Saturday, 15 August 2020 13:56

የሆድ ሕመም -- በእርግዝና ጊዜ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

በዚህ እትም የምናስነብባችሁ አንዲት ሴት እርግዝና ላይ እያለች ስለሚሰሙዋት የውስጥ በተለይም የሆድ ሕመም ይሆናል፡፡ በቅድሚያ ግን ስለኮሮና ቫይረስ ሊረሱ የማይገባቸው ነገሮችን ለማስታወስ ያህል መረጃው ያወጣውን ታነቡ ዘንድ ግብዣችን ነው፡፡
አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ እያለች ደህንነት የሚሰማት ከሆነ ….እኔ ጤንነት ይሰማኛል… ስለዚህ ወደ ሆስፒታል መሄድ አይገባኝም…የሚል ስሜት ውስጥ እንዳትገባ አስቀድማ መጠንቀቅ ይገባታል:: የቀጠሮ ጊዜዋን በማክበር ወደሕክምና ባለሙያ በመቅረብ የራስዋንና የልጅዋን ጤንነት መከታተል አለባት፡፡
ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችም ስለደህንነታቸው በወትሮው እንቅስቃሴአቸው ሊያስቡ እና ዝግጁ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ እርጉዝ ሴቶችም የህክምና አገልግሎት የሚያገኙባቸውን የህክምና ተቋማት ደህንነት ሊተማመኑበት ይገባል፡፡
አንዲት እርጉዝ ሴት የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን በራስዋ ላይ ካየች እና በማንኛውም መንገድ የደህንነት ስሜት ካጣች ከሐኪምዋ ጋር መነጋገር አለባት፡፡ ባለሙያዎቹ በሚሰጡት ምክር መሰረትም ቀጣዩን ጉዞዋን ማስተካከል ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ከላይ ያነበባችሁት በወቅቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው …..የሰዎችን ጤናና ሕይወት አደገኛ ሁኔታ ላይ የጣለው ….እስከአሁንም ገና መድሀኒቱ በውል ያልተረጋገጠለት….ክትባቱም ገና በምርምር ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስን ጥንቃቄ ለማስታወስ የሚረዳ ነው:: በእርግጥ የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑ ሲነገር እነሆ አምስተኛ ወሩን (እ.ኤ.አ March 13--August 13,2020) የጨረሰ ሲሆን በሰዎች ዘንድ መተላለፊያው መንገዶቹ ላይ ጥንቃቄ በማድረጉ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ቸል ተኛነት ስለሚታይ ማስታወስ ተገቢ ነው በሚል ነው የሆድ እቃ ህመምና እርግዝና የሚለውን መረጃ ያገኘንበት ድረገጽ ይድረስ ለአንባቢ ያለው፡፡ እኛም እነሆ አድርሰናል፡፡  
የሆድ እቃ ሕመም በእርግዝና ጊዜ ሊከሰት የሚችልና ብዙ ጊዜም ለዚህ ስሜት መጨነቅ የማይገባ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን አንዳድ ጊዜ የሌላ ሕመም ምልክት ሊሆን እንደሚችልም ችላ ማለት አይገባም፡፡
በእርግዝና ጊዜ የሚሰከት የሆድ ሕመም ስሜት መካከለኛ ወይንም የማያስጨንቅ ከሆነ ወይንም እንቅስቃሴን…አካባቢን…አመጋገብን…ወይንም ወደ መጸዳጃ ቤት በሚገቡበት ወቅት የሚተው እና ቆይቶ የሚመለስ ወይንም እስከጭርሱንም የህመም ስሜቱን የሚተው ከሆነ ዝም ብሎ ማዳመጥ አይከፋም፡፡ ነገር ግን የሚያስጨንቅና ተከታታይነት ያለው ሕመም ከሆነ ሐኪምን ማማከር ግድ ይሆናል፡፡
ጉዳት የሌላቸው የሆድ እቃ ሕመሞች….አንዳንዴም ዝቅተኛ አንዳንዴ ደግሞ ኃይለኛ የሚሆን ስሜት ያላቸው ሲሆን ምክንያቱ ከሚከተሉት መካከል ሊሆን ይችላል፡፡  
የህመም ስሜቱ እየጨመረ የሚሄድ የሆድ እቃ ሕመም በአንድ አቅጣጫ ወይንም በሆድ የታችኛው ክፍል የሚሆን ከሆነ ምናልባትም ከጽንሱ እድገት ጋር በተያያዘ ከሚኖር ከጡንቻዎች መወጣጠር ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡
የሆድ ድርቀት ሲኖር (ይህ በእርግዝና ጊዜ ብዙ ጊዜ የተለመደ ነው)
በነፋስ አካባቢ ከመቆየት ወይንም ከቅዝቃዜ ጋር በተያያዘ ስሜቱ ሊከሰት ይችላል፡፡
ስለዚህ ምክንያቶቹ ከላይ የተገለጹትና ሌሎችም ሊሆኑ በሚችሉ ምክንያቶች አንዲት እርጉዝ ሴት የሆድ ህመም ሲኖራት የሚከተሉት ምልክቶች ሊኖሩአት ስለሚችሉ አፋጣኝ የሆነ የሐኪም እርዳታ ያስፈልጋታል፡፡
መድማት ወይንም የደም ነጠብጣብ በውስጥ ሱሪ ላይ የሚታይ ከሆነ፤
በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ሰውነትን የሚያኮማትር የሚያስጨንቅ ወይንም ተመሳሳይ የሆነ ስሜት ካለው ፤
በብልት በኩል ባልተለመደ መልኩ ፈሳሽ የሚታይ ከሆነ፤
በታችኛው የወገብ ክፍል ሕመም ካለው፤
ስቃይ ወይንም ትኩሳት የሚሰማ ከሆነ፤
ከ30-60 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ ቢያርፉበትም ሕመሙ የማይተው ወይንም የማይቀንስ ከሆነ ምናልባት የሌላ ሕመም ምልክት ሊሆን ስለሚችል እርዳታ ለማግኘት በአስቸኳይ ሕክምና ማግኘት ይገባል፡፡
ከተጠቀሱት በተጨማሪ አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ እያለች የሆድ ሕመም ሊሰማት ይችላል ሲባል ከተለመደው ወይንም በትእግስት የእርግዝናው ጊዜ እስኪያበቃ ለመጠበቅ የማያስችሉ ከተባሉት ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ከማህጸን ውጭ እርግዝና…
ይህ እርግዝና ከማህጸን ውጭ ባሉ ለምሳሌም (fallopian tube) በሚባለው አካባቢ ቢፈጠር እርግዝናው ወደፊት መቀጠል ወይንም ማደግ ስለማይችል በሕክምና መወገድ ይገባዋል:: ወደሕክምናው ከመድረስ በፊት ሕመሙ የገጠማት ሴት ስሜት…
የሆድ ሕመም እና መድማት፤
በትከሻ አካባቢ ህመም(ስቃይ)፤
ወደመጸዳጃ ቤት ቢሄዱ ምቾት ማጣት (በሚሰማው ህመም ምክንያት በቀላሉ መጠቀም አለመቻል)፤
የጽንስ መቋረጥ ወይንም የመቋረጥ ስሜት..
አንዲት እርጉዝ ሴት የሆድ ሕመም ሊሰማት ከሚችሉባቸው ምክንያቶች አንዱ የእርግዝናው ጊዜ ከ24 ሳምንት በፊት ባለበት ወቅት የሚከሰት መድማት ሲሆን ይህም ምናልባት ጽንሱ ሕይወቱን ማጣቱን ሊያመላክት ይችላል:: በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የደም ምልክት እየታየ ጽንሱ ህይወቱን የሚቀጥልበት አጋጣሚም ሊኖር ይችላል፡፡   
በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት (Pre-eclampsia)
የሆድ ሕመም በቀኝ በኩል ከደረት አጥንት ስር ሲሰማ በእርግጥ የጽንሱን እያደገ መምጣት የሚያሳይ ሲሆን ይህም ማህጸን ወደላይ ሊገፋው የሚሰማ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በተለይም በቀኝ ጎን በኩል ከባድ የሆነ ህመም የሚሰማበት ከሆነ ምልክቱ የከፍተኛ የደም ግፊት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም አንዳንድ እናቶችን ጉዳት ላይ የሚጥል ሲሆን የሚጀምረውም በእርግዝናው ከ20 ሳምንታት በሁዋላ ወይንም ልክ ልጁ እንደተወለደ ነው፡፡ ለዚህ ሕመም ሌሎች ምልክቶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከፍተኛ የሆነ የእራስ ሕመም፤
የእይታ ችግር፤
የፊት…የእጅ…የእግር…እብጠት…የመሳሰሉት ምልክቶች ይታያሉ፡፡
ጊዜው ያልደረሰ ምጥ መምጣት
እርግዝናው ከ37 ሳምንታት በታች ጊዜ ያለው ከሆነ እና የሆድ ሕመም የሚሰማቸው ከሆነ ምናልባትም የእርግዝና ጊዜው ሳይጠናቀቅ ሊወለድ ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል መሄድ ይገባል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የእንግዴ ልጅ ስፍራውን መልቀቅ….የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመሳሰሉት ሁሉ በእርግዝና ላይ ላለች ሴት የሆድ ሕመም ሊያስከትሉ ስለሚችሉ በአፋጣኝ ወደሕክምና መሄድ ይገባል፡፡


Read 17667 times