Saturday, 08 August 2020 12:06

“ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፤ “በግጥም ሃሳብን ለመግለጽ” በሚል ርዕስ የፃፉትን ታሪክ ወደ ስድ ንባብ ስንቀይረው የሚከተለውን ስነ ተረት ይመስላል፡፡
አንድ ገጣሚ ያጋጠመውን እንዲህ ሲል ተረከ፡-
የሚተርከው ለአንድ ፈላስፋ ነው፡፡
“ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ንጉስና ንግስቲት ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ይኖሩ ነበረ፡፡ እስካሁን ልጅ አልወለዱም፡፡ መንግሥቱን የሚመራና ዙፋኑን የሚወርስ ልጅ ለማፍራት ይፈልጋሉ፡፡ ውለው አድረው አንድ ወንድ ልጅ ወለዱ፡፡ ሰፈርተኛው ባለሥልጣን ንጉሣዊ ቤተሰብ የተለያዩ የውጭ ሀገር እንግዶች ሁሉ ተገኙ፡፡ እንኳን ማርያም ማረችሽ ለማለት የመጡ ናቸው፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ሙገሳና እንኳን ደስ አልዎት ብለው ለንጉሡ ደስታቸውን ለመግለጽ ተዘጋጅተው የመጡት አያሌ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ “በሉ የልጁን፣ የልዑሉን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ምኞታችሁን ተናገሩ፡፡” አሉ ንጉሡ፡፡
ሳይንቲስት ተነሳና “ይሄ ልጅ ሃኪም ይሆናል” አለ፡፡
ሰው ሁሉ አጨበጨበ፡፡
ቀጥሎ የቤተክህነቱ ሹም ተነሱና “ይሄ ልጅ ጳጳስ ይሆናል” አሉ፡፡
ሰው ሁሉ በጭብጨባ ደስታውን ገለፀ፡፡
ሌላው ሰው ተነሱና “ይሄ ልጅ ያለጥርጥር ጀነራል የአገራችን የጦር መሪ ነው የሚሆነው፡፡”
ሰው ከሁሉም የበለጠ ጭብጨባ አሰማ፡፡
ሌላው የመጨረሻው ሰው ተነሳና የተለየ ነገር ተናገረ፡፡
እንዲህ አለ፡- “ሁላችሁም ያላችሁት ሊሆን የሚችልና ልዑላችንም ያለጥርጥር ሊካንበት እድሉ ሰፊ የሆነ ነገር ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ምንም ቢባል ምንም ከመሆን የማይቀር ነው፡፡”
ሁሉም “ንገረና ምንድነው ከመሆን የማይቀረው ያልከው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
የመጨረሻው ሰው ሲመልስም፤ “ይሄ ልጅ አንድ ቀን ይሞታል” አለ፡፡
በቤተ መንግሥት የነበረው ሰው ሁሉ ከፋው፡፡ ተቆጣ፡፡
ሟርተኛ አለው - አንዱ፡፡
ጥቁር ምላስ አለው - ሌላው፡፡
“ይሄ ሰው የመንግሥታችንና የንጉሣችን ጠላት ነው አሉ” ሌሎቹ፡፡
“ይሄን ሰው ሁለተኛ አይኑን እንዳናይ፤ ሠፈራችን እንዳይመጣ፤ ሠይጣን ዲያብሎስ” እያሉ ጥንብ እርኩሱን አወጡት፡፡ ሌላም ሌላም እርግማን አወረዱበት፡፡ አንዳንዶቹ ለጠብ ተጋበዙ፡፡ ጥቂቶቹ በዱላ አነከቱት፡፡
“ፈላስፋ ሆይ! ያጋጠመኝ ይህ ነው፤ አየህ እኔ ሀቀኛ ሰው ስለሆንኩኝ መዋሸት አልፈልግም፤ እውነት ተናግሬ ደግሞ መቀጥቀጥ አልሻም፤ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም አንተ በኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ፈላስፋውም “ወዳጄ፤ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥምህ “ኦሆሆ! አሀሀ!” እያልክ መውጣት ብቻ ነው” አለው፡፡
*   *   *
ከጉዳይ ሁሉ ክፉ አላስፈላጊ መስዋዕትነት መክፈል ነው፡፡ ከድርድር ሁሉ ክፉ አስቀድሞ ባለቀ ጉዳይ ላይ መነታረክ ነው፡፡ በዘመናዊ አነጋገር በተበላ እቁብ ላይ መጨቃጨቅ ነው፡፡ ጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜን፣ ንብረትንና አቅምን ከማባከን የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አባባል፤ “riding dead horse” (በሞተ ፈረስ መጋለብ ነው፡፡) የእነግብጽ አካሄድ ይሄን ይሄንን ያጠቃልላል፡፡ ሃገራችን “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” ብላ መልካምና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ጥበብን የተላበሰ ጉዞ አካሂዳለች፡፡ ሚስጢር በወጉ ካልተጠበቀ የባቄላ ወፍጮ ነው በማለትም ተገቢ ጥንቃቄ አድርጋለች፡፡ ማስፈራሪያና ፕሮፓጋንዳ ሳይበግራትም አፀፋውን እየመለሰች የመጀመሪያ የውሃ ሙሌቷን በስኬት ተወጥታለች፡፡ ገና ግን በጥበብ ፣ በብልሃት፣ በፖለቲካ ብስለት፤ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ እንዳትሆን አድርጋ መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ ትዕግስት አስፈላጊ መሆኑን የማወቃችንን ያህል፣ ፍርሃት እንዳልሆነም በቅጡ እናውቃለን፡፡
የውሃ ሙሌት ብቻ ሳይሆን የልብ ሙሌትም ያስፈልጋል፡፡
“ወባህነ”
“ወከመ ዘኢነኢባህነ ኮነ” አለች ይላል፤ ውሻ፡፡ ይላል የግዕዙ ትርጓሜውም፡-
“ጮህን ጮህን
እንዳልጮህን ሆንን”   
ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን የጮህንላቸውን ፍሬ ጉዳዮች አለመርሳት ተገቢ ነው፡፡
“የረጋ ወተት ቂቤ ይወጣዋል” ብለናል፡፡
ቆራጥነትና ሃሞተ መራር መሆን ያስፈልጋል ብለናል፡፡
“ኧረ ምረር ምረር ምረር እንደ ቅል
አልመርም ብሎ ነው ዱባ እሚተከል” ብለናል፡፡
ህግን ተንተርሶ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ መጠነ ሠፊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንርሳ፡፡
“ነገሩ አልቆም ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር
ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር” ብለናል፡፡
የሞላና የጐደለውን፤ የጠጠረና የላላውን ለይቶ የፖለቲካ ጥብቅነትን መጠበቅ ያሻናል፡፡
“ከሚጋልብ ፈረስ፣ መንገድ የምታውቅ ታሪክ ትሻላለች” ብለናል፡፡
“ከጥንት ጀምረን እኛ እንደምናውቀው
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው” ብለናል፡፡
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ” ብለናል፡፡
ጅማሮዎቻችንን እናጢን፡፡ የቀሩንን እናስላ፡፡
“ያረፈ የሊጥ ሌባ…” ተባብለናል፡፡
በመጨረሻም “እማማ ሰነፏን” እናስታውሳለን፡፡
እማማ ሰነፏ ምርጥ ባለሙያ ጠላ ጠማቂና ሻጭ ናቸው፡፡ ጠላቸው በጣም ጣፋጭ ነው፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ግቢያቸው ከአፍ እስከ ገደፉ ይሞላል፡፡
ታዲያ እድሜ ልካቸውን በሳምንታት አንድ ቀን ይጠምቁና፤ ያቺ ቀን ስታልፍ ደሞ የጠላው ጊዜ እስኪደርስ ለጥ ብለው ይተኛሉ፡፡ ለዚህ ነው እማማ ሰነፏ የተባሉት፡፡ አድናቂያቸው ጠላ ጠጪም ቶሎ ቶሎ ደጋግመውና አሳምረው ጥመቁ አይልም፡፡ እሳቸውም ተፎካካሪ ይመጣብኛል ብለው አይሰጉም፡፡ ወይም በርከት አድርገው የመጥመቅ እቅድ የላቸውም፡፡
ከእማማ ሰነፏ የምንማረው ነገር አለ፡፡ ለአንድ ሰሞን ብቻ የሚደረግ ዘመቻ ምንም ያማረ ቢሆን፤ ከዚያ መታቀብ ከዘላቂ ልማት ጋር ይጋጫል፡፡ የመጀመሪያው የግድቡ ውሃ ሙሌት በአያሌው ተደንቋል፡፡ ከዘላቂ ግብ አኳያ ግን ብዙ መንገድ ይቀረዋል፡፡
ችግኝ ተክለን፤ ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
ግድብ ሞልተን ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
እጃችንን ታጥበን ጭንብል አጥልቀን ተራርቀን…ቀጥሎስ? ማለት አለብን፡፡
…ቁጥጥርና ግምገማስ መቼ እናድርግ ማለት አለብን፡፡ ዲሞክራሲውስ ምን ያህል አደገ? ጐለበተ? ምን ያህል ከሌሎች የእድገት ጉዳዮቻችን ጋር ተሰናሰለ? ጐረቤቶቻችንስ ምን ሂደት ላይ ናቸው? የካሮትና የአርጩሜ ነገር እንዳይሆን፡፡
“Carrot and Stick” ሥርዓታችን እና መርሀችን የት ድረስ ሥራ ላይ ዋለ? ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችንስ የት ድረስ ሥራ ላይ ዋሉ? ትኩረትን በሰፊው የሚሹ ብዙ ጥያቄዎች አሉን፡፡ ተረካቢው ትውልድም ሆነ አስረካቢው አንጋፋ አቃጅ፣ አትጊ፣ አነቃቂና ውጤት ናፋቂ እንዲሆን፤ ሌት ተቀን ንቃትና ትምህርት ወደ ህዝቡ እንዲዘልቅ፣ ጥርት ባለ መንገድ፣ ዛሬ የወቅቱ ጥያቄያችን ነው፡፡ አንድን ግብ ለማሳካት ድካምና መስዋዕትነት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት በሚያጋጥመን ሰዓት ዘላቂውን ግብ እያሰብን፣ ትናንሾችን ችግሮች በትዕግስት ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ አይጢቱን ለመምታት አብረን ምጣዱን እንዳንሰብረው፡፡ “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” ማለት አለብን፡፡

Read 12001 times