Sunday, 26 July 2020 00:00

የ75 አመቱ ሙሴቬኒ ለ6ኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ይወዳደራሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አል በሽር ሞት ሊፈረድባቸው ይችላል ተባለ


                የ75 አመቱ የዕድሜ ባለጸጋ የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ በመጪው አመት ጥር ወር ላይ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለ6ኛ የስልጣን ዘመን በመወዳደር አጠቃላይ የስልጣን ዘመናቸውን ወደ 40 አመት ለማድረስ መወሰናቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1986 በወታደራዊ አመጽ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን በብቸኝነት አንቀጥቅጠው ሲገዙ የኖሩት ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ፤ እድሜና ጤና ተጫጭኗቸው ራሳቸውን ችለው ለመጓዝ እንኳን የማይችሉበት ደረጃ ላይ ቢገኙም በቀጣዩ በምርጫ ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተባለው ፓርቲያቸው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ኤንቲቪ በተባለው የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ስራ አስፈጻሚው ሙሴቬኒ የአገሪቱን የለውጥ ተግዳሮቶች ለማጥፋት አቻ የሌላቸው መሪ ናቸውና ፓርቲውን ወክለው እንዲወዳደሩና በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ወስኛለሁ ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ሰውዬውን በስልጣን ላይ ለማቆየት ሲባል ከ75 አመት በላይ የሆነው ሰው ፕሬዚዳንት መሆን አይችልም የሚለውን ህግ ከ2 አመታት በፊት መሰረዙንም አስታውሷል፡፡
የሙሴቬኒን ስልጣን ለማራዘም ተብሎ የዕድሜ ገደብ ህጉ መሰረዙን በመቃወም በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞዎችን በማቀጣጠልና ለእስር እስከመዳረግ በመድረስ የሚታወቀው ዝነኛው የአገሪቱ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይኒ በመጪው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ማሰቡን ከሰሞኑ ለሲኤንኤን በሰጠው ቃለመጠይቅ መናገሩንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በሙስና ወንጀል የ2 አመታት እስር ተፈርዶባቸው በወህኒ የሚገኙት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኡመር አል በሽር፣ ከ30 አመታት በፊት ወደ ስልጣን የመጡበትን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አቀነባብረዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በሞት ሊቀጡ እንደሚችሉ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡ በህዝባዊ ተቃውሞ ባለፈው ዓመት ከስልጣን የወረዱት የ76 አመቱ አል በሽር፣ በመዲናዋ ካርቱም በሚገኝ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም፣ ችሎቱ ምንም አይነት የምስክርነት ቃል ሳይቀበል ጉዳዩን ብዙ ጠበቆችና የተከሳሽ ቤተሰቦችን መያዝ በሚችል ሰፋ ባለ የችሎት አዳራሽ ለማየት ለነሃሴ 11 ቀጠሮ በመስጠት መጠናቀቁ ተነግሯል፡፡
በሰኔ ወር 1989 ከተፈጸመውና ለስልጣን ካበቃቸው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከእሳቸው በተጨማሪ የቀድሞ የአገሪቱ የጦር ሃይል አመራሮችና ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎች 16 ሰዎችም ክስ እንደተመሰረተባቸው አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የሱዳን የጦር ሰራዊት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ ሰራዊቱን በሚሳደቡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት በሚገኙ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድና ለዚህም ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለህግ የሚያቀርብ ልዩ ክፍል ማቋቋሙን በመግለጽ ማስጠንቀቁ ተነግሯል፡፡


Read 2250 times