Print this page
Saturday, 01 August 2020 12:36

ፖሊስ በግለሰብ እጅ ሊኖር የማይገባ የሳተላይት መሣሪያ በአቶ ጀዋር ቤት አግኝቻለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ የሃይማኖትና ብሔር ግጭት በማነሳሳት፣ በተጠረጠሩት የኦፌኮ አባሉ ፖለቲከኛው ጀዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ድጋሚ ብርበራ፣ በግለሰብ እጅ ሊኖር የማይገባ የሳተላይት መሣሪያ ማግኘቱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የፖሊስ የምርመራ ቡድን በተጠርጣሪው ላይ እያከናወነ ያለውን ምርመራ አለማጠናቀቁን በመግለፁም ለ3ኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡ የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራትና ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለፍ/ቤቱ አመልክቶ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ በተጠርጣሪው አቶ ጀዋር ቤት በድጋሚ ባደረገው ብርበራ፤ በግለሰብ እጅ ሊገኝ የማይገባው የሳተላይት መሣሪያ ማግኘቱን፣ መሣሪያው ለምን ተግባር ሲውል እንደነበር በባለሙያዎች እየተጠና መሆኑን የጠቆመው ፖሊስ፤ መሣሪያው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮም ኔትዎርክ ቢጠፋ እንኳ በራሱ አለማቀፍ አገልግሎት ማስጠቀም የሚችል መሆኑ ታውቋል ብሏል፡፡
ተጠርጣሪው በህገወጥ መንገድ ባደራጀው ቡድን፣ ንፁሃንን ሲያፍንና በታዋቂ ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ስለመስጠቱ በሰው ምስክር መረጋገጡን የምርመራ ቡድኑ የገለፀ ሲሆን እርምጃ የሚወስድባቸው ሰዎች ስምና አድራሻም መኖሩን የሰው ምስክሮች አስረድተዋል ብሏል - የምርመራ ቡድኑ፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎም፣ አስከሬኑን ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የምኒሊክ ሃውልትን በማፍረስ ቤተ መንግስቱን በሃይል ለመቆጣጠር ያለመ አደረጃጀት፤ ተጠርጣሪው ስለመፍጠሩም በማስረጃ ማረጋገጡን የምርመራ ቡድኑ አስታውቋል፡፡
በኦኤምኤን ጣቢያው ተጠርጣሪው የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ቅስቀሳ ስለማድረጉም ማስረጃ ማሰባሰቡን የገለፀው የምርመራ ቡድኑ፤ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ሁከት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የማጣራት ተግባር እንዲያከናውን የተላከው 17 የምርመራ ቡድን አጣርቶ ባቀረበው ሪፖርት፤ የ109 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ 187 ሰዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 44 ሆቴሎች ተቃጥለዋል፣ ሁለት ሃውልቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል፣ 322 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ 199 የንግድ ድርጅቶችና 70 የመንግስት ተቋማት እንዲሁም አንድ የእምነት ተቋም መውደሙን የጠቆመው ፖሊስ፤ 26 የግል ድርጅቶችና 53 ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል፡፡
በእነዚህና ሌሎች ወንጀሎች ላይ አቶ ጀዋር መሐመድ የነበራቸውን ተሣትፎ በተመለከተ 25 የሰው ምስክሮች ማዳመጡንና የተጠርጣሪዎች ቃል መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ በቀጣይ የወደሙ ንብረቶችን በባለሙያ ለማስገመት፣ የሟቾችን የህክምና ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ እንዲሁም የተገኘውን የሳተላይት መሣሪያ በባለሙያ ለማስጠናት  14 ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል::
ተጠርጣሪው ጀዋር መሐመድ በበኩሉ፤ የሀገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃን ችሎቱን እንዲታደሙ ይደረግ የሚል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን “እኔ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እንዲቀሰቀስ አላደረግሁም ይልቁንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ሠርቻለሁ” ብሏል፤ በቤቱ የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በተመለከተም የጉምሩክ ስነስርዓት የተፈፀመባቸውና ህጋዊ ሂደትን ተከትለው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
ጃዋር ለፍ/ቤቱ፤ “ባልፈፀምኩት ወንጀል የምጠየቀው በቀጣይ ምርጫ እንዳልሳተፍ በመፈለጉ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡
የአቶ ጀዋር ዘጠኝ ጠበቆች በበኩላቸው፤ “የምርመራ ቡድኑ የጠየቀው ጊዜ አሣማኝ አይደለም፣ የምርመራ ውጤቱም ካለፈው የተለየ አዲስ ነገር የለውም፣ የተጠርጣሪውን ተሳትፎ በተናጠል አልዘረዘረም፤ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ አሳማኝ አይደለም” የሚል ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡
ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ፤ ፖሊስ ከጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 12 ቀናት በመፍቀድ፣ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡  
በተመሳሳይ፤ በአዲስ አበባ ሁከት በማስነሳት በተጠረጠሩት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ እንዲሁም በኦሮሚያ ከተፈጠረው ሁከትና ግርግር ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ ባሉት የኦፌኮ አመራር በቀለ ገርባ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡
ይሄን ተከትሎም የአቶ እስክንድር ጉዳይ ለነሐሴ 1 እንዲሁም የአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ደግሞ ለሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡


Read 9421 times