Sunday, 02 August 2020 00:00

(የአጭር አጭር ልብወለድ)

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(12 votes)

  የቁም ቅዠት
                           
            ውድቅት ላይ ነው፡፡ ጧ ያለ እንቅልፍ ላይ ነኝ፡፡ ግን እረፍት የለሽ ነፍሴ ትቃትታለች፡፡
ይመስለኛል !... የአያቴ ቤት ነው፡፡ ፊት ለፊቱ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የሚገማሸር ወንዝ አለ፡፡ ህፃናት ጠርዙን ይዘው ተኮልኩለዋል:: በእጃቸውና በእግራቸው እንደ ልብ ያንቦጫርቃሉ፡፡ በደስታ ማዕበል ይከንፋሉ:: ይራጫሉ፡፡ ይራጫሉ፡፡ ግና አንድም ሰው ጉዳዬ አላላቸውም፡፡ ህልም የራስ ነውና ይቀዝፋሉ፡፡ ወንዙም ይከንፋል፡፡ ጥልቀቱ አስፈሪ ቢሆንም ከጉዳይ አልጣፉትም፡፡
ወንዙ ውስጥ ያሉትን አዞዎች ባሰብኩ ጊዜ ህሊናዬ  ተናወጠ፡፡ “ህፃናቱን ከልክሏቸው!” በማለት ተናዘዝኩ፡፡ አክስቴ  ግን “ #ምን ታንባርቃለህ? ህፃን ተጫውቶ ነው እሚያድገው፡፡ ደሞ ያርባ ቀን እድሉ ከሆነ ጮኸህ አታስቀረው” ከማለቷ አንድ ህፃን በአዞ ተበላ፡፡
ኡኡኡኡኡ....አልኩ፡፡ የሚሰማኝ ግን አጣሁ፡፡ ከድንጋጤዬ ብዛት ሰውነቴ አቅም አጣ፡፡ መነሳት ተሳነኝ፡፡ በተቀመጥኩበት ዳከርኩ፡፡ የህልም እሩጫ ሆነብኝ፡፡  ደግሞ ሌላ ህፃን ተበላ፡፡ ጉልበቴ ተብረከረከ፡፡ ባለሁበት የድረሱላቸው ጩኸት ባሰማም (የሚሰማኝ) የሚነሳ የለም፡፡
የጭንቅ ሩጫዬን ጀመርኩት፡፡ እያየኋቸው፤ እየቀረብኳቸው ግን ራቁኝ:: ሁሉም በድንጋጤ ፈዘዋል፡፡ እጮሀለሁ፡፡አንዳቸውም ለማምለጥ አይጥሩም፡፡ ወንዙ እያጓራ ይነጉዳል፡፡ አዞዎቹ ይቃማሉ፤ እርስ በርስ ይታገላሉ፡፡ አሞራ ከላያቸው ያንዣብባል፡፡
አጎቴ ከታች እየጮኸ ቀድሞኝ ደረሰ፡፡ ህፃናቱን እየነጠቀ፤እየገፈተረ ወረወራቸው:: ባረቀ፡፡ ሰሚ አጣ፡፡ ተወራጨ፡፡ በእጁም በአይኑም ከዚህ ጥፉ አላቸው፡፡ እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ ወደ እኔ ዞረ፡፡ ከደሙ ነፃ ነኝ ለማለት ያክል ...ጣቴን ወደ አያቴ ቤት ቀሰርኩ፡፡ መልስ ሳይሰጠኝ ተንደርድሮ ገባ፡፡ ግን ምንም አልተፈጠረም፡፡ ለምን ???
ከአዘጋጁ፡-ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡



Read 4167 times