Saturday, 08 August 2020 12:12

የአቢሲኒያ ባንክ ሀዋሳ ዲስትሪክት ሰራተኞች ለተጎዱ ድጋፍ አደረጉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በቀጣዩ ሳምንት በኮቪድ - 19 ለተጐዱ ድጋፍ ያደርጋሉ
                                     
            የአቢሲኒያ ባንክ ሃዋሳ ዲስትሪክት ሰራተኞች በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከትና ግርግር፣ በሻሸመኔ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተለያዩ ድጋፎች ማድረጋቸውን የዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ተስፋዬ አስታወቁ፡፡ ሥራ አስኪያጁ እንደገለፁት፤ በዲስትሪክቱ ሥር ያሉ የ48 ቅርንጫፍ ሰራተኞችን በማስተባበርና ከአንድ ባለሀብት ያገኙትን ድጋፍ በመጨመር 300 ሺህ ብር ገደማ የሰበሰቡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 170ሺ ብሩን በማውጣት፣ በሻሸመኔ ንብረታቸው ለወደመባቸውና ጊዜያዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 250 አባወራዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ለእያንዳንዱ አባወራ 10 ኪ.ግ ዱቄት፣ 3 ሊትር ዘይት፣ አምስት ፓስታና ግማሽ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና መለገሳቸውን አብራርተዋል፡፡ በቀጣዮቹ 10 ቀናትም በቀሪው 130ሺህ ብር በሀዋሳ ለሚገኙ በኮቪድ - 19 ወረርሺኝ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አቢሲኒያ ባንክ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ አገራቸውን አገልግለው ጡረታ የወጡና  የጡረታ አበላቸውን ከአቢሲኒያ ባንክ ለሚቀበሉ 5ሺህ ያህል ጡረተኞች 8 ሚ.ብር በጀት በመመደብ፣ ራሳቸውን ከወረርሽኙ የሚጠብቁበትን የንጽህና መጠበቂያና ማስክ ድጋፍ ማድረጉንም ሃላፊው አውስተዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ እ.ኤ.አ በ1996 ዓ.ም በ131 ባለ አክሲዮኖች፣ በተከፈለ 17.8 እንዲሁም በተፈቀደ 50 ሚ. ብር ስራ የጀመረ ሲሆን በመላ አገሪቱ ያሉትን የቅርንጫፎቹን ብዛት 516 ያደረሰ ሲሆን 10 ዲስትሪክቶች እንዳሉትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት 3.1 ቢሊዮን ብር የተከፈለና 4ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ባለቤት ለመሆንም በቅቷል፡፡


Read 2376 times