Saturday, 15 August 2020 14:31

ኢሠመኮ በኦሮሚያ በተፈጠረው ሁከት ጥቃት የደረሰባቸው አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 - መንግስት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስቧል
           - የግድያ ማስፈራሪያ እየተሰነዘረባቸው ነው ብሏል

                      የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን “አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች” በሚል ትናንት አርብ ረፋድ ላይ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፣ በኦሮሚያ በተፈጠረው ሁከት ጉዳት የደረሰባቸው አሁንም ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ጠቁሞ፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ የተከሰተውን ሁከትና ግርግር አስመልክቶ ባከናወነው ቅድመ ምርመራ፣ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው የነበሩ ዜጐች አሁንም በስጋት ውስጥ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ከ40 በላይ በሚሆኑ ችግሩ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የምርመራ ቡድን አሠማርቶ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ቤተሰቦችና የመንግስት አካላት በማነጋገር መረጃ ለማሰባሰብና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ጥረት ማድረጉን ጠቁሟል፡፡
በዚህ ምርመራ ወቅት የታዩና ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውንም ኮሚሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው የዘረዘረ ሲሆን በዋናነት ጥቃት ተፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች የጥቃቱ ሠለባዎች አሁንም ከተለያዩ ቡድኖችና የህብረተሰብ ክፍሎች ዛቻዎች እየደረሰባቸው መሆኑን መረዳቱን አስታውቋል፡፡
ዛቻና ማስፈራሪያ ከደረሳቸው መካከልም በዶዶላ ከተማ ግጭቱ ከደረሰ በኋላ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከ60 በላይ ሰዎች ስም ተዘርዝሮ ከተማውን ለቀው እንዲወጡ፣ ካልወጡ ግን እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን የሚገልጽ ወረቀት መሠራጨቱን፣ ለባቱ ከተማ ተጐጂዎች አሁንም “ከተማውን ለቃችሁ ውጡ” የሚል ማስፈራሪያ በስልክና በአካል እየደረሳቸው መሆኑን፣ በሻሸመኔ ከተማ ደግሞ ያልታወቁ ሰዎች ቤት ለቤት እየዞሩ “ከ5ሺህ እስከ 10ሺህ ብር ካላመጣችሁ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን፤ እናንተንም እንገድላችኋለን” የሚል ዛቻ እየተሰነዘረባቸው መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በመንግስት የፀጥታ አካላት ሳይቀሩ ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህም ውስጥ በቡራዩ ከተማ በተለይ ከታ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ እንዲሁም በጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ ተጠቅሰዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ማስፈራሪያና ዛቻዎችን በመመርመር የመከላከልና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ስራ እንዲሠራ፣ እንዲሁም ተጨማሪ የፀጥታ ጥበቃ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በዚህ አስቸኳይ ሪፖርቱ ኮሚሽኑ ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቀው ሌላው ጉዳይ የሰብአዊ እርዳታን ይመለከታል፡፡
ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው  ያስገነዘበው ኮሚሽኑ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ አሁንም በየሰው ቤት፣ በሃይማኖት ተቋማትና በሌሎች ስፍራዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው ቦታዎች መካከልም በዶዶላ ከተማ በገብረክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ በአሶሳ ከተማ ገብርኤል ቤተክርስቲያን፣ በሻሸመኔ ከተማ ተክለሃይማኖት፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ ጊዮርጊስና ኡራኤል አብያተክርስቲያናት እንዲሁም አጋርፋ እርሻ ኮሌጅ ተጠቅሰዋል፡፡
አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በመንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ቢደረግላቸውም፣ የሚሠጣቸው የእለት ምግብ እርዳታና የህክምና አገልግሎት በቂ አይደለም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ በተጨማሪም በቂ የደህንነት ዋስትና ባልተሠጠበት ሁኔታ “ተፈናቃዮችን ወደ ቤታችሁ ተመለሱ” በሚል ከመንግስት አካላት የሚደርሰው ጫናም ተገቢ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
መፍትሔውን በተመለከተም፤ የፌደራልና የክልሉ መንግስት ለተፈናቃዮች ተገቢውን ዋስትና በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ በፍጥነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ ማድረግ ነው - ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
የእስረኞች አያያዝ ሁኔታንም የገመገመው ኮሚሽኑ፤ አብዛኛው አመቺ ባልሆነ ሁኔታ መታሠራቸውን ጠቁሞ ማስተካከያ እንዲደረግ እንዲሁም አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጥ አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ ከሁለት ሣምንታት በፊት ጀምሮ 40 በሚደርሱ ችግሩ ያጋጠማቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የምርመራ ቡድን አሠማርቶ የደረሰውን የጥቃትና ጉዳት መጠን እየመረመረ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ሙሉ የምርመራ ስራውም በጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑንና ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡


Read 5199 times