Wednesday, 12 August 2020 12:32

“ለ57 ዓመት ለፍቼ ያፈራሁት ሀብት ወድሞ ያለ መጦሪያ ቀርቻለሁ” (ወ/ሮ ሽቶ ተገኝ፤)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  እኔ የ70 ዓመት አዛውንት ነኝ፤ በአለም ማያ 01 ቀበሌ ላለፉት 57 ዓመታት ኖሬያለሁ:: አግብቼ ንብረት አፍርቼበታለሁ፤ ከሰውም ጥሩ ፍቅር አለኝ፡፡ ምንም በማላውቀው ሰኔ 23 7፡30 ላይ ነው ዱብዳ የወረደብኝ:: እኔ ከሀረር 23 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከምትገኝ ኮምቦልቻ የምትባል ቦታ ችግር ተፈጠረ ሲባል፣ እዚያ ላሉ ዘመዶቼ ነበር ዋይ ዋይ እያልኩ የምጨነቀው፡፡ እኔንማ በኖርኩበት ባሳደግኳቸው ልጆች ማን ይነካኛል ብዬ አስቤ፡፡ ከዚያ ቀን በ7፡30 ላይ የውጭ” በር ገንጥለው ገቡ፤ መዓት ናቸው፡፡ “ልጆቼ ምን አደረግኳችሁ? ምን በደልኳችሁ?” ብዬ ጡቴን አውጥቼ “በጠባችሁት ጡት ይዣችኋለሁ፤ እኔ ከማን ነው ጠቤ? ምን አደረግኩኝ? እባካችሁ ተውኝ” ስላቸው፤ “አንቺን ማንም አይነካሽም፤ ነይ ውጭ” ብለው ከደረጃ ላይ ጐትተው ሜዳ ላይ ወረወሩኝ፡፡ “በእጄ የተወለዳችሁ ናችሁ፤ እኔም ለማንም ክፉ አይደለሁም፤ በፈጠራችሁ ተውኝ” ብልም አልሰሙም፡፡ “እሺ በእሳት አታቃጥሉኝ፤ ስቃዬን አታብዙት፤ ባይሆን አርዳችሁ ገላግሉኝ” አልኩ፡፡ የቤቱ ጭስ አፈነኝ፤ ጆሮዬም ተዘጋ፤ አይኔም ተደፈነ፡፡
የድንጋይ ናዳ ከላይ ይወርድብኛል፡፡ እኔ አክስት የሆንኳት ልጅ ቤት ነበረች፡፡ “ዛሬ እኔ ቀፎኛል፤ ተነሽ እንውጣ” ስትለኝ “አርፈሽ ቁጭ በይ፤ እኔን ማንም አይነካኝም፡፡ ይሄ ከተወለድኩበት ቦታ በላይ የምወደው፣ ወግ ማዕረግ ያየሁበት ቦታ ነው” ብዬ ቆይቼ ነው ይሄን ሁሉ መከራ የተቀበልኩት፡፡ እሷን አንዴ እሳት ውስጥ ይከቷታል፤ አንዴ ያወጧታል፤ በስንት መከራ ነፍሳችን ተረፈ፡፡ 57 ዓመት ሙሉ ያፈራሁትን ንብረት፣ ግሮሰሪዬን፣ እቃዬን፣ ገንዘቤን በሙሉ በእሳት አውደመው፣ አልቃጠል ያለውን ቴሌቪዥን… ፍሪጅ ስብርብር አድርገው ያለ መጦሪያ አስቀሩኝ፡፡ አሁን ጉልበቴ ደክሟል፤ ሰርቼ እተካዋለሁ አልልም፡፡ 70 ዓመት ሆኖኛል:: መጦሪያ የለኝም፤ (ለቅሶ)…ለምን ይሄ መከራ እንደደረሰብኝ አላውቅም፡፡
ከዚህ በኋላ ጐዳና ላይ ወድቄ ከመለመን ውጭ ሌላ ተስፋ የለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚህ ቤት  ፀሐፊ የሆነና አንድ ፖሊስ ተከራይ ነበሩኝ፡፡ ፖሊሱ “መሳሪያ ደብቋል፤ አውጪ” ብለው የሁለቱንም ተከራዮች ቤት ከእነ እቃቸው ነው ያወደሙት፡፡ መንግሰትና ህግ ባለበት አገር እንዲህ አይነት ለጆሮ የሚዘገንን ጥቃት ነው የደረሰብን፡፡ መንግስት አጥፊዎቹን ይቅጣልን፤ እኛስ እድሜያችን ሄዷል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚኖሩት ልጆቻችን ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ ዙሪያው ገደል ነው የሆነብን፡፡ ደማችን ፈሰሰ፤ ሀብታችን ወደመ፡፡ ወዴት እንድረስ? በቀጣይስ ሌላ መከራ አይደርስብን እንደሆነ በምን እናውቃለን? እስካሁን በምን ምክንያት ይሄ ሁሉ ግፍ እንደደረሰብን አናውቅም፡፡ መንግስት ይድረስልን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳያችንን ይሰማልን፡፡ ከዚህ በላይ ምንም የምለው የለኝም፡፡ ያገር ያለህ፤ የወገን ያለህ… የመንግስት ያለህ መከራችን ይብቃ፡፡



Read 1308 times