Print this page
Saturday, 01 August 2020 11:44

ከህዳሴ ግድብ ሙሌት በኋላ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 - ቤታቸውንና ወርቃቸውን የሚሰጡ ሰዎች አሉ
    - በልማት ባንክ ብቻ ከሐምሌ 1 እስከ አሁን ከ32 ሚ. ብር በላይ ቦንድ ተሸጧል
    - በ8100A ከ500 ጊዜ በላይ ደስ እያለኝ ልኬአለሁ
    - የ 5 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል
          
           የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት መከናወኑን ተከትሎ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን የጨመረ ሲሆን አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብቻ ከ3ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ መከናወኑ ተገለፀ፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ከህዳሴው ግድብ ሙሌት በኋላ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡ የቦንድ ሽያጩ እየተከናወነ ያለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በልማት ባንክና በማይክሮ ፋይናንሶች መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ በሁሉም የቦንድ መሸጫ ቦታዎች የቦንድ ሽያጩ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን ከዕቅድ በላይ ማከናወን መቻሉንም አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሪፖርቱን የሚያቀርብላቸው ሁልጊዜም ወር በገባ በ25ኛ ቀኑ መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ የዚህ ወር የንግድ ባንክ ሪፖርት እንዳልደረሳቸውና በልማት ባንክ በኩል ግን ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ሽያጭ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ በተከናወነ የቦንድ ሽያጭ፤ አቶ በላይነህ ክንዴ የተባሉ ባለሀብት የአምስት ሚሊየን ብር ቦንድ የገዙ ሲሆን፤ አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ ለ50ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸው ማክበሪያ ባዘጋጁት ገንዘብ የአንድ ሚሊየን ብር ቦንድ መግዛታቸውን ጠቁመው ይህም ህብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን ከፍተኛ ስሜት የማያመለክት መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ተናግረዋል፡፡
በክልሎችም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከግድቡ ውሃ ሙሌት በኋላ በአስገራሚ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን የጠቆሙት ወ/ሮ ፍቅርተ፤ መኖሪያ ቤታቸውን፣ ወርቃቸውንና ዋጋ ያወጣል ያሉትን ንብረታቸውን ሁሉ የሚሰጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ ብለዋል፡፡
ሁሉም ህብረተሰብ በቀላሉ ድጋፉን ለማድረግ የሚችልበት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ከእነዚህም ዋነኛው የ8100 አጭር መልዕክት እንደሆነና ከየካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ  29 ሚሊዮን 197ሺ ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በየክልሎችና በክፍለ ከተሞች እየዞረ ሲሆን በዚህም ከፍተኛ ገንዘብ እየተሰበሰበ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ተሳትፎ የሚዲያው ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ወ/ሮ ፍቅርተ ገልፀዋል፡፡
መጋቢት 4 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሌት ከተከናወነበት ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ለግድቡ ድጋፍ የማድረግ ፍላጐትና የእኔነት ስሜት እየጨመረ ሄዷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አተላስ ሆቴል አካባቢ በሚገኝ አንድ የግል ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ወጣት ዳዊት ዮሐንስ እንደተናገረው፤ ግድቡ በተጀመረበት ወቅት በአንድ የመንግስት ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ በመ/ቤቱ በኩል የቦንድ ግዢ ማከናወኑንና በወቅቱ ግዢውን የፈፀመው በመ/ቤቱ በመታዘዙ እንጂ በፍላጐቱ እንዳልነበረ ገልፆ፤ ግድቡ እዚህ ደረጃ ደርሶ ላየው እችላለሁ የሚል እምነት እንዳልነበረው የሚናገረው ወጣቱ፤ ለቦንድ ግዢ የከፈለውን ገንዘብ እንደ ኪሳራ ቆጥሮት ትቶት እንደነበር ገልጿል፡፡ አሁን ግድቡ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሌት ተከናውኖና አገሬ ወደ ከፍታ የምትወጣበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ስትንደረደር ማየት መቻሌ ደስታዬን የላቀ አድርጐታል::  በየእለቱም በ8100A ድጋፌን ሳላደርግ ያለፍኩበት ቀን የለም፤ ይህንን የማደርገውም በጣም ደስ እያለኝ ነው ብሏል፡፡
ከ5 አመታት በፊት በውጪ አገር በሚማሩ ሁለት ልጆቻቸው ስም ቦንድ ገዝተው እንደበር የገለፁት አቶ ተስፋ ተገኝ፤ በወቅቱ ልጆቹ የቦንድ ግዢውን ለመፈፀም ብዙም ደስተኛ ባይሆኑም በእኔ ጉትጐታና ጫና ግዢውን ፈፅመው ነበር ይላሉ፡፡ አሁን ልጆቼ ተጨማሪ ቦንድ ግዢ እንድፈፅምላቸው ጠይቀውኛል፡፡ ይህ የኮሮና ወረርሽኝ ባይዛቸው ኖሮ ለአዲስ አመት ራሳቸው በአካል መጥተው ግድቡንም አይተው ተጨማሪ ቦንድ ገዝተው ለመሄድ ፈልገው ነበር፡፡ ሁኔታው አልፈቀደም እንጂ ብለዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በአባይ ወንዝ ላይና ዙሪያ ምንም አይነት የልማት ስራዎችን እንዳታከናውን ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት ቆይቷል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ለመጀመሪያ ዙር የታቀደለትን 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ ችሏል፡፡ ከ4-6 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ደግሞ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲይዝ ይደረጋል:: በቀጣዩ ዓመት ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንዲጀምሩ እንደሚደረግና በ2015 ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ 

Read 924 times