Print this page
Saturday, 01 August 2020 11:50

መዘናጋት በኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 - ከ15ሺ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል
     - በአምስት ቀናት ብቻ 3ሺ 117 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል
     - 53 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል
     - ከጥቂት ወራት በኋላ የማንቀለብሰው ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል


             በአሁኑ ወቅት ለሚታየው ከፍተኛ የኮሮና ወረርሽኝ የህብረተሰቡ መዘናጋት ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተጠቆመ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የድንተኛ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰርና በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 የጤና ቴክኒክ አማካሪ ቡድን አስተባባሪ ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋነው ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ለኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ጉዳዮች ዋነኛው መዘናጋት ነው፡፡ ህብረተሰቡ በሽታው በአገራችን በተከሰተባቸው ጥቂት ቀናት ያደርጋቸው የነበሩትን የጥንቃቄ እርምጃዎች እየዘነጋቸው በመምጣቱና በብዙ አካባቢዎች ላይ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች በመቀነሳቸው የበሽታው ስርጭት እየተባባሰ መሄዱን ያመለከቱት ረዳት ፕሮፌሰር ወልደሰንበት ይህ ነገር የበለጠ ዋጋ ሳያስከፍለን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ህግ ቢያወጣም አስፈፃሚ አካላት ህጉ በአግባቡ መፈፀሙን ሊቆጣጠሩ ሲገባ ይህ ባለመደረጉ ምክንያት የወጡ ህጐች እየተጣሱ ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ነገሮች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል - ዶ/ር ወልደሰንበት፡፡ አሁን በሽታው እየሄደ ያለበት ሁኔታ ሊያስፈራራንና ሊያስደነግጠን ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ወደኋላ መመለስ ባንችል እንኳን በሽታውን ባለበት ለማስቆም የሚያስችል ዕድል በእጃችን ላይ አለ ብለዋል፡፡
የውስጥ ደዌ ሀኪሙ ዶ/ር ዳግማዊ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ የክረምቱ ወራት ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች እንዳሉት ገልፀው፤ የክረምት ወራት ጉንፋንን ጨምሮ የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች የሚቀሰቀሱበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን የኮቪድ 19 በሽታም የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች መካከል በመሆኑ ስርጭቱ ከፍ ማለቱ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከፍ ያለ ቅዝቃዜ የሚኖረው የክረምቱ አየርም ለበሽታው ተጋላጭነታችንን የበለጠ ይጨምረዋል፡፡
የመተንፈሻ አካላት በቅዝቃዜ በሚጐዱበት ወቅት ለኮሮና ቫይረስ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፤ ይህ ደግሞ በበሽታው በቀላሉ እንድንጠቃ ያደርገናል ብለዋል - ዶ/ር ዳግማዊ፡፡
የኮሮና ወረርሺኝ በአገራችን ከተከሰተበት መጋቢት 4ቀን 2012 ዓ.ም ከፍተኛ ቁጥር ያለው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተመዘገቡበት ሳምንት ይህ የያዝነው ሣምንት ሲሆን፤ በአምስት ቀናት ብቻ 3117 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 53 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምርመራ አቅማችን እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ ይህም በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ለማወቅ እንዳስቻለን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ:: በአምስት ቀናቱ ብቻ 39ሺ 289 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ 930 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከትናንት በስቲያ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የበሽታው ስርጭት መጠን መጨመር በህብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ መዘናጋት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው፤ በተለያዩ አካባቢዎች ያለ ጥንቃቄ የተደረጉ ሰልፎችና እንቅስቃሴዎች ለቁጥሩ ማሻቀብ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
አያይዘውም፣ መዘናጋታችን ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ኋላ የማንመለስበት ዋጋ ሊያስከፍለን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገራችን እስከ ሐምሌ 22/2012 ዓ.ም ድረስ ለ403ሺ 611 ሰዎች ምርመራ ተደርጐ 15ሺ 810 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ሲረጋገጥ 253 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡ እስከ አሁን 6685 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል፡፡



Read 1094 times