Monday, 03 August 2020 00:00

“ለእኔ ብለሽ አታልቅሽ! ታሪክ አንድ ቀን ትክክለኛውን ፍርድ ይሰጣል”

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

  የነጻነት ታጋዩ ፓትሪስ ሉሙምባ በበልጅግ መንግሥት በግፍ ታሥሮ በነበረበት ጊዜ  ለባለቤቱ በእሥር ላይ ሆኖ ደብዳቤ ሲጽፍ “ክብርት ባለቤቴ ሆይ፤ ለእኔ ብለሽ አታልቅሺ፤ ታሪክ አንድ ቀን ትክክለኛውን ፍርድ ይሰጣል” የሚል ቃል አስፍሮ ነበር፡፡ የመፈታት እድል ያላገኘው ፓትሪስ ሉሙምባ፤ በበልጅግ መንግሥት ባለሥልጣኖችና ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች በምሥጢር በተቀነባበረ ሴራ በግፍ እንደተገደለ፤ ማንነቱም እንዳይታወቅና ማስረጃም እንዳይገኝ ሥጋው ተቆራርጦና በሰልፈር መርዝ ተጠቅልሎ ስለ ተቀበረ ደብዛው ጠፍቶ ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን “እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም” እንደሚባለው፣ ቤልጅግን እንቅልፍ አላስኛት ብሎ የኖረው የሉሙምባ የአገዳደል መንፈስ ከ39 ዓመታት በኋላ በእጅጉ የሚያሳስብ ርእሰ ጉዳይ ሆነ:: የሉሙምባ አገዳደል ጭካኔና ግፍ የተመላበት መሆኑን ያረጋገጠው በአዲስ መልክ ተከፋፍሎና የቤልጅግን ቤተ መዛግብት የመረጃ ቋት መሠረት አድርጎ በዶ ዊቴ የታተመው አዲስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ያረጋገጠው የቀድሞው የቤልጅግ የቅኝ አገዛዝ መንግሥት በመጨረሻ ሉሙምባንና ሁለት ተባባሪ ጓደኞቹን ለመግደል እቅድ እንዴት እንዳወጣ ብቻ ሳይሆን ወንድማማቾቹ የጦር መኮንኖቹም ጉዳዩን እንዴት እንዳስፈጸሙ ጭምር ነው:: ይህንን ግፍ የተመላበት ግድያ አንድ የቤልጅግ የጦር  መኮንን  ከታናሽ ወንድሙ ጋር የፈጸሙት መሆኑን አምኖ፣ በቤልጅግ ቴሌቪዥን ከመናገሩ ባሻገር ሉሙምባንና ሁለት ጓደኞቹን ከገደሉዋቸው በኋላ መረጃ እንዳይገኝ ሰውነታቸውን በቆንጨራ ከታትፈው፣ ቆራርጠውና በመርዘኛ የሰልፈር አሲድ ፈሳሽ ውስጥ ጨምረው እንዳጠፏቸው አስረድቷል፡፡
በወቅቱ “የቤልጅግ ጠላቶች ናቸው” በሚል እሳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ ጋር ተገድለው፤ ተቆራርጠውና መርዝነት ባለው ኬሚካል ተጠቅልለው እንደ አልባሌ ዕቃ የተጣሉት ጓደኞቹ ዮሴፍ አኪቶ፤ የኮንጎ ምክትል ፕሬዚደንት፤ ሞሪስ ምፖሎ፤ የማስታወቂያ ሚኒስትር መሆናቸው ተገልጧል፡፡ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት የሰጠው የቤልጅግ ፓርላማ በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 9 ቀን 1999 በአደረገው ስብሰባ ስለ ሉሙምባ አሟሟት የሚያጣራ እና የቤልጅግም ኃላፊነት ምን መሆን እንዳለበት የሚወስን መርማሪ ኮሚሽን  አቋቁሞ ነበር፡፡ በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው በሉሙምባ የአገዳደል ድራማ ዋነኛዋ ተዋናይ ቤልጅግ ብቻ ሳትሆን  አሜሪካ ጭምር ናት፡፡ ይህንን ጉዳይ የቤልጅጉ ጋዜጠኛ ፍራንሴስ ሚሰር “ሉሙምባ የተደበቀው እውነት” በሚለው ዘገባው  ኦሴይ ቦተንግ በተባበሩት መንግሥታት ስለ አሜሪካ ጣልቃገብነት የተነተነውን እና ብዙ የአውሮፓ ከተሞችን ያስደነገጠውን ታሪክ ጠቅሶ  ዋነኛ ርእሰ ጉዳይ በማድረግ ጸፏል፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ በኮንጎ  የነጻነት ትግል ታላቅ ሚና የተጫወተ የፖለቲካ መሪ ሲሆን ያደረገው ተጋድሎም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ጭምር ዝነኛ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
በዚህ ዓይነት የሩሲያ መንግሥት ሞስኮ ውስጥ “ፓትሪስ ሉሙምባ  ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ዩኒቨርሲቲ” በሚል በስሙ የትምህርት ተቋም ሰይሞለታል:: ከዚህም ዩኒቨርሲቲ በርካታ የአፍሪካና የዓለም ወጣቶች በያመቱ በከፍተኛ ማዕረግ ይመረቁበታል፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ማለትም እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ዓመታት ላይ ጠንካራ ከነበሩት የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለሦስት ወራት ያህል አገሩን የመራው ሉሙምባ ከመገደሉ  ከሳምንት በፊት ለባለቤቱ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፎላት ነበር፡፡            
“ክብርት ባለቤቴ! ይድረስሽ አይድረስሽ ባላውቅም እነዚህን ቃላት ልኬልሻለሁ:: ደርሰውሽ የምታነብቢያቸው ከሆነ እስከ አሁን  በሕይወት ያለሁ መሆኔን ትረጃለሽ፡፡ እኔ እና ጓደኞቼ ለሀገራችን ነጻነት የምናካሔደው ትግል በመጨረሻ በድል እንደሚጠናቀቅ፤ቅኝ ገዥዎችና ወራሪዎችም እንደሚባረሩና ወደ መጡበት ሀገር እንደሚመለሱ ለአፍታም ያህል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ለዚህም ሕይወታችንን እንሰጣለን፡፡ ለሀገራችን የምንመኘውም የተሟላ መብት፤ክብር ያለው ሕይወት፤ የማይደፈር ማንነትና ገደብ የሌለው ነጻነት ነው፡፡ ይህም በቤልጅግ ቅኝ ገዥዎችና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ በሚያደርጉላቸው የምዕራብ ተባባሪዎቻቸው ሊታሰብ የማይገባውን ነጻነት ማለታችን ነው፡፡ ወይም ሁለቱም አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ልክ እኛ አባል የሆንበት የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣኖችን እገዛ ስንፈልግ የሚደረግልንን እርዳታ ዓይነት ማለት አይደለም፡፡ ለጥቂት ዐርበኞቻችንና ለሌሎች (የቤልጅግ ቅኝ ገዥዎች) ማባበያና ጉቦ እየሰጡ፤እውነታውን እያጣመሙ ለነጻነት የምናደርገውን ተጋድሎ ያጓትቱብናል፡፡ ምን ማድረግ እችላለሁ?
              
ባለቤቱ ፓውሊን የሉሙምባ ደብዳቤ ከእሥር ቤት በደረሳት ጊዜ ስታነባ

በቅኝ ገዥዎች ትእዛዝ ሞትኩም፤ ዳንኩም፤ ታሰርኩም፤ ተፈታሁም እኔ ብቻ የማደርገው አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህንን (ትግል)ተግባራዊ የምናደርገው ኮንጎና  ነጻነት ወደ እስር ቤት የተቀየሩባቸው ድሆቹ ሕዝቦቻችን ናቸው፡፡ እና የውጭው ዓለም አንዳንዴ በደግነትና አንዳንዴ ደግሞ በደስታና በእርካታ እየፈረጀ ሱባኤ እንደገባን አድርጎ የሚመለከተን ወገን ሳይሆን ወሳኞቹ  እኛው ነን፡፡ ስለዚህ  እምነቴ ሳይናወጥ ይቀጥላል፡፡ የሚገባኝና በልቤም የሚሰማኝ ነገር ቢኖር አሁንም ሆነ ወደፊት ሕዝቦቻችን የውጭም ሆኑ የውስጥ ጠላቶቻችንን ራሳቸው እንደሚያባርሯቸው ነው፡፡ እንደ አንድ ሰው ሆነውም “ከእንግዲህ በቅኝ ገዥዎችና በመጤ ወራሪዎች የምንዋረድበትና የምንሸማቀቅበት ጉዳይ አይኖርም፡፡” እያሉ በመታገል ክብራቸውን የሚጎናጸፉበት ጊዜ መድረሱን ያሳዩዋቸዋል፡፡ ለተለየኋቸውና ምናልባትም እንደገና ተመልሼ ለማላያቸው ለልጆቼም የምነግረው የማካሂደው ትግል ለእነርሱና ለእያንዳንዱ ኮንጎ ዋዊና አፍሪካዊ ጭምር መሆኑን ነው፡፡ የተቀደሰችዋን ነጻነታችንን እንደገና ለመቀዳጀትና ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር መሥዋዕትነት መክፈል አስፈላጊ መሆኑን እናገራለሁ፡፡ ያለ ክብር መብት የለም፡፡ ያለ ፍትሕ ክብር የለም:: ያለ ነጻነት ደግሞ ነጻ ሰዎች አይኖሩም፡፡ ዐረመኔያዊ ድርጊት፤ጭካኔም ሆነ ሥቃይ የበዛበት ግርፋት ተምበርክኬ  ከቅኝ ገዥዎች ይቅርታና ምሕረት እንድጠይቅ አያደርጉኝም፡፡ ይህን ከማደርግ እና የመሥዋዕትነትን መርሕ ባለመቀበል በጭቆና እና በውርደት ከምኖር ለሀገሬ ከአለኝ ታላቅ ክብር፤ ጥልቅ ፍቅር እና የጸና እምነት ጋር ሳላጎበድድ እና ሳልንበረከክ ከነ ክብሬ መሞትን እመርጣለሁ:: ታሪክ አንድ ቀንትክክለኛውን: ፍርድ:ይሰጣል ግን ይህ ታሪክ በብሩሴልስ፤  በፓሪስ፤ በዋሽንግተን፤ በተባበሩት መንግሥታት የሚያስተምሩት አይደለም፡፡ ነገር ግን ከቅኝ አገዛዝና ከአሻንጉሊቶቹ  ነጻ በወጡ  አገሮች ውስጥ የሚያስተምሩት እንጂ፡፡ አፍሪካ ለደቡብና ለሰሜን ሰሓራ አገሮች ታሪኳን መጻፍ አለባት፡፡ ምክንያቱም ይህ  አንጸባራቂና ታዋቂ ታሪክ  ስለሆነ ነው፡፡
የተከበርሺው ውድ ባለቤቴ  ለእኔ ብለሽ አታልቅሽ፡፡ በብዙ መከራ በመሠቃየት ላይ ያለቺው ሀገሬ  ነጻነቷን  እና መብቷን እንዴት  አድርጋ ለማስከበር እንደምትችል ታውቅበታለች፡፡ ኮንጎ ለዘለዓለም ትኑር፤ አፍሪካ  ለዘለዓለም ትኑር፡፡”
 እኤአ በጥር አጋማሽ 1961 ይህ ደብዳቤ የተላከላት ሴት ፓውሊን ሉሙምባ ናት:: ጸሐፊው ደግሞ የኮንጎ  የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ ሲሆን የጻፈላት ሊገደል ሳምንት ሲቀረው ነው፡፡“ ክብርት ባለቤቴ ሆይ! ለእኔ ብለሽ አታልቅሺ፡፡ ታሪክ አንድ ቀን ትክክለኛውን ፍርድ ይሰጣል፡፡” ብሎ ሉሙምባ ሲጽፍ አንድ ቀን ያለው አንድ ቀን ባልታሰበ ሁኔታ የነጻነት ጎሕ ለኮንጎ  ሕዝብ የሚወጣለት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ስለ ሉሙምባ አገዳደል ግልጽ ምርመራ እንዲካኼድ በቤልጅግ ፓርላማ የተወሰነው  በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚስተር ጉይ ቬርሆቭስታትድ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሚስተር ሉዊስ ሚቼል አሳሳቢነት ነው፡፡ ሁለቱም ሰዎች በደች ቋንቋ በሉዶ ደ ዊቴ በተጻፈው አዲስ መጽሐፍ (ዶ ሙርድ ኦፕ ሉሙምባ) ድንጋጤ ተሰምቷቸዋል:: መጽሐፉ የታተመው በቫን ኃሌውርስክ ሉቬይን  ቤልጅግ ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፉ በፈረንሳይኛ ጭምር ተተርጉሞ የወጣ ሲሆን በእንግሊዝኛ ግን የትም ተተርጉሞ አልታየም፡፡ ግን፤ እስከ አሁን ተተርጉሞ ሊሆን ይችላል፡፡ በደች ቋንቋ የተጻፈው ዋናው መጽሐፍ ግን በቤልጅግ መገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚስተር ጉይ ቬርሆቭስታትድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሚስተር ሉዊስ ሚቼል ሊቋቋሙት የማይችሉት ተቃውሞ፤ግን አንድ ነገር ለማድረግ የሚያስችላቸውን ችግር አስነሥቶባቸዋል፡፡
የሥነ ሰብእ (ሶሺዎሎጂስት) ተመራማሪ የሆነው ዶ ዊቴ በመጽሐፉ ውስጥ የእሥረኞችን ታሪክ አልጻፈም:: እውነታን መሠረት አድርጎ እንዲህ አለ:: “ቤልጅግ በሉሙምባ አገዳደል ላይ ታላቅ ኃፊነትን ወስዳለች፡፡
ቤልጂግ  ሉሙምባ ከተዛወረበት እና ከተሠቃየበት ከካታንካ ጀምሮ አካሉ ተቆራርጦ ደብዛው እስከጠፋበት ድረስ የነበረውን  ቅንብር ተከታትላ እውነታውን የማውጣት ኃፊነት አለባት::” የቤልጅግን ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት በደረጃ የመከፋፈል አጋጣሚውን  እንዳገኘው  እንደ ዶ ዊቴ እምነት ከሆነ፤ ሉሙምባን ለመግደል የተወሰነው በቤልጅግ ባለሥልጣኖች ሲሆን ይኸውም የኮንጎ  የነጻነት ቀን እኤአ ሰኔ 30 1960 እና ሐምሌ 14ቀን 1960 ከተከበረ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው:: በወቅቱ የቤልጅግ አምባሳደር በሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አገሮች ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ባሰማው ንግግር፤ “አሁን ያለው ነበራዊ ሁኔታ የተሻለ ሊሆን የሚችለው የኮንጎ ፕሬዚዳንት ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ፓትሪስ ሉሙምባ) እና የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሲወገዱ (ሲገደሉ ነው)” ብሏል:: በእርግጥም የብሩሴልስ ባለሥልጣኖች ንጉሣቸው ንጉሥ ሊዎፖልድ ባውዶዊን በኮንጎ  ብሔራዊ የነጻነት ቀን በዓል ላይ ተገኝቶ በነበረበት ሰዓት የነጻነት ታጋዩ ፓትሪስ  ሉሙምባ “ለኮንጎ  ሕዝብ ባርነትን እና ጭቆናን ያመጡበት  ቤልጅጎች ናቸው” ብሎ እና ሕዝቡ የደም ዕንባ እያነባ እና እየተበሳጨ  ከሚኖር፣ ለአርነቱ እና ለነጻነቱ መታገል  ያለበት መሆኑን ጠቅሶ፤ ለሕዝቡ በአሰማው ኃይለኛ እና ጠንካራ ንግግር ይቅርታ ሊያደርጉለት አልቻሉም:: በወቅቱ የሉሙምባ ንግግር የቤልጅጉን ንጉሥ ባውዶዊንን  በእጅጉ ያበሳጨው ሲሆን፤ በተቃራኒው በኮንጎ  ብሔራዊ የነጻነት ቀን አደባባይ ላይ ተገኝቶ የሉሙምባን ንግግር የሰማውንና በኮንጎ  መገናኛ ብዙኃን የተከታተለውን እያዳንዱን ዜጋ ስሜቱን ነክቶትና ቁጭት ላይ ጥሎት ነበር::
ከዚህም የተነሣ ብሩሴልስ በሉሙምባ ላይ የነበራትን ቂም ልትረሳ አልቻለችም፡፡ ይኸውም ሉሙምባ የቤልጅግ ወታደሮች ከኮንጎ  ጦር ሠራዊት እንዲሰናበቱና እኤአ ሐምሌ 11 ቀን 1960 በመርዲ የወደብ  ከተማ ላይ ቦምብ አፈንድተው ጥቂት የአውሮፓ ዜጎችን ጨምሮ ንጹሐን የኮንጎ  ዜጎችን የገደሉት የቤልጅግ ቅኝ ገዥ ወታደሮች አገር ለቅቀው እንዲወጡ በማድረጉ ነው:: ፓትሪስ ሉሙምባ እንዲወገድ ቤልጅጎች ያቀነባበሩት ስልት በአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቶ ነበር፡፡ ይኸውም በአሜሪካ መንግሥት እምነት ኮሙኒስቱ ፓትሪስ ሉሙምባ የሩሲያን ጦር ሠራዊት በመጋበዝ እኤአ ግንቦት 8 እና ሐምሌ 11 ቀን 1960 ነጻ የወጣችውን የደቡብ ካሳይን ግዛትና ተገንጣይቱን የካታንካ ክፍለ ሀገር ለመቆጣጠር አስቧል በሚል ሥጋት ነው፡፡ በመሆኑም ሉሙምባን ለማስወገድ በብሩሴልስ የተጠነሰሰውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ አሜሪካ ዋነኛ አቀንቃኝ ሆና ተሰለፈች፡፡ በማዴሊን ካልብ  አማካኝነት እኤአ 1982 “ኮንጎ  ኬብልስ” በሚል በማክሚላን የታተመው መጽሐፍ ከመንግሥት ምክር ቤት አፈትልኮ የወጣን መረጃ መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ እንደ መረጃው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ዶ አይዘናዎር ሉሙምባን ለማስገደል በያዘው ረጅም እቅድ መሠረት፤ ለስለላ ድርጅቱ ሲ አይ ኤ (CIA) የመግደል ፈቃድ ሰጥቶ ነበር:: ከመጽሐፉ ለመረዳት እንደሚቻለው፤ የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት (የስለላ ድርጅት) አባል የነበረው ሮበርት ጆንሰን፤ እ.ኤ.አ በ1975 በድርጅቱ (NSC)  ስብሰባ ላይ ቀርቦ በሰጠው የምስክርነት ቃል ሲናገር፤ “እኤአ ነሐሴ 18 ቀን 1960  ፕሬዚዳንት አይዘናዎር አንድ ነገር ተናገረ:: የተናገረውን ቃል ግን ለማሰታወስ አልችልም፡፡ ሉሙምባን ለማስገደል የሰጠው ትእዛዝም ሊመጣልኝም አልቻለም ” የሚል ነው፡፡ እኤአ ነሐሴ 1960 በተደረገ  የጥቂት ደቂቃዎች ስብሰባ ግድያውን የሚያስፈጽም የተወሰነ ኮሚቴ በምሥጢር እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡ በስምምነቱ ላይ “በመጨረሻው እቅድ መሠረት የተደረሰበት ስምምነት፤ ኮንጎ  የማንኛውንም የአገዛዝ መርሐ ግብር ማለት የሉሙምባን የነጻነት መንፈስ እንደገና እንድትቀበል ጭምር አስተዋጽኦ የሚያደርግ እና ይህን ሐሳብ የሚያስለውጥ ማለት አይደለም” የሚል ሐሳብ ሰፈረ፡፡
የቤልጅጉ ንጉሥ ሊዎፖልድ ባውዶዊን በኮንጎ  ብሔራዊ የነጻነት ቀን በዓል ላይ
ተገኝቶ ለሕዝቡ  ሰላምታ ሲሰጥ   

Read 3436 times