Saturday, 01 August 2020 11:46

ሐምሌ፤ የክረምት ንጉሥ

Written by  አዲሱ ዘገየ
Rate this item
(1 Vote)

    "--ከጠላት ወረራ በኋላ በሀገር ደረጃ የተከናወኑ ጉዳዮችን ለመጥቀስ ያህል፣ ሐምሌ 16 ቀን 1935 የቀ.ኃ.ሥ. 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (ያሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ) መቋቋሙ፤ በዚያው ዓመት ሐምሌ 24 ቀን የቴምብር ቀረጥ አዋጅ መታወጁ፤  ሐምሌ 2 ቀን 1936 ደግሞ መጽሔተ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ለኅትመት መብቃቱ፣ ዘመናዊ የሥልጣኔ ብርሃን በወርኀ ሐምሌ ለመፈንጠቃቸው ምሳሌ ይሆናሉ፡፡--"
       
              (ካለፈው የቀጠለ)
፩ኛ. ዜና ልደት ወሥርዓተ-መንግሥታት፡- በሐምሌ ዕለተ ልደታቸው ከሚከበርላቸው መሪዎችና ታዋቂ የሀገሬ ግለሰቦች መካከል ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ አፄ እስክንድር (ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ በ1463)፣ ልዑል አልጋ ወራሽ መርዕድ አዝማች አስፋወሰን ኃይለሥላሴ፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ አበበ በቂላ፣ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ፣ ስመ ጥሩ አርበኛ ደጃዝማች ኪዳኔ ወልደመድኅን ጥቂቶቹ ናቸው:: ከውጭ ሀገራት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች መካከል ደግሞ ቢል ክሊንተን፣ ናፖሊዮን፣ ባራክ ኦባማ፣ ፊደል ካስትሮ፣ ሁጎ ሻፌዝ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ጣልያናዊው የፋሺስት መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ሣልሳዊ አቡነ ሺኖዳ ፓትሪያርክ ዘእስክንድሪያ፣ የብሪታንያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሰር ኤድዋርድ ሂዝ፣ አምባገነኑ የቱኒዝያ ሪፐብሊክ መሥራች ፕሬዚዳንት ሀቢብ ቡርጊባ፣ የሞሮኮው የቀድሞ ንጉሥ ዳግማዊ ሐሰን፣ የአጭር ርቀት ሯጩ ኡዜን ቦልት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ግለሰቦች በሀገር ደረጃ በየሙያ ዘርፋቸው ንጉሣዊ አክሊልን ከመቀዳጀታቸውም በላይ የፊታቸው ቅርጽ አንበሳ የሚመስልና የደልዳላ ቁመና ባለቤቶች አድርጓቸዋል፡፡
ጁሊየስ ቄሳር የሚባል ሮማዊ ንጉሥ ነበረ፡፡ ይህ ንጉሥ ሀገረ ግዛትን በማስፋፋት ታሪኩ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳ የፈረንጆቹ ጁላይ ወር በርሱ ስም እንድትሰየምለት ተደርጓል፡፡ የሀገሩን ግዛት ለማስፋፋት የረዳውን የትግል ስልት በገለጸበት ጽሑፉ “መጣሁ! አየኋቸው! ድል አደረግኋቸው!” ይላል፡፡ ይህ ንጉሥ የአሸናፊውን የአንበሳ መገለጫ ይዟል፡፡ አሰድ ቋሚ፣ ጽኑ፣ ንቁ፣ በዕይታው ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያለው ኮከብ ነው፡፡ በሀገሬው “አሰድ ያየውን አይሰድ” ተብሎ ተመስክሮለታል፡፡ ያየውን አይሰድም፤ በዋዛ ፈዛዛ አይለቅም፤ የፈለገውን አያጣም፤ “ፍንክች ያያ ቢላዋ ልጅ!” የተባለለት ነው፡፡ በሀገሬ አርሶ አደር ዘንድ ዘር ለመዝራትና በዐውድማ ላይ ምርትን ለማፈስ የሚመረጠው ግለሰብ ኮከቡ አሰድ የሆነለት ነው፡፡ አሰድ የዘራው ሰብል አይባክንም፤ ምርቱ ይትረፈረፋል እንጂ፤ አሰድ ያፈሰው ምርትም እንዲሁ ለብክነት አይዳረግም የሚል እምነት አለ፡፡ ወርኀ ጁላይ ከላይ በተጠቀሰው ጀብደኛ ንጉሥ ስም ስትጠራ ተምሳሌታዊነቷ የኃይል ድጋፍ በማግኘት ድል የሚፋጠንባት፣ በግለሰብ፣ በቤተሰብ በሀገር ደረጃ የሚደረግ የግዛት ማስፋፋት (የአዛዥ ናዛዥነት ሥልጣን፣ የኃይል ሚዛን) የ“ይገባኛል!” ንቅናቄዎች በድል የሚቋጩባት ወር ናት፡፡
ወርኀ ሐምሌ ከሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፣ በትረ-መንግሥቱ ለሚመዘዘው የገዥ አካል የተመቸች ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጨለማው ሐምሌ ከጭለማ መውጣትን የሚገልጽ የኅትመት ብርሃን የፈነጠቀላት በ1900 ነበር፡፡ በሶርያዊው ሃቢብ ይድሊቢ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባው ማተሚያ ማሽን ለመጀመሪያ ጊዜ የኅትመት ሥራውን ያወጣበት ወር ናት። የሚከተሉት የኢትዮጵያ ሕገ-ደንቦችን የተመለከቱ ዐዋጅ የታወጀባቸው ምክንያቶች ሲሆኑ፣ በዚሁም ሀገሪቱ ወደ ሠለጠኑ ሀገራት ተርታ እንድትገባና እንድትዘምን በማለም የተከወኑ ሥራዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የባላባት ደንብ/ድርሻ ዐዋጅ ሲሆን ሐምሌ 20 ቀን  1912 የታወጀና ዓላማውም የዘመኑ ባላባቶች ከምስኪን አርሶ አደሮች የሚቀራመቱትን ዓመታዊ የአዝመራ ፍሬ ድርሻ ለመወሰን የተዘጋጀ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የትምባሆ ሬዥ አፈጻጸም ደንብ ዐዋጅ ሲሆን፣ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ አማካይነት ሐምሌ 1 ቀን 1920 ታወጀ፤ ሶስተኛው ከሁለት ዓመት በኋላ (1922) የውጭ ሀገር ሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለመሆን የሚችልባቸው ሁናቴዎችን የሚዘረዝር ዐዋጅ በሐምሌ 15 ቀን ጸድቆ ወደ ሥራ ገባ:: በአራተኛ ደረጃ ፋና ወጊ የምታሰኝ ዐዋጅ የታወጀባት ዕለት ናት፡፡ ይህቺውም ሐምሌ 9 ቀን 1923 ላይ የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት የጸደቀችባት ቀን ናት፡፡ ይህ የሆነውም ንጉሡ ከነገሡ ሁለት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ ካመት በኋላ ደግሞ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት (የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂ/አሰናጂ) ስለ ሕገ-መንግሥት ጥቅምና ፋይዳዎች፣ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ ዓይን ገላጭ ማብራሪያ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ያቀረቡት በሐምሌ ወር ነበር፡፡ ወርኀ ሐምሌ የአፈርሳታ ደንብ (ሐምሌ 26 ቀን 1925) ዐዋጅ (በአፈርሳታ አውጫጭኝ ስብሰባ ምክንያት አርሶ አደሩ ከሥራ እየቦዘነና ምርቱ እየቀነሰ በመምጣቱ ገበሬውን ከሥራው ላለማቦዘን በማሰብ) የወጣበት ጊዜ ነው:: ከጣልያን ወረራ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የወጣው ሌላ ዐዋጅ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዐዋጅ ሲሆን፣ ጊዜውም ሐምሌ 1 ቀን 1927 ነበር:: የቀይ መስቀል ማኅበር በጦርነት ወይም በሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው አካላት አስፈላጊ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግን ዓላማው አድርጓል፡፡ ይህ ማኅበር በኢትዮጵያ ሲመሰረት የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ንጉሠ ነገሥቱ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡
ከጠላት ወረራ በኋላ በሀገር ደረጃ የተከናወኑ ጉዳዮችን ለመጥቀስ ያህል፣ ሐምሌ 16 ቀን 1935 የቀ.ኃ.ሥ. 2ኛ ደረጃ ት/ቤት (ያሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ) መቋቋሙ፤ በዚያው ዓመት ሐምሌ 24 ቀን የቴምብር ቀረጥ አዋጅ መታወጁ፤  ሐምሌ 2 ቀን 1936 ደግሞ መጽሔተ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ለኅትመት መብቃቱ፣ ዘመናዊ የሥልጣኔ ብርሃን በወርኀ ሐምሌ ለመፈንጠቃቸው ምሳሌ ይሆናሉ፡፡
ከባህር ማዶ ሀገራት ተሞክሮ አንጻር፤ የታላቋ ብሪታንያና የአየርላንድ መንግሥታትን በማዋሐድ የአሁኗ የታላቋ ብሪታንያ እና ሰሜን አየርላንድ ውሕደት ሕግ ጸድቆ የተተገበረው በሐምሌ 1793 ነበር፡፡ ሐምሌ 1948፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አይዘንሃወር፤ በሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የእንደራሴዎች ሸንጎ/ሴናተሮች አማካይነት በጋራ የጸደቀው “በእግዚአብሔር እናምናለን” ወይም In God We Trust የሚለውን ብሔራዊ የሀገሪቱ መፈክር እንዲሆን ያጸደቁበት ጊዜ ናት፡፡ በተመሳሳይ በአሜሪካ የ500፣ 1000፣ 5000 እና 10000 የገንዘብ ወረቀቶች (ዶላር ቅጠሎች) ከሥልጣናቸው የተሰናበቱት በሐምሌ ወር ላይ ነበር፡፡
፪ኛ. ሹመት-ሽረት እና ዜና ረፍት፡- ሐምሌ በአንበሳው ኮከቧ መጋቢነት ሥርዓተ-ሲመት (ሹመት፣ ሽረት፣ ውርስ) እና የታዋቂ ሰዎች ዜና ረፍት ይዛለች፡፡ 1260 ወርኀ-ሐምሌ አፄ ይኩኖ አምላክ ተቀብተው ሲነግሡ፣ በ1971 ደግሞ ሳዳም ሁሴን በኢራቅ ነገሡ፤ በ1994 ሐምሌ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲለወጥ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት፣ ታቦ ኢምቤኪን የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አድርጎ ሾመ:: በ1823 ቤልጅግ ነጻ ሀገር ስትሆን ቀዳማዊ ሊዮፖልድ የሀገሪቷ ንጉሥ ሆኑ:: ጀርመናዊው የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር፣ የጀርመን ሰብዓዊ የሠራተኞች ማኅበር (Nationalsozialistische Deutsche Arbeiterpartei) መሪ ሆኖ የተሾመው በሐምሌ 1913 ነበር፡፡
1944 ሐምሌ ላይ በጋማል አብዱልናስር የተመሠረተ የግብጽ መኮንኖች ቡድን፤ በጀኔራል ሙሐመድ ናጊብ መሪነት የወቅቱን ንጉሥ ከመንበረ-ሥልጣኑ ላይ አወረደ:: 1966 የግሪክ ወታደራዊ መንግሥት ከሥልጣኑ ተሽሮ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ኮንስታንቲን ካራማንሊስ አዲስ መንግሥት እንዲያቋቁሙ ተደረገ፡፡ በሐምሌ 1978 የኡጋንዳው መሪ ሚልተን ኦቦቴ፣ ለ2ኛ ጊዜ ከመሪነት መንበር ላይ የወረዱበት ነው። 1992 ሐምሌ 16 ቀን ታዋቂው የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊ አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ ዜና ረፍታቸው የተሰማባት ናት፡፡ በ1892 ሐምሌ ላይ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የኢጣልያ ንጉሥ የነበሩት ቀዳማዊ ኡምቤርቶ በነፍሰ ገዳይ እጅ የተገደሉበት ነው፡፡
፫ኛ. ፈጠራና ግኝት፡- በወርኀ ሐምሌ ዓለም በፈጠራና ግኝት ፍሬዎቿ እንድትደምቅ  ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ በጨረቃ የግዛት ዘመን ጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መርገጥ የተቻለበት ነው:: ወደ ጨረቃ የተደረገውን ጉዞ አፖሎ 11 የተሰኘችው መንኮራኩር የሰው ልጆችን ይዛ ከጆን ኤፍ ኬኔዲ የጠረፍ ምርምር ማዕከል የተተኮሰችበት ዕለት 1961 ሐምሌ ወር ላይ ነበር፡፡ መንኮራኲሯ ጨረቃ ላይ ስታርፍ የሰላሳ ስምንት ዓመቱ ኒል አርምስትሮንግ የጨረቃን ወለል በመርገጥ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ሆኖ ተዘገበ፡፡ በዚህቺው የሐምሌ ወር ላይ ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ጠፈርተኞቹን የያዘችው መንኮራኩር በሰላማዊ ውቅያኖስ ላይ አረፈች፡፡ በ1962 ባስራ አንደኛው የሐምሌ ወር ላይ ግብጽ ለ11 ዓመታት (10 ዓመት የሚሉ ምንጮችም አጋጥመውኛል) ያህል ስትገነባው የነበረውን የአስዋን ግድብ ፍጻሜ ያበሠረችበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ41 ዓመታት በኋላ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጀመረች፡፡ ዘጠኝ ዓመት ከአራት ወራት በኋላ የግድቡን የውሃ ሙሌት ለመጀመር በኢትዮጵያ የሐምሌ ወር ተመረጠ፡፡
ጨረቃ የባህር፣ የውቅያኖስና የአየር ሞገዶችን በምትመራበት ሐምሌ ወር ላይ ከተፈበረኩ የፈጠራ ውጤቶች መካከል በ1769 ላይ ኦክስጅን የተሰኘ ንጥረ ውህድ በእንግሊዛዊው ጆሴፍ ፕሪስትሊ አማካይነት ሲገኝ፣ በ1970 ደግሞ ሉዊዝ ብራውን የተሰኘች የመጀመሪያዋ የቤተ-ሙከራ-ጽንስ የተወለደችበት ጊዜ ነው፡፡ ከሞገዳማ ክስተቶች መካከል በ1978 ሐምሌ ወር ላይ በመቀሌ ከተማ የሰማዕታት ሐውልት አጠገብ የሚገኘው፣ ዕድመ ንለካቲት 11 የሚለው  ድምጺ ወያነ የተሰኘ የራዲዮ ጣቢያ በደደቢት አካባቢ ሥርጭቱን ጀመረ:: ይህ የራዲዮ ጣቢያ ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያ አድጎ 34ኛ ዓመቱን ሊያከብር ሲሰናዳ፣ የቲቪ ስርጭቱ የተቋረጠው በሰኔ ወር ማሰሻ ወይም ሐምሌ ዋዜማ ላይ ነው፡፡ ጨረቃ ማለት ወርኅ የሚል ፍቺ ያስገኘች ዑደታዊ የብርሃን ቅንጣት ናት፡፡ ስለሆነም ጨረቃ ገዥ በምትሆንበት ጊዜ በሰው በተለይም ወራቸውን በሚቆጥሩ እንስቶችና በባህር ሞገድ ላይ የባህርይ ለውጥና ነውጥ መከሰቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ምሳሌ የምትሆነው ሕንዳዊት ሴት ታሪክ ነው፡፡ በሀገረ ሕንድ ጨረቃን የሚወክል አንድ ታሪካዊ አጋጣሚ ሐምሌ 1999 ተከናወነ፤ ራቲባ ፓቲል የተሰኘች የመጀመሪያዋ ሕንዳዊ አንስት ፕሬዚዳንታዊ ቃለ መሐላ ፈጽማ መንበረ መንግሥቱን ተቆናጠጠች፡፡
ሐምሌ 1937 ላይ የተባበረችው አሜሪካ የመጀመሪያውን አቶሚክ ቦምብ ሙከራ በስኬት አከናወነች፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ይመስላል፤ የአቶሚክ ቦምብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅማ በጃፓኗ ሄሮሽማ ግዛት ላይ ጥቃት ስታደርስ ባንዲት ቀን ከ70 ሺህ በላይ፣ በቀጣይ ቀናትም ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲጠፉ ምክንያት የሆነች ወርኀ ሐምሌ ናት፡፡ ጃፓን ከስምንት ዓመታት በኋላ ሌላ ተፈጥሯዊ አደጋ አስተናገደች፡፡ ይህም በሆንዳ ደሴት ላይ (1945) በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ1700 በላይ ሰዎች ያለቁበት ሆኖ ተመዘገበ፡፡
፬ኛ. የሐምሌ መንገድ፡- ወርኀ ሐምሌ ከቦታ ቦታ ከመዘዋወር ይልቅ ባሉበት ቦታና የሥራ ድርሻ ረግተው፣ ጸንተው የሚያሳልፉባት መክተቻ ወር ናት፡፡ በጊዜዋም ከቦታ ቦታ ለመዘዋወርና ለመንቀሳቀስ የሚያበቃ ዘዋሪና አሣሽ የኮከብ ባህር የላትም፡፡ ይህን ሀሳብ ከሚያጠናክሩ አብነቶች ለመጥቀስ ያህል፣ በሀገራችን ሐምሌ 21 ቀን 1908 የተፈጸመ ጉዞ ነበር፤ ልጅ ኢያሱ ወደ ሐረር ወጥተው በዚያው ያስቀራቸውን የጉዞ ስምሪት ሀ ብለው ጀመሩ፡፡
በቀጣዩ ዓመት ሐምሌ 29 ቀን ደግሞ ልጅ ኢያሱን ለመያዝ በመቅደላ ውጊያ ተደረገ፡፡ ልጅ ኢያሱ ሐምሌን ለሽሽት መምረጣቸው እህል ውሃቸው ማለቁን የሚያመለክት ንግር ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የእህል ውሃ ማለቅ ከወንዝ ወንዝ ተሻጋሪ መሆን፣ ዘዋሪነት፣ ዋታችነት፣ ፈላሽነት ያሳያልና:: እኒህ የመንበረ መንግሥት ወራሽ፣ ቋሚ የሕይወት ሚና አጥተው፣ ተነጥቀው፣ መዋለል፣ መባዘን፣ ርጋታ አልባ መሆን መታወቂያ ሆኗቸው በወጡበት እንዲቀሩ ተደረገ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በ1535 ኢትዮጵያን ለመርዳት የተላከው የፖርቱጋል ሠራዊት በዕለተ ቅዳሜ ምጽዋ ደረሰ፡፡ ክረምቱንም በዚያ አሳለፈ፤ በኋላም እቴጌ ሰብለወንጌል ወደሚገኙበት ቦታ የደረሰው ክረምት ከወጣ በኋላ ነበር፤ የኢትዮጵያን ምድር ከረገጠ በኋላ ጉዞውን ወደ ዕረፍት ለወጠ እንጂ ወደፊት መገስገስን አልመረጠም።
የጆን ኤፍ ኬኔዲ ቤተሰብ በእንቅስቃሴ አማካይነት የሚፈጠር የመጀመሪያውን ቤተሰባዊ አደጋ ያስተናገዱት በሐምሌ 1961 ነበር፡፡ ታናሽ ወንድምዬው ሴናተር ኤድዋርድ ኬኔዲ መኪና እየነዳ ሳለ ባደረሰው የመኪና ግጭት ከእነመኪናው ድልድይ ጥሶ ባህር ውስጥ ገብቶ ሕይወት አጥፍቷል፡፡ የጆን ኤፍ ኬኔዲ ልጅ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጁንየር ይባላል፡፡ ይህ ሰው ባለቤቱንና የባለቤቱን እህት አሳፍሮ በረራ እያደረገ ሳለ አውሮፕላኑ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ሰምጦ ሁሉንም ተጓዦች እንደወጡ ያስቀራቸው በሐምሌ ወር 1991 ነበር፡፡ ሐምሌ ከቤት የማይወጣባት ወር መሆኗን ሌላ ፕሬዚዳንታዊ ጉዞ ምሳሌ እናድርግ፡፡ ጊዜው 1997 ወርኀ-ሐምሌ ነው፤ በወቅቱ የሞሪታንያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ማውያ ኡልድ አህመድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ተጓዙ፤ የጉዞው ዓላማ በሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ፉዓድ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘት ነበር፡፡ እኒህ ሰው “ሀገር ሰላም!” ብለው ወጥተው ሳለ በወጡበት እንዲቀሩ ያደረጋቸው መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደባቸው፤ ይህም ከሥልጣናቸው ለመሰናበት አበቃቸው፡፡
ሐምሌን በአንበሳው የሊዮ ኮከብ በኩል ሲፈቷት፣ ከላይ የተጠቀሱ የእምነት አባቶች፣ ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ የቀድሞ ነገሥታትና የሀገር መሪዎች ለቆሙለት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ዓላማ ስኬት የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ ያከናወኑትን የመሪነት፣ ያስተማሪነት፣ ሚና አብነት አድርገን ስንጨዋወት ቆየን:: ዕድሜና ጤና ብንታደል ወራሽ ወራቶች የያዙትን ምስጢራትም በቀጣይ የምናወጋ ይሆናል፡፡

Read 899 times