Saturday, 01 August 2020 13:28

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ሞት  ማስደንገጥ ሲያቅተው
ሞት ማስደንገጥ ሲያቅተው
ያን ጊዜ ነው
ምን መሆኔን የማላውቀው፡፡
    ነፍስ ነስጋ ስትለይ
    ተመልሳ ላትከተት
    የእንቁላል ዘመኑን አልፎ
    ሰብሮ እንደወጣ ነፍሳት
    እንኳን በግፍ ተሰርቃ
    እንደሷ ሕይወት ባዘለ
    በመሰሏ እጅ ተነጥቃ
    በእንቅልፍ ዓለም እንኳን
    ጀንበር ሲጠባ ባታይ
    ለወትሮው
    የቋሚው የውስጥ ለቅሶ
    የኗሪው የውስጥ ብካይ
    በቋሚው ውስጥ ነፍስ እንዳለ
    የሚያሳይ ምልክት ነበር
    ሰውን እንደ ሰው ሲያከብር
ምክንያት ለማዳን እንጂ
ጥብቅናው ለሞት ከሆነ
ልቤ
ህልፈት ካደነደነው
ነፍስ ሲጠፋ ካላዘነ
ማልቀስ ያለብኝ ለኔ ነው
በውስጤ ሕይወት ለሞተው
የፍትህ ዘር ለማልዘራው
የሰው ሞት ካደነደነኝ
ማልቀስ ያለብኝ ለኔ ነው፡፡
ከበደች ተክለአብ
እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ጁላይ 2020


Read 2346 times