Saturday, 01 August 2020 12:51

“ሠላምና የህዝብ ሉአላዊነትን ለድርድር አናቀርብም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   ቀጣዩ የፓርቲዎች ውይይት በብሔራዊ መግባባት ላይ ይሆናል

            ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ  ባደረጉት ውይይት፤ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሊት፣ የታሰሩ የፓርቲዎች አመራር ጉዳይ፣ የህወሃት ህገ መንግስት የሚጥሱ ድርጊቶችና መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር ያሳየው ዳተኝነትና ያስከፈለው ዋጋ በዋናነት ተነስተዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ፤ በተለይም የፓርቲያቸው አመራር አባል አቶ ልደቱ አያሌው ማስረጃ በሌለበት ያለ አግባብ መታሠራቸውን የገለፁ ሲሆን የኦነግ ም/ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላም የድርጅታቸውን አመራሮች ጨምሮ አባሎቻቸው ከሰሞኑ ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡  የትዴፓ ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ በትግራይ ህወኃት እያራመደው ያለውን አቋምና ከህግ ውጭ ምርጫ ለማድረግ ውሳኔ ላይ መድረሱን በተመለከተ አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ህወኃት ህገመንግስቱን የሚጥሱ ድርጊቶች በግልጽ እየፈጸመ መንግስታቸው ምንም እርምጃ አለመውሰዱን በመጥቀስ ወቅሰዋል::
ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም የተለያዩ ሃሳብ አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃም የህዳሴውን ግድብ እና መንግስት ለኮሮና ወረርሽኝ እየሰጠ ያለውን ምላሽ አድንቀዋል በእነዚህ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይም የጋራ አቋም እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በበኩላቸው ከፓርቲዎች ለተነሰላቸው ጥያቄዎች ከሰጡት ምላሾች መካከል የታሠሩ ሰዎች ጉዳይ ይገኝበታል:: መንግስታቸው እስካሁን የህግ የበላይነት ሲጣስ በቸልታ ሲያልፍ የነበረው የተከፈተው የፖለቲካ ምህዳር ወደ ኋላ እንዳይመለስ በማሰብ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ግን የሀገርን ህልውና የሚገዳደርበት ደረጃ ላይ በመደረሱ እርምጃ ለመወሰድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡  
ከሰሞኑ ግርግርና ሁከት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አካል የታሠረው ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች መሆኑን ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አንድ የከተማ ሙሉ ካቢኔ መታሠሩን በመጥቀስ፣ እስሩ የፖለቲካ ልዩነትን ሳይሆን ጥፋተኝነትን መነሻ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
የታሠሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንም ሆነ ግለሰቦችን ጉዳይ መርምሮ መፍታት የሚችለው ፍ/ቤት ብቻ መሆኑን ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ሰዎችን ከእስር እንድፈታ ሽማግሌ የምትልኩብኝ ሰዎች እኔ ታሣሪዎችን የመፍታት ስልጣን እንደሌለኝ ልታውቁልኝ ይገባል ብለዋል፡፡ የታሠሩ ግለሰቦች ሰብአዊ መብት መጠበቅን በተመለከተ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ በመግለጽም፤ ጉዳያቸው በፍጥነት በፍ/ቤት እንዲታይና በዋስ መፈታት ያለባቸውም በዋስ ይፈቱ ዘንድ መንግስታቸው ግፊት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡   
“በወንጀል ጉዳይ ያለን ሰው ስፈልግ ይቅር የምል፣ ስፈልግ ደግሞ ይታሰር የምል ከሆነ አደገኛ አካሄድ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ እኔ በግል ከማንም ጋር ፀብ የለኝም፤ በዚያው ልክ የፍርድ ስርአትን ለማበላሸት  አልችልም ብለዋል፡፡
አርቲስት ሃጫሉ ከተገደለ በኋላም ሌሎች የሚገደሉ ሰዎች ዝርዝር መገኘቱን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው ይሄን ታሣቢ ያደረገ ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ለፓርቲ አመራሮቹ አብራርተዋል፡፡
ከኦነግ ምክትል ሊቀመንበር ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ኦነግ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ከማድረግ ጀምሮ ከማንም ፓርቲ በበለጠ መንግስታቸው በገንዘብ ጭምር ድጋፍ ሲያደርግለት እንደነበር አስታውሰው፤ ኦነግ ግን ከተደጋጋሚ ጥፋቶች መታረም አልቻለም ብለዋል፡፡ “በተደጋጋሚ ገዳይ ስኳድ ከተማ ውስጥ አታስገቡ፣ እኔን ለመግደል የምታደርጉትን ሙከራ አይጠቅማችሁም ብዬ ነግሬያችኋለሁ” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ "እኔን መግደል ኢትዮጵያን መግደል አይደለም" ብለዋል፡፡   ኦነግ በብልጣብልጥነት ሁለት ቦታ መርገጡን አቁሞ በሃሳብ ብቻ እንዲታገልም አሳስበዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ የኦነግም ሆነ የማንም አባል ህግ ከጣሰ በህግ ይጠየቃል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁከትና ብጥብጥን መርሃቸው ከማድረግ እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከትግራይ ምርጫ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄዎችም፤ መንግስታቸው በምንም መመዘኛ የትግራይን ህዝብ በሚጐዳ መልኩ የሃይል እርምጃ እንደማይወስድ አስገንዝበዋል፡፡ ምርጫው ቢደረግ ባይደረግ የመንግስታቸው ጉዳይ አለመሆኑን፣ መንግስታቸው የሚያሳስበው በሀገሪቱ የተዛቡ ትርክቶች እየፈጠሩ ያለውን ችግር እንዴት ይፈታ የሚለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡  
መንግስታቸው ከእንግዲህ የሀገሪቱን የሠላምና ሉአላዊነት ጉዳይ ለድርድር እንደማያቀርብ ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ "ኢትዮጵያንም ስሟን ለመጥራት የሚጠየፉ እነሱ ይጠፋሉ፣ እሷ ግን ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡
 በሚቀጥለው ስብሰባቸው፤ በመጪው ዓመት በኮቪድ ሳቢያ የተቋረጠው ትምህርት ይቀጥል ወይ በሚለው ጉዳይ ላይ ከፓርቲዎቹ ጋረው እንደሚወያዩ፣ምርጫው መቼ ይካሄድ የሚለውንም ተመካክረው እንደሚወስኑ ተጠቁሟል፡፡ ቀጣይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት፣በብሔራዊ መግባባት ላይ እንደሚያተኩር የተገለጸ ሲሆን በአጀንዳው ላይ የመነሻ ጽሑፎችን የሚያቀርቡና ውይይቱን የሚያቀናጅ 7 አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙ ታውቋል፡፡     

Read 11487 times