች ኢትዮጵያውያንን በበላይነት መሩ፡፡
“ከሣቴ ብርሃን ሰላማ፣ ብርሃነ አዜብ!” የተሰኘ ማዕረግ የደረቡ አባቶች በኢትዮጵያ አገለገሉ:: ሣልሣዊው ሰላማ እንደ አባትነቱ የሰላም ምንጭ መሆን ሲገባው ደጃች ውቤንና ራስ ዐሊን አዋግቶ፣ እሱ ግን ሰላሙን ይዞ በጎንደር ሲኖር “በሣልሣዊ ሰላማ ይደርሳል የቀን ጭለማ!” የሚል ንግር ተሰምቶበታል፤ በዘመኑም የቀናች ሃይማኖት ትጠፋለች ተብሎ ተተንብዮአል፡፡ ሣልሣዊ ሰላማ ከአባትነቱና ከስሙ የሚጠበቅ ዕውቀትና ጥበብ አለመያዙ፣ ፬፻ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ሃይማኖታዊ ክርክር ላይ ተረጋገጠ፡፡ ባስተርጓሚ ቃሉን ያሰማው አቡን፤ ውርደትን በኢትዮጵያዊው አለቃ ዓሥራት አማካይነት ተከናነበ፡፡ ይህ አቡን ለ፯፻ ዓመታት ሆድ ያባው የግብጦች ምስጢር/ሴራ/ሸር ለአደባባይ እንዲወጣ ምክንያት ሆነ፡፡
አባዊ የሚለው ቃል ትርጉሙ ያባቶች መሐላና ቃልኪዳን ማለት ሲሆን፣ አንድም ጥቁር አባይ ታላቅ፣ ፈሳሽ፣ ጎርፍ፣ ማዕበል ማለት ነው:: ይህም ቀዳሚነትን፣ በኩርነትን የሚገልጥ ተምሳሌታዊ የማዕረግ ስያሜ ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን መክፈት፣ መግለጥ፣ ማብራት፣ መንገር፣ ማውጣት፤ ብርሃንን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብን፣ እንቆቅልሽን፣ ፈሊጥን፣ ቅኔን፣ ድንቁርናን ወዘተ ለሚያከናውን መሪ የሚቀጸል ማዕረግ ሲሆን፣ ሰላማ ደግሞ ሰላማዊ፣ የዕርቅ የፍቅር፣ የይቅርታ ሰው ማለት ነው፡፡ ብርሃነ አዜብ ማለት የጥቁሯ ደቡባዊት ንግሥት ብርሃን፣ (ቡርሃን በዐረቢ) አብነት፣ መምር፣ ተርጓሚ፣ ተንታኝ፣ ፈካሪ፣ ገላጭ፣ አስረጅ አካል መጠሪያ ነው፡፡ የዚህ ተምሳሌታዊ ፍቺ ኢትዮጵያ በጊዜው በዕውቀት አልባዎች የተመላችበትን የጭለማ ዘመን ውስጥ መዋለሏን ይወክላል፡፡ እስከ ዘመነ-መሳፍንት ድረስ የርስ በርስ ጦርነት በባዕድ አባት ተባርኮ የሚቀጣጠልበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚህን ወቅታዊ ዐውድ ከሚገልጡ የኢትዮጵያ አባቶች አንዱ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ናቸው፡፡ አለቃ ባንድ ዘመን የሚከተለውን ተናገሩ፡፡ “ያገራችን ፊደል ራሱን የቻለ ነው፡፡ ሀገራችንም እንደዚሁ በማዕድን፣ ባትክልት በንስሳ ራሷን የቻለች ናት፡፡ በውቀትም ራሷን የምትችልበት ጊዜ ይመጣ ይኾናል፡፡ ልጆቿም ርስ በርሳቸው ካልተጣሉ በቀር በወንድነት ራሳቸውን የቻሉ ናቸው:: ጠላታቸውም ሁልጊዜ ተስፋ የሚያደርገው ርስ በርሳቸው መጣላታቸውን ነው፡፡ የጥሉም መሠረት መደበኛው ሃይማኖት ይባላል፤ (1928ዓ.ም.)፡፡”
አለቃ የግብጽንና አጋር ሀገራትን ለምሳሌ ሮማ፣ ግሪክ፣ አርመን ሴራ በሕይወት ዘመናቸው ለ፳፪ ዓመታት ያህል በእሥራኤል ሀገር የኢየሩሣሌም ከተማ በዓይናቸው አይተዋል:: ጥናትና ምርምር አድርገው ግብጽና አጋሮቿ የኢትዮጵያን ገናነት የሚያወሱ ቁሳዊና መንፈሳዊ ጥሪቶችን መቀራመታቸውን በቁጭት ይገልጻሉ:: በዚህም ግብጽ አባዊ ሥልጣንን በእጇ ስታደርግ፣ አንድም አባት ማለት የሀገር ደንብ፣ አገባብ፣ ሥርዓተ-ሕግ፣ የዕድር ውል ሰነድ ማለት ነውና (ፍትሐ ነገሥትን/ፍ.ነ. እና ሌሎች ማጣቀሻዎች በሃይማኖታዊ አገልግሎት) ስም በሀገሯና በዐረቢ ቋንቋ ጽፋ ለኢትዮጵያ ሰጠች:: ይህ ሰነድ ከዐረቢ ወደ ግእዝ ተተርጉሞ በአፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን ወደኢትዮጵያ ገባ፡፡ ሰነዱ በተቻለው መጠን አባይ የምድረ-ግብጽ ሲሳይ ሆና/ኖ እንዲያለማ ያደረገ የውሃ አጠቃቀም ደንብ ይዟል፡፡ በዚህም አባይ የምድር አላባዎችን ሁሉ እያግበሰበሰ በረሃማውን የግብጽ ምድር ሲያለመልም፣ እኛ የአባይን ዳር ድንበር ለወንበዴዎችና ዘራፊዎች፣ ለባሪያ ፈንጋዮች ቀጠና አድርገን ስሙን ስናጠለሽ፣ በግብጽ ቤት ግን ሠርግና ምላሽ ነበር:: አባ ገብርኤል የተሰኘ የፍትሐ ነገሥት ጸሐፊ የሴራውን መሪ ሰነድ አስገኘ፡፡ ይህም “ጥቁር አያጰጵስ!” ብሎ ደነገገ:: የግብጽ መንግሥታት ያባይን ዳር ድንበር የሚገዙ የኢትዮጵያ ሰዎች ውኃውን በመመለስና ወደ ሌላ በማፍሰስ ግብጽን እንድትራብና እንድትጠማ ማድረግ የሚቻላቸው ስለሆነ ከነገሥታቱ የሚገባቸውን ጉርሻ እየተሰጣቸው ኖረዋል፡፡
ፍ.ነ. የኢትዮጵያ አባቶች ከግብጻዊ አባታቸው በማዕረግ የበታች ሆነው ማገልገል እንደሚገባቸው ይወስናል፡፡ ይህ ሰነድ የግብጽን ሥጋዊ ፍላጎቶች ለመሙላት የተሰናዳ ግን መንፈሳዊ ካባ ደርቦ ወደ ሀገር የገባ ነው፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በአንቀጽ 37 “ስለመከራየትና ስለአከራይ” (ስለውለታዎችና ስለአዋዋይ ይናገራል) ይህም 1179ኛው ንዑስ ክፍል ስለ ውሃዎችና ስለ ቆላ ምድር ሰዎች መብትና ግዴታ ያትታል፡፡ ለደገኞች ወንድሞች ውሃቸውን በማሳመር መስደድ በግድ የሚገባቸው ነው፡፡ ለቆለኞችም የደገኞችን የምድር ተድላና የሆነውን ድልብዋን በመቀበላቸው ስለዚህ ጥቅም ፈንታ ለውጥ አለባቸው፡፡…በተውሶ የሄደ ገንዘብ ሰላሳ ዓመት ካለፈው የተዋሹ ንብረት ነው፡፡ …በ1190 ንዑስ ክፍል ደግሞ አንዱም ከእርሱ የተነሳ የጎረቤቱ መጎዳት የሚመጣበትን ማናቸውንም አያድስ፡፡ የሚገባውን የማይሰራበት አግባብ ሁሉ ዐሥር ዓመት ያህል ነው፡፡ የተሰመረባቸው ዓረፍተነገሮች ወደግብጽ ጥቅም ያደሉ ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡
ግብጽ ከላይ የቀረቡ የማሰሪያ ድንጋጌዎችን በአባ ገብርኤል በኩል ስታቀርብ “ተጠማኝ/ጭሰኛ ቢሰነብት ባለርስት ይሆናል!” በሚለው የሀገሬው ብሒል ያመነች ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ደገኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ለቆለኛዋ ግብጽ ውሃዋን በመስመር የመልቀቅ ግዴታ ተጥሎባታልና፡፡ እንዲሁም በተውሶ አባይ ግብጽን ማጠጣት ከጀመረ ከሰላሣ ዓመት በላይ ከማስቆጠሩ አልፎ ኢትዮጵያ የሚገባትን ሳትሰራበት ሰላሣ ዓመት ስላለፈባት ወደ ግብጽ የሚፈሰው አባይ ንብረትነት በግብጻውያን እጅ መተላለፉን አምና ስትሰራ ኖራለች:: አምና ስትሰራ ማለት፣ አምና ስታሳምን፣ ደጋፊዎች ስታፈራ፣ ቀድሞ ከጥቁሮች ያዋገናት አላዋቂነታቸውን ተጠይፋ ከቡድን ምንትስ ሀገራት ጋር ለማበር አዋቂነታቸው ያማለላት መሆኑን ስታስረዳና ስታሳምን ኖረች፡፡  በኢትዮጵያ አማኞችና የእምነት አባቶች መካከል የሚያግባባ ቋንቋ ጠፍቶ፣ በጥቁር ምድር ያለው አባት መልኩ፣ ግብሩ፣ ቋንቋው፣ ጠባዩ ለባዕድ የሚሰራ ሆኖ ተገኘ፡፡ ቀደምት የሀገሪቱ ልሂቃን በባነኑበት ጊዜ አባት አልባ ያደረጋቸውን ሴራ ደረሱበት፤ ጊዜው በ1920 ዓ.ም. ነበር፡፡ እነዚህን አቡኖች በሀገሬው ለመተካት እልህ አስጨራሽ ድርድር ተካሂዶ (ግብጻውያን ባይዋጥላቸውም) የመጀመሪያው ጥቁር አባት ሥርዓተ ሲመት በ1951 ዓ.ም. ላይ ተከናወነ፡፡
ዘመናት ነጎዱ፤ አባይ ከመፍሰስ አልታቀብ አለ፤ ፍትሐ ነገሥቱ በሕገመንግሥት የተለወጠው በቀ.ኃ.ስ. ዘመን ነው፡፡ አባይን በፍትሐዊ ክፍፍል መገልገል የሚያስችል ያጠቃቀም ውል ዳግማዊ ምኒልክ የፈረሙት ከመቶ ዓመታት በፊት፣ ለዚያውም በሶስተኛ ወገን በኩል ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት አባይንና ሌሎች የውሃ ምንጮችን ለልማት የሚያውል ጥበብና አቅም፣ ዕውቀትና ኃይል አልነበራትምና “ውሃው በላኝ! አባይ ማደሪያ የለው…! ያባይን ልጅ ውሃ ጠማት!” የመሳሰሉትን መጥቀስ የዘወትር ልማድ አደረገች፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችና ችግሮቻችን እየባሱ እንደ ሌሎች ሀገራት ልማት ጠፍታብን ስንጫረስ፣ በግብጾች ቤት ግን ሠርግና ምላሽ ነበር፡፡
ግብጽ ጥንት የደረበችውን “ክርስቲያናዊ ጥቁር ካባ” አውልቃ፣ የምሥራቃዊ ዓረብ ሀገራትን “ኢስላማዊ ነጭ ካባ” ስትለውጥ ሃይማኖትን ለድረሱልኝ ጥሪዋ ማድመቂያ አደረገች፡፡ የግብጽም ሆነ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ትኩሳቶች ከውሃ በላይ የሆኑ ትእምርታዊ ፋይዳ መያዛቸውን ለመገመት ጠንቋይ መሆን አያሻም:: በሀገሬው ዘንድ ለሬሳ ማጠቢያ የማይከለከለው የተፈጥሮ ሀብት ተምሳሌታዊ ፋይዳ ከዚያ በላይ ነው፡፡ ይህን ለማለት የሚያበቃ መንደርደሪያ ፍንጭ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን “አባይ” በሚል ርዕስ በጻፈው ግጥም ውስጥ ይገኛል፡፡ የአባይ ተምሳሌታዊ ፋይዳ በቦታና ጊዜ የማይወሰን፣ ዝንታለማዊና ሁለንተናዊ ሚና እንዳለው ከላይ የተጠቀሰው ግጥም ያስረዳል፡፡
በዚህ መሠረት አባይ ለሀገሬው የጥበባት መፍለቂያ ምንጭ/አዘቅት ነው! “የማን ጥበብ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አባይ ጥበብነቱ ለጥቁሮች፣ ለነገደ ኩሽ ሲሆን፣ የጠቢባኖቻቸው አዋይ/ጠባቂ፣ አምባ፣ ተገን መኩሪያ ነው:: የጥቁር ዘር ብሥራት፣ ወይም የድኅነት ቃልኪዳን ዓባይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ደም፣ የዓለም የሥልጣኔ እምብርት አባይ ናት/ነው፡፡ ይህ/ቺ አባዊ/እማዊ ባህርይ አባይ-አቢይ፣ ዓባይ-ግዮን ስትሰኝ የምጥቀቷ አርያማዊነት የማይደረስበት፣ የሙታን መርዶነቷ ቅድመ ገናና ያደረጋት፣ የርሷን ያድናቆት ልክ ዓለም ጠልቆ መረዳት የተሳነው ሆኗል፤ ሆነናልም፡፡ በዚህ የተነሳ የእናት አባይ አሻራ እንዲደበዝዝ ያደረጉ የባዕዳን ጩኸቶች (ትላንት)፣ ያላዋቂ ሁከቶች (ዛሬ) ተደበላልቀው ጋርደዋታል፡፡ እናም አባይ እንቆቅልሽ፣ ቅኔ፣ ፈሊጥ ሆና ሳትፈታና ሳትተረጎም ኖረች፡፡ ስለዚህ እንቆቅልሽ የሆነችን አባይ ለመፍታት፣ ለመተንተንና ለመፈከር ከሆሄ መጀመር ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ጭምር ነው፡፡ ስሞቿም አባይ-አቢይ አባይ-ግዮን ወይም/እና ዓባይ አቢይ፣ ዓባይ ግዮን ናቸው፡፡
ግብጽ በዘመናት ልዩነት በደረበቻቸው መንታ የእምነት ካባዎች፤ የመርህ ተገዢ ሆና እውነተኛ መንፈሳዊ ተልዕኮን፣ አገልግሎትን፣ ወዘተ ለማሳካት ብትሰራ ኖሮ “የማን አባቱ ገደል ገባ!” የሚሉ ከሽምግልናና ከዕርቅ የራቁ አባቶችን መርጣ አታሰማራም ነበር፡፡ የግብጽ ዓላማ አባይ የያዘውን የጥቁር አፍሪካ የሥልጣኔ አሻራ/ማኅተም፤ “የእኔ፣ የግሌ፣ የብቻዬ!” ብላ መድመቅና በወዳጅ ሀገራት ዘንድ ዕውቅና ማግኘት ነው፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ በብዙ ቢላዋዎች መብላት ሳይሆን ማባላትን በምድረ-ኢትዮጵያ የሚተገብሩ አቡኖች አሰማርታ ኖረች፡፡ ለአብነት ያህል ቅድመ-ብሉይ ኪዳን፣ ዘመነ ብሉይ ኪዳን፣ ዘመነ ሐዲስ ኪዳን፣ ቅዱስ ቁርአን ወዘተ መጥቀስ ብቻ ሳይሆን መጻፍና መተርጎም ሳይሳናት የየእምነቶችን መሠረታዊ መርህ የሚጥሱ ተግባራት ለመፈጸም እንዲያግዙ ተባባሪዎቿን የማሰማሪያ ጥሪ ጩኸታችንን ቀምታ ታስተጋባለች፡፡ (ከሚያባሉ ወዳጅ ሀገራት የቀሰመችው ልምድ ቀላል ባይባልም) ስለዚህ በምታነሳቸው እምነት ተኮር ማጣቀሻዎች፣ ቀደምት የሥልጣኔ አሻራዎች፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍት፣ መጻሕፍተ ባልቴቶች፣ የስምምነት ውሎች፣ ለርሷ የሚያደሉ አንቀጾችን ዘወትር ማነብነብ መለያዋ አደረገች፡፡
የኢትዮጵያውያንን የቤት ሥራ ፈታኝ ካደረጉ፣ የግብጽን ግን ካቃለሉ ታሪካዊ እውነታዎቻችን መካከል የግብጽ ምሁራን፣ ሥነ-መንግሥታት፣ ማኅበረ-ባህላዊ ተቋማት ወዘተ --- ለሀገር በሚበጁበት የቀዬው ቋንቋ በማስተማር አዋቂዎቿ እንዳይባክኑ ሰርታለች፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ምሁራን፣ መንግሥታት፣ የትምህርት ሥርዓቶች፣ ወዘተ ሀገራቸውን ጥለው፣ ለሌሎች የሚሰሩ ምሁራንን፣ መንግሥታትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ጸረ-አባዮችን ወልዶ ለማሳደግ የውጭ ሀገራት ቋንቋን መረጠች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግብጽ ታላላቅ የዓለም ሀገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ ለዘመናት የውጭ ግንኙነት ሥራዎቿን ስታስፋፋ፣ ሀገራችን ግን የውጭ ግንኙነት ሥራን ከቤተ መንግሥት ዓይን እንዲገለሉ ለሚደረጉ ግዞተኞች ሰጥታ፣ ከልባቸው እንዳይሰሩ ዲፕሎማሲያዊ ሚና በግዞት ሕይወት እንዲታሰብ አደረገች፡፡
አባይ ከወንዝ በላይ የጥቁሮች ሁለንተናዊ ተምሳሌት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የግብጽ አቡኖችን ሥልጣን አልባ እንዳደረጉ ሁሉ አባይ የበቀለበትን ቀዬ እንዲያለማ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱት በቀ.ኃ.ሥ. ዘመነ-መንግሥት ነው፡፡ ቀ.ኃ.ሥ. የሀገሬውን አቅምና የግብጽን አቅም በማመዛዘን ሲገልጹ፤ “እኛ አባይን እንገድብ ብንል አቅም የለንም፤ የውጭ ሀገራት ደግሞ አባይን ለመገደብ እርዱን ብንል ግብጥን ላለማስቀየም ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ግን በራሱ ንዋይ (ገንዘብ) ይገነባዋል፡፡ ጥናቱ በክብር ይቀመጥ!” የሚል ተስፋ አዘል መልዕክት አኖሩልን፤ ይህ ዓይነት ሀገራዊ ዓላማ በጊዜው እንዳይሳካ ከውጭም ከውስጥም መሰናክሎች ሲጋረጡ ቆይተዋል፡፡
እንደመታደል ሆኖ አባይ የተመረጠው ለኃይል ማመንጫ ግድብ መሆኑም የግብጽን ተቃውሞ አባባሰ፤ ይህ በራሱ በኃይል ብርሃን፣ በወጋገን፣ በዕውቀት፣ በሥልጣኔ፣ በጥበብ፣ በፍልስፍና ወዘተ ተምሳሌት የቆመ መሆኑ ግብጻውያንን በስጋት አዘቅት ውስጥ ጣለ፡፡ ዕውቀት ዳር እስከ ዳር ባልተዳረሰበት ዘመን ዕውቀቷን በልቧ ይዛ ሀገራችንን ስትመራ የቆየችው ግብጽ፣ አሁን ደግሞ ዕውቀት በቀላሉ በሚገኝበትና ጥጋ ጥጉን ባዳረሰበት ዘመን፣ ዕውቀትማ የሥልጣኔ በኩርነትማ፣ የኃይል ሚዛን የበላይነትማ ያለ እኔ፣ ያለ አባት ልማድ ብላ ከቆመችበት የማዕረግ  መንበር ለአፍታም ቢሆን ወርዳ ለመደራደር የፈቀደች አትመስልም::
ግብጽ የአስዋን ግድብን ለአስራ አንድ ዓመት ያህል ገንብታ ያጠናቀቀችው በ1962 ነበር፡፡ አትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ከራሷ የውሃ ምንጭ የኤሌትሪክ ኃይልን ለማመንጨት የተነሳችው ከግብጽ 41 ያህል ዓመታት ዘግይታ ነው፡፡ ለዚያውም የፕሮጀክቱ መጠሪያ አንዱንም የቀዬ ስም አልመረጠም፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፈረንጆች አፍ (Great Ethiopian Renaissance Dam) ይሰኛል፡፡ ይህን ስም የያዘ ውሃ ገንብተን ለመጨረስ እነሆ ዘጠኝ ሙሉ ዓመታት ቆጠርን፡፡ የሀገራችንን የሕዳሴ ግድብ ባምስት ዓመት ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት ግንባታው ቢጀመርም፣ ውስጥ ውስጡን በአምካኝ ሴራዎች እየተጠለፈ በአንዳንድ ቋጣሪዎች ሲቋጠርብን! ወደ ኋላ ሲያስቆጥሩንና ሲቆጥሩብን ዘጠኙን አገባደን ወዳስረኛው ገባን፡፡ አባይ፣ ዓባይ፣ ግሽ አባይ፣ ግዮን፣ ወይም…ናይል በሚሉ ስሞች ይጠራል፡፡ አባይ የሚጠራባቸው የግብር፣ የባህርይና የነገር መግለጫ ስሞች ቀዬአዊ፣ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ ብሎም ዓለማቀፋዊ ወሰንን ያካልላሉ፡፡ በአራቱ ቃላት የሚገለጸው የስሙ ትርጉም (ቃላቱ በተናጥል ወይም በጋራ የያዙት ፍቺ ሲተነተን) ወንዙ ከያዘው የታላቅነት ልዕልና ማዕረጉ የሚያሳንሱት አይደለም፡፡
“አባይ-አቢይ አባይ-ግዮን ዓባይ አቢይ፣ ዓባይ ግዮን” መታወቂያው የሆኑለት የወንዝ አባትና እናት መፍለቂያ ምንጩ ምድረ-ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህ/ቺ ወንዝ የዘፍጥረትን ታሪክ እንዲያስቡ ያደርጋል/ታደርጋለች፡፡ ገነትን ከበው ከሚያጠጡ ካራቱ ታላላቅ የውሃ አባቶች/አድባራት መካከል አንዱ/ዷ ናት/ነውና ፈለግ አባዊ ተባለ/ች፡፡ አባይ-አቢይ በሚሉ ቃላት ቅንጅት ሲጠራ  የውሃዋን ውፍረት፣ ግዝፈት፣ ደንዳናነት መለያዋ የሆነላት የተፈጥሮ አካል ይገልጻል፡፡ በሌላ ፍቺ ደግሞ አባይ-አቢይ ዕድገቷን፣ በላጭነቷን፣ ታላቅነቷን፤ የክብር ደረጃዋን፣ የልዕልና ማዕረግዋን ክብደት ያሳያል፡፡ በዚህ ምክንያት አባይ-አቢይን ንብረት ማድረግ ከኃያላን ሀገራት ተርታ የሚያሰልፍ፣ ጽናት፣ ብርታት፤ ብዛት፣ ብርካቴ፣ ክብደት፣ አለመለየትን ያመለክታል፡፡  
አባይ ዓባይ ተብሎ ሲጠራ ደግሞ የውሃ አውራነቱ፣ ታላቅነቱ፣ ገናናነቱ፤ ብርቱነቱ፣ ብዙነቱ፤ ፍጹምነቱ ልዕልናው፣ ከፍታው፣ ብልጫው፣ ክቡርነቱ ይመለከትበታል፡፡ ዓባይ በራሱ አካላዊ ቁመና ብቻ ገዝፎ አይታይም፤ የሚፈስባቸው የሚጓዝባቸው የመልክዓምድር ወሰኖችን  በሙሉ ሀብታቸው በመሆኑ አድገው፣ ከፍ ከፍ ብለው፣ ልቀው፣ በልጠው፣ ከብረው፣ ኮርተውና ተጓደው እንዲታዩ የሚያበቃ ግርማ ሞገስን ይደርብላቸዋል፡፡ በዚህም ዓባይ መታበያ፣ “እኔ እበልጥ” መባባያ ተገን ትሆናለች::
ግዮን የሚለው መጠሪያዋ ውሃዋ ከምትፈልቅበት ውስን  ምድር፣ እንዲሁም የእንቅስቃሴ ሁኔታ አንጻር የተሰጣት መለያ ነው፡፡ ግዮን የምድረ-ኩሽ ሕዝብ ያንድነት ዜማ ይፈልቅባታል፡፡ የዜማ ቃናዋና ለዛዋ ከፏፏቴ ስትወርድ፣ መስኩን፣ ሸለቆ ሸንተረሩን ስታቆራርጥ የምታሰማው ድምጽ፣ ወይም ተመማ፣ ጩኸት፣ ድንፋታ፣ ቁጣ፣ ማጉረምረም፣ ዝየራ፣ ሙሾ ወዘተ መግለጫ ነው፡፡ የውሃዋን ብዛት፣ ስፋት፣ ምላት፤ ኃይል አዘል ርምጃ ማለትም የጩኸቷን ግርማ ሞገስ፣ የፏፏቴዋን ተዋረዳዊ ፍሰት፣ ነጎድጓዳማ የማዕበል መልክ በጆሮ በማስደመጧ የተሰጣት ነው፡፡ እናት ወንዛችን ከገባሮቿ ጋር ሆና በጋራ መላ ግብጽን ከላይ እስከ ታች አጠጥታ፣ አጥግባ፣ አርክታ፣ አረስርሳ፣ ዐልፋ ተርፋ ወደ ስሜን ጎርፋ ከሜዲትራንያን ባሕር ትገባለች፡፡
የግእዙ አቢይ በዐረቢ አበይ ይሰኛል፤ ይህም እንቢታና ተቃውሞን ገላጭ ቃል ነው፡፡ አበያ እንቢተኛ በመሆን፣ በመጓደድ፣ የታዘዘውን የለመኑትን ባለመቀበል የሚታወቅ ባህርይ መግለጫ ቃል ነው፡፡ ይህም አለመስማት፣ አለማድረግ፣ እሺ በጎ፣ ይሁን አለማለትን፣ አመጸኝነትን ያሳብቃል፡፡ ዐረቢ ትልቅ የሚለውን ቃል ከቢር፣ አክባር፣ ’ረዚም (ረዥም ይመስለኛል?) ብሎ ይፈታዋል፡፡ ታላቁ ማለት ነው በሀገሬኛ/በሀገሬው፡፡ ከላይ የቀረቡ ሐተታዎች የወንዙን ታላቅነት፣ አባትነት፣ ቀደምትነት፣ እናትነት ወዘተ ገላጭ ናቸው፡፡ ግን እንደ ስሙ እያከብርን፣ ታላቅነቱን እያወጅን፤ ባለቤት መሆናችንም የታላቅነት ግርማ ያላበሰን መሆኑን አልተናገርንለትም፤ በተለይ በዚህቺ በእኛ ጊዜ፡፡
ግብጽ “ሰሚ ነው እንጂ ተቸጋሪ
ደንቆሮ መልካም ኗሪ”
በሚል ጆሮዎቿ እንዳይሰሙ፣ ዓይኖቿ እንዳያዩ ያሰናከለቻቸው ይመስላል:: ለዚህ አብነት የሚሆነው ሕገ-ደንቦች እንደሚያረጁ፣ እንደሚታደሱ፣ ለውጥ/ማሻሻያ እንደሚደረግባቸው የተረዳች አለመምሰሏ አንደኛው ነው፡፡ ወይም እንዲገባት አለመሻቷ ለድርድር የሚሆን ቅን ልብ ማጣቷን ያሳያል፡፡ በነገር ሴራዎች ሰክራ የሰነበተችው ኢትዮጵያም ስካሯ ሲለቃት ራሷን ማደስ፣ መቆነጃጀት፣ ማልማት አማራት፡፡ ሕዳሴ አዲስ በመሆንና በማድረግ፣ በማደስ፣ በመታደስ፣ በአስተዳደስ፣ ጥቅምንና ፋይዳን ማራዘም ማለት ነው:: ፍቺውም ማንሰራራት አዳዲስ ፍላጎቶችና ዝንባሌዎችን መፍጠርና መተግበር ይይዛል:: የኋልዮሽ መመለስንም ሊጨምር ይችላል:: ይህም መወለድ፤ መብቀል፣ ማደግ ሕዳሴ ይሰኛል፡፡ ግድቡ ወይም ግድባችን ደግሞ ውሃን ከማቆር አልፎ ገንዘባችን፣ ልባችን፣ ቀልባችን፣ ሀሳባችን፣ ንብረታችን፣ ልጆቻችን፣ መንፈሳችን እየታቆሩበት የለማ ላዕላይ መልኩ የውሃ ማገጃ፣ መቋቻ፣ መዋኛ ጥልቅ ቦታ ሲሆን፣ በሌላ በኩል መደኋላ ማገድ፣ ማቋት አዲስ ሕገ ደንብን በማበጀት ወደተግባር በመግባት ይቋጫል፡፡
አባይ ብሎም ዓባይ አባት አደግ ወንዜ፣ ሀብቴ፣ አካሌ፣ ቁመናዬ ብሎ መጠየቅ የባህርይ ወገንን በኀሠሣ ማግኘት ነው፡፡ ከዚያ በላይ ሊያስመኩና ሊያኮሩ የሚያበቁ ተምሳሌታዊ ዋጋዎች አባይ አዝላለች፡፡ የሕዳሴው ግድብ ሀገርን ወደአዲስ የተሻሻለ ገደብ፣ ወሰን፣ ዳር ድንበር፣ መዳረሻ ልክ መርቶ ያደርሳል፡፡ ግድብ የገደብ ምንጭ፣ የዕድር ሕግና ደንብ፣ የሥነ-ዐዳር መመሪያ ውል ነው፡፡ ግድቡ የኃይል ማመንጫ፣ የብርሃን ማፍለቂያ፣ ጭለማን ወደ ብርሃን ማሸጋገሪያ፣ ድንቁርናን ማጥፊያ ወዘተ ዋጋዎች አሉት፡፡ የዓባይ ውሃ መማሪያ፣ መፈወሻ፣ መሸጋገሪያ ፋይዳውን በግብጽ አባቶች ለረዥም ዘመናት ተነፍገን ኖረናል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከጥቁርነት ጋር የተያያዘ የሥልጣኔ አሻራ ይገልጽ ዘንድ አባይ-አቢይ አባይ-ግዮን፣ ዓባይ አቢይ ዓባይ ግዮን በሚል ልዕልናውን፣ የማዕረግ ደረጃውን፣ ጠሊቅነቱን፣ ምጡቅነቱን የሩቅነቱን የሚያሳዩ ፍንጮች ናቸው፡፡ እግረመንገድ ለማስታወስ ያህል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በተንቀሳቃሽ ስልኮች የሚልካቸው መልእክቶች ከአባይ የልዕልና መንበር የማይተካከሉ አሳናሽ መሆናቸውን ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም:: ይህን ለማለት ያበቁ ምሳሌዎችን በተገቢው ጊዜና ቦታ በመጥቀስ መወያየት ያሻል፡፡
አባይ የተሰኘው የባለቅኔው ግጥም በ1964 የተጻፈ ነው፡፡ አስዋን ግድብ ከተጠናቀቀ ሁለት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ መታሰቢያነቱም በሀገሬው የጥበብ ጓዳ በመምነሽነሽ ዘመናቸውን ላገባደዱት ለአለቃ አስረስ የኔሰው ተበርክቷል:: ግብጽ አባይን ትገድብ ዘንድ አስቀድሞ አራት የሥልጣን መናብርት ተፈጥረው ባንዱ እንድትቀመጥበት ተደነገገ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ግብጽ በነካካው እጇ ካራቱ ዐበይት ወንዞች አንዱን ጠለፈች፡፡ ግን ይህ ምስጢር የተጋለጠው በአራት መቶ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ፊት ሆነ፤ አራት መቶ ወይም አራትነታቸው ምሉዕ በኩለኼ ሥልጣን እንዳገኙ የሚገልጽ የብድር መክፈያ ጽዋ ነው፡፡ በአራቱ መናብርት ስም የተወሰደብን ሥልጣን በአራት መቶ ሊቃናት መናብርት ጉባኤ ማርከን መመለሳችንን ያውጃል፡፡ የሣልሣዊ ሰላማ “ባዶ ማድጋነት” የታወቀው በአለቃ ዓሥራት የክርክር መርቻ ጭብጥ ሆነ፤ በዚህም አባትነት አስታራቂነትን ከጥበብ ጋር አዋሕዶ በመያዝ ይገለጣል፡፡ በጥበብና ዕውቀት መራቀቅ ሌላ የዕውቀት አድማስን የሥልጣን መንበርን፣ የማዕረግ ደረጃን ያስገኛል፡፡ ዕድሜ ለአባቶቻችን! ይህም ያለ ፋይዳ አልነበረም፡፡
የግብጾችን ሴራ (ላዩ ዳባ ውስጡ ደባነት) ኢትዮጵያ ለመረዳት/ለመባነን ሰባት መቶ ዓመታት ፈጅቶባታል፤ ወይም በእንቅልፍ ውስጥ ነበረች፡፡ ሰባት፣ ሰባ፣ ሰባት መቶ፣ ሰባት ሽህ ላንድ ተመሳሳይ ዓላማ የሚመረጡ ፍጹም ቁጥሮች ናቸው፡፡ ፋይዳቸውም የብድር መክፈያ ጽዋዕ ሙላትና ጉድለትን ያሳያሉ፡፡ ብድር በምድር የሚመልስባቸው ቁጥሮች አራት፣ አርባ፣ አራት መቶ ወዘተ ወኪል ናቸው፡፡ አለቃ ዓሥራት ደግሞ የሰባት መቶ፣ የሰባ እና የሰባት ተምሳሌት ናቸው፤ ይህም ግብጽን “ያንቺ ጽዋ ሞልቷል! ኢትዮጵያውያንን ያጠጣሻቸውን የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈረቃው ወዳንቺ ዞረ፤ አንቺም እስቲ ተጎንጭ!” የሚል መልእክትን ለመናገር የታጩ አብሪ የሀገር ልጆችን አባይ-አቢይ ዓባይ-ግዮን ወልዳ አሳድጋለች፡፡
ይህ የሕይወት ዑደት ወይም ፈረቃ ይባላል፡፡
“ማነሽ ባለ ሳምንት?
ያስጠምድሽ ባስራ ስምንት” ያለው ግብጻዊው ሙሴ ነው፡፡
“እኔ ነኝ የአባይ-አቢይ ዓባይ-ግዮን ወዳጅ” ብላ ለመመረቅ ጎንበስ ያለችው ኢትዮጵያም ባለ ሳምንት ናት፡፡Read 2499 times