Saturday, 15 August 2020 14:15

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ህወኃት እና ፌደራል መንግስትን እንዲያስታርቁ ተጠየቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

     - ክራይሲስ ግሩፕ ፌደራል መንግስትና ህወኃት እንዲታረቁ ይፈልጋል
                      - ለደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጥያቄ አቅርቧል

            የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግስትንና የትግራይ ክልላዊ መንግስትን እንዲያስታርቁ አለማቀፉ የግጭት ትንተና ቡድን (ክራይሲስ ግሩፕ) ጠየቀ፡፡
ቡድኑ ከትናንት በስቲያ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የፌደራል መንግስቱና ትግራይን እየመራ ባለው ህወኃት መካከል ያለው ፍጥጫ ለሀገሪቱ ሠላምና ዘላቂ ህልውና አስጊ መሆኑን በግምገማ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው የፖለቲካ ውጥረት በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውንና በብዙዎች ተስፋ የተጣለበትን ሽግግር ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑን የጠቆመው ክራይሲስ ግሩፕ፤ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ከዚህ በፊት ሲገልጿቸው የነበሩ የእርቅና የሠላም ንግግሮችን ወደ ተግባር እንዲለወጡ ጠይቋል፡፡
ሁለቱ ሃይሎች በአፋጣኝ ወደ እርቅ የማይሄዱ ከሆነ የፖለቲካ ሽግግሩ እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችል ያስገነዘበው ቡድኑ፤ በኦሮሚያ ከተሞች በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረው ችግርም ሀገሪቱ የጀመረችውን ፖለቲካዊ ሽግግር አደጋ ላይ የሚጥል አደገኛ ምልክት ነው ብሏል::
በኢትዮጵያ የተጀመረው የፖለቲካ ሽግግር በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፉ መሆኑን ያመለከተው ክራይሲስ ግሩፕ፤ ህወኃት እና የፌደራል መንግስት በየፊናቸው የያዙት ጽንፍ ሀገሪቱን የገደል ጫፍ ላይ ያደረሰ አደገኛና ነው ብሏል፡፡
በዚህ የእርቅ ሂደት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም እንዲሳተፉ ቡድኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዚህ የሽምግልና ሂደት አሸማጋዮች የፌደራል መንግስት፣ በትግራይ ክልል ላይ ምንም አይነት የሃይልም ሆነ የፋይናንስ እቀባ እርምጃ እንዳይወስድ እንዲሁም የትግራይ ክልላዊ መንግስት ደግሞ ለማካሄድ ያቀደውን ምርጫ እንዲተው ማግባባት ይኖርባቸዋል ብሏል - ክራይሲስ ግሩፕ፡፡  


Read 1111 times