Saturday, 01 August 2020 13:24

የልጆች ጥግ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ውድ ወላጆች ሆይ!!
ለልጆቻችሁ ጊዜ ስጡ
ከልጆቻችሁ ጋር ጥልቅ ግንኙነትና ቅርብ ትውውቅ መስርቱ፡፡ በየዕለቱ ከልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፉት በቂ ጊዜ ይኑራችሁ፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ በመቀመጣቸው ብቻ ግን ከልጆቻቸው ጋር በቂ ጊዜ እያሳለፉ ነው ማለት አይደለም፡፡ ልጆች በየራሳቸው ጨዋታ ተወጥረው፣ ወላጆችም ኮምፒዩተራቸው ላይ ተደፍተው ኢ-ሜይል የሚመለከቱ ወይም ኢንተርኔት የሚበረብሩ ከሆነ አንድ ላይ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡
ወላጆች፤ ከልጆቻችሁ ጋር የጨዋታ ጊዜ ይኑራችሁ፡፡ መሬት ላይ አብራችኋቸው እየተንከባለላችሁ ተጫወቱ፤ ተላፉ፤ ተቀላለዱ፤ ተረት ንገሯቸው፤ እንቆቅልሽ ጠይቋቸው፤ መጻሕፍትም አንብቡላቸው፡፡ ስለ ት/ቤት ጓደኞቻቸው ጠይቋቸው፡፡ ስለ ት/ቤታቸው ወይም አስተማሪዎቻቸው ምን እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ለማወቅ ሞክሩ፡፡  
አድማሳቸውን አስፉላቸው
ለልጆቻችሁ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከቅርብ ጓደኞቻቸው ውጭ ያለውን ዓለም አስተዋውቋቸው፡፡ የብሔር፣ ፆታ፣ ሃይማኖትና ባህል ልዩነቶችን እንዲቀበሉና እንዲያከብሩ አስተምሯቸው፡፡
በሌሎች የዓለም ክፍሎች ስለሚገኙ ሥፍራዎች፣ ባህሎች… ልማዶች… የአኗኗር ዘይቤዎች ዕውቀትና ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ አስተምሯቸው፤ ንገሯቸው፡፡ ይህን በማድረጋችሁም የዕይታ አድማሳቸውን ታሰፉላችኋላችሁ፡፡
በተግባር አሳይዋቸው  
ልጆቻችሁ እንዲሆኑ የምትሹትን በቃል ወይም በምክር መልክ ከመንገር ይልቅ ሆናችሁ አሳይዋቸው፡፡ ለምሳሌ ደግነትን፣ ትህትናን፣ አክብሮትን፣ ሃቀኝነትን ጨዋነትን ወዘተ--- በዕለት ተዕለት ህይወታችሁ እየሆናችሁና እየኖራችሁ አስተምሯቸው::
የቤት ሠራተኛዋን ወይም ሞግዚቷን በትህትና በማናገር፣ የተቸገረን በመርዳት፣ ለታላላቆች አክብሮት በማሳየት ወዘተ--በበጐ ሥነምግባር ልትቀርጿቸው ትችላላችሁ፡፡ ልጆቻችሁ እንዲሆኑ የምትሹትን ሆናችሁ ማሳየት ወይም ማስተማር አንድ ነገር ነው::
በሌላ በኩል፤ በልጆቻችሁ መሃል ስለ ልዩነትና ጥላቻ ማውራት፣ እንዲሁም ሃሜትና ክፉ ቃላትን መወርወር የልጆች ባህርይ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራልና ከዚህ ድርጊት ተቆጠቡ፡፡
የማድነቅ ፋይዳ  
ለልጆቻችሁ አቅማቸውን የሚመጥን ሥራ ሰጥታችሁ በአግባቡ ሰርተው ግዴታቸውን ከተወጡ፣ ሳትሰትቱ  በወጉ አድንቋቸው፡፡
ከተቻለም ሸልሟቸው:: በተጨማሪ፤ በትምህርታቸው ወይም በጂምናስቲክ አሊያም ደግሞ በተሰጥኦ ውድድር ግሩም ውጤት ሲያመጡም አድናቆታችሁን ከመቸር ወደ ኋላ አትበሉ:: ከአድናቆትም ባሻገር እንደ ማበረታቻ ሽልማት አበርክቱላቸው::
(ሽልማቱ ምንም ሊሆን ይችላል) ዋናው ቁምነገር ልጆቹ ለጉብዝናቸው ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተላቸው መሆኑን መገንዘባቸው ነው፡፡ ልጆች፤ እየተደነቁና እየተመሰገኑ ካደጉ፤ እነሱም  በተራቸው አድናቂና አመስጋኝ ይሆናሉ፡፡


Read 1630 times