Print this page
Saturday, 15 August 2020 14:28

የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም፤ ያለፈ ትርክትና ዘርን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ክርክሮችን የሚከለክል ህግ እንዲወጣ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

       የፀጥታ አካላት አደረጃጀትም ሊፈተሽ ይገባል ብሏል

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ በኦሮሚያ አካባቢያዎች የተፈጠረውን ሁከትና ግርግር አስመልክቶ የምልከታ ሪፖርት ያወጣው የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም፤በሀገሪቱ ለደም አፋሳሽ ግጭቶች እየዳረጉ ያሉ የፖለቲካ ክርክሮች ከእንግዲህ ያለፈ ትርክትንና ዘርን መሠረት ያደረጉ እንዳይሆኑ የሚከለክል ህግ እንዲወጣ ጠየቀ፡፡  
ተቋሙ ችግር ተከስቶባቸዋል ወደተባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይ ወደ ምዕራብ አርሲ ባለሙያዎችን አሠማርቶ ምልከታ ማድረጉን ጠቁሞ፤ በምልከታውም በሁከትና ግርግሩ በዜጐች ላይ እጅግ አሠቃቂና በአንድ ሰብአዊ ፍጡር ይደረጋል ተብሎ የማይታመን ወንጀል መፈፀሙን መገንዘቡን አስታውቋል፡፡ ግርግርና ሁከቱን ተከትሎም ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ማረጋገጡን አመልክቷል፤ ተቋሙ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ብሔርን፣ በሌሎች ሃይማኖትን፣ በትላልቅ ከተሞች ደግሞ የፖለቲካ ውግንናን (የመንግስት ደጋፊዎች ናቸው በሚል) መሰረት በማድረግ በዜጐች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነው ተቋሙ በሪፖርቱ ያመለከተው::
በአብዛኞቹ አካባቢዎች የተደራጁ ሃይሎች ጥቃት ሲፈጽሙ የፀጥታ አካላት #ትዕዛዝ አልተሰጠንም; በሚል ህብረተሰቡን ከጥቃት ለመከላከል ጥረት አለማድረጋቸውንም ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጥቃቶች እንዳይደገሙ ዘላቂ መፍትሔዎች መታሠብ እንዳለባቸው የጠቆመው የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋሙ፤ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮችም ላይ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ለመሰል ጥቃቶች መፈፀም መነሻና ገፊ ምክንያት እየሆነ ያለው ያለፈ ታሪክን የተመለከተ የተዛባ ትርክት መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ፤ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ይቻል ዘንድ ከእንግዲህ የሚደረጉ የፖለቲካ ውይይቶችና ክርክሮች ያለፈ ትርክትንና ዘርን መሠረት ያደረጉ እንዳይሆኑ የሚከለክል ህግ ሊደነገግ ይገባል ብሏል፡፡  የፀጥታ አካላት አደረጃጀትም ሊፈተሽ እንደሚገባው ያመለከተው ተቋሙ፤ ሁሉም የሀገሪቱ የፀጥታ ሃይሎች በፌደራል ፖሊስ ስር መሆን እንዳለባቸው ምክረ ሃሳቡን  አቅርቧል፡፡ መንግስት ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽም፤ የተጀመረው ህግን የማስከበር ተግባር የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቋል፡፡  

Read 6138 times