Saturday, 25 July 2020 15:57

የዋልድባ መነኮሳትና የሕውሓት ትግል ከትናንት እስከ ዛሬ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ሕውሓቶች የመንግስትን የሥልጣን ወንበር ባልተገባ መንገድ ከተቆጣጠሩ በኋላም ሆነ ገና በርሃ በሽፍታነት ሙያ ሳሉ ጀምሮ፣ እንደ ዋልድባ ገዳም መነኮሳት መራር የሆነ መንፈሳዊ ትግል ያጋጠመው ሌላ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከዚህ ቀደም ባየናቸው የምስክርነት ቃልና ከአንዳንድ አፈትላኪ ሰነዶቻቸው መታዘብ እንደሚችል፤ ሕውሓት ዋልድባ ገዳምን  ምን ያህል በጥላቻ ዓይን ይመለከተው እንደነበርና በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ የዘለቀ ግፍና በደል የተፈፀመበትና እየፈፀሙብን እንደሆነ ለማወቅ ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም:: የዘወትር ሮሮአችንን መንግስትና ሕዝብ ሲሰማሙ ኖሯል፡፡ እየጠሉንም ቢሆን እየሰሙን መሆኑ ሀቅ ነው፡፡
በዋልድባ ገዳምና በሕውሓት መካከል ለዓመታት የዘለቀውን ጠብ፤ እጅግ ውስብስብና ፈታኝ ካደረጉት ምክንያቶች በዐቢይነት ከምንጠቅሳቸው ጉዳዮች መካከል፡- የቤተ ክህነት ሰዎች በፍራቻ፣ በዘረኝነት፣ በስልጣንና በጉቦ በመደለል፤ ገዳሙ አንዳች አይነት በደል እንዳልደረሰበት አድርጎ በየቴሌቬዥን መስኮቱ ላይ እየወጡ በሃሰት መመስከራቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዓለም በቃኝ ብለው የመነኑ ምስጉን መነኮሳትን ማሸማቀቅና ማሳደድ ነው:: ለዚህ እኩይ ድርጊት እንዳንድ የሲኖዶስ አባላት፤ የቤተ ክህነት ሰራተኞች፤ አድር ባይ መነኮሳት ዋነኛ ተባባሪዎች ነበሩ፡፡ ናቸውም:: ከዚህ ባሻገር በሕዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችም የገዳሙን ጥፋት አስመልክተው ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ለኅብረተሰብ  ከማሰራጨት ይልቅ የአንድ ቡድን ልሳን በመሆን፤ ይባስ ብለው ስለ ገዳማቸው ተቆርቋሪ የሚባሉ መነኮሳትን ለማሸማቀቅና ‹‹ገዳሙ እየለማ ነው›› የሚል ዘጋቢ ፊልም እየሰሩ ማሳየታቸውን ለታዘበ አገረ እግዚያብሔር ኢትዮጵያ ወደ የት እየሄደች እንደሆነ በእውነቱ ለማሰብ ያስቸግራል፡፡
በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር የእውነተኛ ገዳሙ መነኮሳት ትግል ከመጀመሪያው ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለፉበትን አጠቃላይ ሕጋዊ ሂደትና ያጋጠሟቸው ፈተናዎች ከነማስረጃዎቹ ጋር የምናቀርብ ይሆናል:: ምን አልባትም ገዳሙ ታረሰ፤ የመነኮሳት አጽም ፈለሰ፤ የገዳሙ ደን እየተጨፈጨፈ ስራ አጥ በሚል የተደራጁ ወጣቶች እያከሰሉት ነው፤ ስለ ወርቅ (ቆፋሪ) ለቃሚ ወጣቶችና  መቀር መቃሪዎች፤ ስለ ዛሬዋ ወንዝ ግድብና  የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት (ፋብሪካ)  ግንባታ ብሎም የዓለማዊ ሰዎች ሰፈራን፤ ብዛት ያላቸው ከብቶች ወደ ገዳሙ መግባትና ደን ማውደም በተመለከተ የተለያየ መረጃና ግንዛቤ ላላቸው ሁሉ፤ መሬት ላይ ያለውን እውነት ትረዱት ዘንድ እያንዳንዱን ሰነድ እንደ አስፈላጊነቱ ቃል በቃል የምናሰፍር ይሆናል፡፡
ሦስትና አራት ዓስርት አመታትን ለፈጀው የገዳሙና የሕውሓት ትግል  (ባለፉት ምዕራፎች ለማየት እንደሞከርነው) ዋነኛው ምክንያት፤ የወያኔ አፈጣጠርና ሃይማኖታዊ ጥላቻው ጫፍ መርገጡና ዘርን መሰረት ያደረገው ዘመን አመጣሹ ብሔር ተኮር ጥላቻ በዐቢይነት የሚጠቀሱ ናቸው:: በመሆኑም በእኛና በወያኔ መካከል ችግር የተፈጠረው ገና በርሐ ላይ እያሉ እንደሆነ ደጋግመን ተናግረናል፤ ይመለከተዋል ላልነው ተቋም ሁሉ አቤት! ብለናል፡፡
ዋልድባ ቅድስት፤ በመላው ኢትዮጵያ አውራጃዎች የሚኖሩ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ይህን ከንቱ ዓለም ንቀውና ተጠይፈው ጸብዐ አጋንንትንና ግርማ ሌሊትን ታግሰው በፆምና በፀሎት ተወስነው፤ አምላካቸውን በማመስገን፤ ከሕዝባቸውና ከአገራቸው አልፎ ለፍጥረት ሁሉ ሰላምና ደህንነት በመማፀን፣ ይህችን አጭር ዘመናቸውን በጥሞና የሚያሳልፉበት ገዳም  መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከአገራችን ባለፈው በተለያዩ የአለማችን ክፍላት ዓለማት የሚገኙ ክርስቲያኖች በብሕትውና ለመኖር ሲሹ  ሁሉንም ትተው የሚመጡበት ቅድስ ስፍራ ነው፡፡ እነዚህ መናኞች ከቀደሙት አበው መነኮሳት ጋር በመሆንና እነርሱንም በማገልገል በገዳሙ ሕግና ሥርዓት መሰረት፤ ምንኩስና ተፈፅሞላቸው እንደቀደሙት አበው ሁሉ እነርሱም በዚሁ ገዳም ይኖራሉ::
በመሆኑም ይህን ገዳም አስቀድመው በስውር፤ ዘግየት ብሎ ደግሞ በገሃድ ለማጥፋት ያደረጉትና እያደረጉ ያለውን ርብርብ አብዛኛው ሕዝበ ክርስቲያን ያውቀዋል፡፡
እንግዲህ  እነዚህ መነኮሳት የሥጋዊ  ሕይወት ፈቃዳቸው ሁሉ ንቀው መጥተው ሳለ  እንሴት ወደ ኋላ ተመልሰው ስላማይረባው አላፊ ጠፊ፤ የክፋትና ተንኮል ዓለም ሊያስቡ እንደሚችሉ እግዚያብሔር ይወቀው፡፡ የባህታዊያን የዘወትር ተግባር ስለ ሰላም ፣ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነት፣ ስለ መተሳሰብ፣ ስለ ማያልፈውና ስለ ወዲያኛው  ሠማያዊ አለም በጸሎትና በምስጋና መትጋት ነው፡፡ ሕወሓት በጠላትነት የፈረጃቸው ዋልድባ ገዳምና  መከራን እየተቀበሉ እዚህ የደረሱት መነኮሳት ዓላማቸው ይኸው ብቻ ነው፡፡ የመስቀሉ ፍቅር የገባቸውና የተገለጠላቸው ሁሉ እውነቱ ይገባቸዋል፡፡
“የዋልድባና የሕወሓት ፍጥጫ” የተቀነጨበ (በአባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም ከተፃፈው)


Read 2389 times