Saturday, 08 August 2020 12:27

አቶ ልደቱ ያሉበት እስር ቤት ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከኢዴፓ በቀረበላቸው አቤቱታ መሠረት የፓርቲውን መስራችና አመራር አቶ ልደቱ አያሌውን የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታ መታዘቡንና በመልካም የእስር አያያዝ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን ለኮሚሽኑ በፃፈው አቤቱታ፤ አቶ ልደቱ አያሌው የአስምና የልብ ህመም እንዳለባቸው ጠቁሞ፤ የእስር አያያዛቸው ሁኔታ እነዚህን በሽታዎች ሊያባብስ ብሎም ለኮሮና ሊያጋልጥ የሚችል ነው የሚል ስጋት አለኝ ብሏል፡፡
አቶ ልደቱ ባሉበት እስር ቤትም ኮሮና ስለመግባቱ ከታሣሪው ከራሳቸው መረጃ ማግኘቱን የጠቆመው ፓርቲው፤ ቀድሞ ካለባቸው ህመም ጋር በተያይዞ ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም አቶ ልደቱ ቢሾፍቱ የሚኖሩት በጊዜያዊነት መሆኑንና ቋሚ አድራሻቸው አዲስ አበባ እንደሆነ በማመልከትም፤ ጉዳያቸውን አዲስ አበባ ሆነው የዋስ መብት ተፈቅዶላቸው እንዲከታተሉ ኮሚሽኑ ግፊት ያደርግ ዘንድ ጠይቋል ኢዴፓ ባቀረበው አቤቱታ፡፡
የፓርቲው አቤቱታ የደረሳቸው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለም፣ በነጋታው አቶ ልደቱ ወደሚገኙበት እስር ቤት በመሄድ ምልከታ ማድረጋቸውንና አቶ ልደቱን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችንም ማነጋገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ልደቱም ሆነ ሌሎች ታሣሪዎች በመልካም የአያያዝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፤ ነገር ግን ከእስር ቤቱ ጥበትና ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንና ለሚመለከታቸው አካላት የማስተካከያ ጥቁምታ ማቅረባቸውንም ፓርቲው ከኮሚሽነሩ ባገኘው ምላሽ መረዳቱን የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሠ አስረድተዋል፡፡  

Read 8897 times