Saturday, 08 August 2020 12:42

በአለማችን በየ15 ሰከንዱ 1 ሰው በኮሮና ይሞታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ኮሮና ቫይረስ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በመላው አለም በየ15 ሰከንዱ አንድ ሰው ወይም በየቀኑ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝና፣ ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበባቸው ቀዳሚዎቹ የአለማችን አገራት አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ህንድ እና ሜክሲኮ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ19.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ713 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስነበበው ወርልዶ ሜትር ድረገጽ፣ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 12.3 ሚሊዮን ያህል መድረሱን አስታውቋል፡፡ የተጠቂዎች ቁጥር ወደ 5 ሚሊዮን የደረሰባትና ከ162 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፤ ከአለማችን አገራት በተጠቂዎችና ሟቾች ቁጥር ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ ብራዚል በ2.8 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ95 ሺህ ሟቾች በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡ ህንድ በ1.9 ሚሊዮን ተጠቂዎች፣ ሜክሲኮ በ50 ሺህ ያህል ሟቾች ከአለማችን አገራት በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ድረገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
ቫይረሱ ከገባባቸው 188 የአለማችን አገራትና ግዛቶች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ ወይም 126 አገራት የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ሪፖርት ማድረጋቸው የዘገበው ሮይተርስ፣ በ80 በመቶ የአውሮፓ እንዲሁም በ70 በመቶ የእስያ አገራት የቫይረሱ ስርጭት እያደገና እየተስፋፋ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ባለፉት 5 ወራት በአለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ወጣቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ መጨመሩን የገለጸው የአለም የጤና ድርጅት፣  ከየካቲት መጨረሻ እስከ ሃምሌ ወር አጋማሽ በነበረው ጊዜ በቫይረሱ ከተጠቁ 6 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 15 በመቶው ወጣቶች መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአፍጋኒስታን አጠቃላይ ህዝብ አንድ ሶስተኛው ወይንም 10 ሚሊዮን ያህሉ በኮሮና ቫይረስ ሳይያዝ እንዳልቀረ በጥናት ማረጋገጡን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሙከራ በማድረግ ላይ ከሚገኘው ጆንሰን ጆንሰን ኩባንያ 100 ሚሊዮን ክትባቶችን ለመግዛት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈጸሙንና በቀጣይም 200 ሚሊዮን ተጨማሪ ክትባቶችን ለመግዛት ማቀዱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም፤ ሩሲያ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመጭው ጥቅምት ወር ለዜጎቿ ለመስጠት ማሰቧን ባለፈው ሳምንት ማስታወቋን ተከትሎ፣ የአለም የጤና ድርጅት ሩሲያ ክትባቱን ለማምረትና ለዜጎቿ ለመስጠት አለም አቀፍ መመሪያዎችን መከተል አለባት ሲል ዕቅዱን መቃወሙን ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በበርካታ የአውሮፓ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ድቀት ማድረሱንና የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ በ11.9 በመቶ መቀነሱን የዘገበው ቢቢሲ፣ የስፔን ኢኮኖሚ ታይቶ የማይታወቅ የ18.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንና የፈረንሳይ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርትም በሁለተኛው ግማሽ አመት የ13.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስረድቷል፡፡
በመላው አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ ወደ 10 ሚሊዮን የተጠጋ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥርም 22 ሺህ ያህል መድረሱን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ 530 ሺህ ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ደቡብ አፍሪካ፤ በአህጉሪቱ በተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች ሲሆን ግብጽ በ95 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ45 ሺህ፣ ጋና በ39 ሺህ፣ አልጀሪያ በ33 ሺህ ተጠቂዎች እንደሚከተሉ ተነግሯል፡፡ በአፍሪካ በቂ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተደረገ አለመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት እያፋጠነው እንደሚገኝ የዘገበው ሮይተርስ፣ በአህጉሪቱ ከተደረጉት 9 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በ10 አገራት መደረጋቸውን አመልክቷል:: ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ሞሪሺየስ እያንዳንዳቸው ከ200 ሺህ በላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎችን ማድረጋቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሶስት ሚኒስትሮች ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው በተረጋገጠባት ጋምቢያ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ሃሙስ ለ21 ቀናት የሚቆይ የሰዓት እላፊና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ የተነገረ ሲሆን፣ በሞዛምቢክም ከትናንት ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ አዲስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተነግሯል፡፡
በደቡብ አፍሪካ 24 ሺህ ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን አልጀዚራ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ ያስነበበ ሲሆን ቢቢሲ በበኩሉ፤ በደቡብ ሱዳን 78 ያህል የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና አንዱ ለሞት መዳረጉን ዘግቧል፡፡

Read 1321 times