Print this page
Saturday, 01 August 2020 12:47

“ባይቶና” የትግራይ የምርጫ ስርአት እንዲቀየር ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ለታላቋ ትግራይ እውን መሆን እታገላለሁ የሚለው “ባይቶና ትግራይ” ፓርቲ፤ በትግራይ ክልል ይካሄዳል የተባለው ምርጫ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ መርህ እንዲፈፀም ጥያቄ አቀረበ፡፡
ፓርቲው በክልሉ ይካሄዳል በተባለው ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ባስታወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫው፤ የክልሉን ስልጣን የተቆጣጠረው ህወኃት፤ ለምርጫው አስፈላጊ የሆነውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ እንዲሁም በሚዲያዎች የጀመረውን ፕሮፖጋንዳና ሌሎችን የማጥላላት ዘመቻ እንዲያቆም አሳስቧል፡፡
በትግራይ የሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ የህዝብ ውሣኔ መልክ ያለው ነው“ ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አዳነ አመነ፤ ከዚህ አንፃር በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች የሚደረገው የበጀት ድጐማና የሚዲያ የአየር ሰአት ለሁሉም በእኩል መከፋፈል አለበት የሚል አቋም አለን ብለዋል፡፡ በክልሉ መቀመጫ ቁጥጥር ልክ ለማደላደል መሞከርም ተቀባይነት የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡
የትግራይ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም እንደነበረው የአንድ ፓርቲ ድምጽ ብቻ እንዲወከልበት አንፈልግም ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ለዚህም የአብላጫ ድምጽ መርህን ያደረገው የምርጫ ስርአት በተመጣጣኝ ውክልና ተተክቶ መካሄድ አለበት ብለዋል፡፡
የክልሉ ህገ መንግስት በምርጫውም መሻሻሉ ስለማይቀር የምርጫ ስርአት ድንጋጌውም እንዲቀየር ባይቶና ጠይቋል፡፡
የተቋቋመው የክልሉ ምርጫ ቦርድ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባና የምርጫ መርሃ ግብር አውጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምር በዚያው ልክ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር በሰፊው የሚገናኙበት መንገድ ከወዲሁ እንዲከፈትም ፓርቲው ጠይቋል፡፡
“ትግራይ የራስን እድል በራስ የመወሰን እድልን መጠቀም አለባት፤ የኢትዮጵያ ሁኔታ ካልተስተካከለ ጥያቄው እስከመገንጠልም ሊዘልቅ ይችላል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በዚህ አካሄድ ላይ ህወኃት እንቅፋት የሚፈጥር ከሆነ፤ የፖለቲካ ዋጋ እንዲከፍል እናደርገዋለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከክልሉ መንግስት በላይ ህዝቡ ለምርጫው ተዘጋጅቶ እየጠበቀ መሆኑንም አቶ ኪዳነ አስታውቀዋል፡፡
ከትግራይ መንግስት ጋር ሆነን ከውጭ የሚመጣን ጫና በጋራ እንቃወማለን፤ በዚያው ልክ በትግራይ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባም ህወኃትን እንሞግታለን እንታገለዋለን ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ ምርጫውም ከዚህ አንፃር ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡  “በክልሉ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅነት እንዳለ እርግጠኞች ሆነናል፤ ምርጫውም ሊታለፍ የማይቻል መሆኑ ታውቋል” ያሉት አቶ ኪዳነ፤ የክልሉ መንግስትም የሚያስተማምን ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በክልሉ ህገመንግስት መሠረት ምርጫውን ለማካሄድም የ3 ወር ጊዜ እንዳለውና እስከ ጥቅምት 30 ምርጫውን ማካሄድ እንደሚቻልም ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡
ብሔራዊ ባይቶና ትግራይ (ባይቶና) ወይም ወደ አማርኛ ሲመለስ የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጐ በዋናነት ለትግራይ ብሔርተኝነት የተቋቋመና ከምንም በፊት የትግራይን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የተቋቋመ ብሔርተኛ ድርጅት መሆኑን ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ፡፡
በትግራይ ክልል ይካሄዳል በተባለው ምርጫ “አረና እና ትዴፓ” እንደማይሳተፉ መግለፃቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ የፌደራል መንግስትም “ክልሉ ለምን ምርጫ ያካሂዳል” ብዬ የሃይል እርምጃ አልወስድም ብሏል፡፡

Read 12035 times